1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃ ቀንድ የጋዜጠኞች ይዞታ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 16 2005

ሶማሊያ ዉስጥ በያዝነዉ የጎርጎሮሳዊ ዓመት 2013 ከባተ የተገደሉ ጋዜጠኞች ቁጥር አምስት ደርሷል። ለጋዜጠኞች መብት የሚሟገተዉ ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች /RSF/ ሰሞኑን አንድ የሶማሊያ ራዲዮ ጋዜጠኛ መገደሉን በማዉገዝ፤ መቅዲሾ ዛሬም ለጋዜጠኞችም ሆነ ለኗሪዎቿ ፀጥታዋ የተረጋገጠነዉ ማለት እንደማይቻል አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/18Mt9
ምስል picture-alliance/dpa

ድርጅታቸዉ በአፍሪቃዉ ቀንድ በሚገኙ ሀገሮች የሚታየዉ የጋዜጠኞች ይዞታ እንደሚያሳስበዉ ያመለከቱት የRSF የአፍሪቃ ጉዳይ ተንታኝ አምብሩዋዝ ፒየር ቤተሰቦቹ ከሚገኙበት ወደሌላ አካባቢ መዛወሩ የተነገረዉ የጋዜጠኛ ዉብሸት ታዬ እና ህክምና ማግኘት አለመቻሏ የተሰማዉ የጋዜጣ አምደኛ ርዕዮተ ዓለሙንም ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን ገልፀዋል።

ሶማሊያዉ ጋዜጠኛ ሞሐመድ ኢብራሂም ራጋ ቀደም ሲል የእንገልሃለን ዛቻ ደርሶት ሀገሩን ለቆ ወደኬንያና ዑጋንዳ ተሰድዶ ቆይቷል። ያኔ የእስላማዊዉ ታጣቂ አሸባብ መቅዲሾም ሆነች በአብዛኛዉ የሶማሊያ ግዛት ጥቃቱን በየዕለቱ ይሰነዝር ነበር። ካለፉት ወራት ወዲህ ቡድኑ ጠንካራ ይዞታዉ ትባል ከነበረችዉ ኪስማዮ ሳይቀር ለቅቋል መባልን ተከትሎ ዋና ከተማዋ መቃዲሾን የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት መሪዎችና የምዕራቡ ዓለም ባለስልጣናት ሲረግጧት ራጋ ሀገር ሰላም ነዉ በሚል ወደትዉልድ ስፍራዉ ተመለሰ። ዛቻዉ ግን በዛቻነት ብቻ አልቀረም ባለፈዉ እሁድ አመሻሹ ላይ ሁለት የታጠቁ ሰዎች በርካታ ጥይት ደረቱና ጭንቅላቱ ላይ ተኩሰዉ መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ህይወቱ አለፈ።

Somalia Mogadischu Anschlag auf den neuen Präsidenten
ምስል Reuters

አብሩዋዝ ፒየር ለግድያዉ ኃላፊነት የወሰደ አካል ባይኖርም ማስፈራሪያ የደረሰዉ ጋዜጠኛ ነበር ይላሉ፤

«በዚህ ሳምንት የተገደለዉን ጋዜጠኛ አስመልክቶ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ ያለ አካል የለም። ኢላማ ተድርጎ የነበረ ጋዜጠኛ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል። ራጌ በስደት ከቆየበት ኬንያያ ዑጋንዳ ገና መመለሱ ነበር። በመሠረቱ ሶማሊያን ለቅቆ የቆየዉ ለድህንነቱ ስጋት ምክንያት ነዉ። ወደኬንያ እና ዑጋናዳ የሄደዉ የግድያ ዛቻ ስለደረሰዉ ነዉ። ያኔ ዛቻዉን የላከለት እስላማዊዉ ሚሊሺያ አሸባብ ነዉ። አሁን መቅዲሾ ሲመለስ ዛቻ የላኩለት ኃይሎች በመጨረሻ ሊገድሉት ችለዋል ብሎ መገመት ይቻላል።»

RSF የጋዜጠኛዉን መገደል በኮነነበት ዘገባዉ ምስራቅ አፍሪቃዉቱ ሀገር ዛሬም ለጋዜጠኞችም ሆነ ለኗሪዎቿ ፀጥታዋ የተረጋገጠ እንዳልሆነችም በግልፅ አስፍሯል። ሶማሊያ ዉስጥ ቀደም ባሉት ዓመታት ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ጋዜጠኞች በጠራራ ፀሀይ የተገደሉ ሲሆን ዘንድሮም በአራት ወራት ዉስጥ ሞሐመድ ኢብራሂም ራጌን ጨምሮ አምስት ጋዜጠኞች ህይወታቸዉን በታጣቂዎች እጅ አጥተዋል። ፒየር፤

«እንደርጅታችን እይታ ከሆነ የፀጥታዉ ሁኔታ በተለይ ለጋዜጠኖች አሁንም እጅግ አስተማማኝ አይደለም። ከአንድ ዓመት በፊት ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች መቅዲሾ በዓለማችን ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ ከሆኑ አስር ቦታዎች አንዷ መሆኗን ገልጿል። አሁን አንዳንድ ሰዎች የፀጥታ ሁኔታዉ ተሻሽሏል፤ ተቋማቱ እየተሻሻሉ ነዉ፤ በዚያ ላይ የየዕለት ኑሮ ሁኔታዉ መቅዲሾ ዉስጥ እየተረጋጋና ወደመደበኛዉ ሁኔታ እየተመለሰ ነዉ ሲሉ እንሰማለን። ነገር ግን እኛ ይህ እንደሚባለዉ አይደለም፤ በተለይ ለመረጃ ጉዳይ ተዋናዮች መቅዲሾ የምድር ሲኦል ናት እንላለን።»

Somalia islamistisicher Miliz in Balad bei Mogadishu
ምስል AP

በማያያዝም ድርጅታቸዉ በአፍሪቃዉ ቀን በሚገኙ ሀገሮች ጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ተግባራትን እንደሚከታተል ያመለከቱት አምብሩዋዝ ፒየር ኢትዮጵያ ዉስጥም እስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኞች ይዞታ እና የፍርድ ሂደታቸዉንም በአካል ተገኝተዉ መመልከታቸዉን ገልፀዋል። የፀረ ሽብር ህግን ተንተርሶ ጋዜጠኞቹ የቀረበዉን ክስ RSF ቀደም ሲልም እንዳወገዘ በመግለፅም በተለይም ሰሞኑን ከነበረበት የአዲስ አበባ እስር ቤት ራቅ ወዳለ ስፍራ መዛወሩ የተገለፀዉን የቀድሞዉ አዉራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ዉብሸት ታዬን ጉዳይ ከቅርብ ሰዎች ማጣራታቸዉን አመልክተዋል።

«አዎ ስለዉብሸት ታዬ ወደሌላ ስፍራ መዛወር ሰምተናል፤ እኔም ኢትዮጵያ ከሚገኙ ወገኖች ዉብሸት ዝዋይ ከተማ ወደሚገኝ የፌደራል እስር ቤት መወሰዱ እዉነት መሆኑን አረጋግጫለሁ። ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነዉ የሚገኘዉ፤ ማለትም እስከዛሬ ከታሰረበት ከዋና ከተማዉ ዉጭ ነዉ። ይህ በእርግጥም አሳዛኝ ዜና ነዉ። ምክንያቱም ይህን ሰዉ ከዋና ከተማዋ ዉጭ ከቤተሰቦቹ አርቆ ለማሰር ምንም የቀረበ ምክንያት የለም። እንደሰማሁት ቤተሰቦች አስቀድሞም እስር ቤት እሱን ለማየትና ለመጎብኘት ችግር ነበረባቸዉ። አሁን ደግሞ ሁኔታዉ ይበልጥ የከፋ ይሆናል። የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡትን ምክንያት እስካሁን አልሰማንም፤ ነገር ግን አሳሳቢ ነዉ። ምክንያቱም የእስር ይዞታዉና ቤተሰቦቹን የማግኘቱ ጉዳይ ይበልጥ የከፋ ይሆናል።»

Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ዉስጥ በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች አንዷ ርዕዮት አለሙ ለገጠማት የጤና እክል ህክምና ማግኘት አለመቻሏ ይሰማል። ወህኒ ዉስጥ ከህመሟ ጋ የምትታገለዉ ርዕዮትን ፅናት ያደነቁት ፒየር RSF ጋዜጠኛ ዉብሸትም ሆነ እሷ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብታቸዉን ስለተጠቀሙ አሸባሪዎች ሊባሉ እንደማይገባ ማሳሰቡን በድጋሚ ልግለፀዉ ይላሉ፤

«ዉብሸት ታዬ እና ርዕዮት ዓለሙ በጎርጎሮሳዊዉ 2011 የበጋ ወራት ነዉ የታሰሩት። ታስረዉ የሚገኙትም በአሸባሪነት ተከሰዉ ነዉ። ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች ደጋግሞ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብትን የፀረ ሽብሩን ህግ ተጠቅመዉ እንዴት እንደሚጥሱ አመልክቷል። አዉግዘነዋል፤ በግልፅም ዉብሸት ታዬና ርዕዮት ዓለሙ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብታቸዉን ተጠቀሙ እንጂ አሸባሪዎች አይደሉም፤ ሊፈቱ ይገባል ብለናል። ርዕዮት ዓለሙን በሚመለከት ይህች ሴት ጋዜጠኛ ባለፈዉ ሳምንት ከዩኔስኮ የፕረስ ነጻነት ሽልማት መሸለሟን ማስታወስ እሻለሁ። ይህም የእሷ ሁኔታ እና ያደረገችዉ አስተዋፅኦ እዉቅና ተሰጥቶት ጥብቅና ሊቆሙላት የሚገባ ጋዜጠኛ ናት። ከሁለት ዓመት በፊት ይህች ጋዜጠኛ ባለባት የጤና እክል ምክንያት ልትለቀቅ ይገባል በሚል ጠይቀን ነበር፤ ግን እስካሁን ያ ተግባራዊ አልሆነም። አሁንም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ህክምና እንድታገኝ እንዲፈቅዱላት እንጠይቃለን።»

አምብሩዋዝ ፒየር RSF ደግሞ ደጋግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመንግስት ባለስልጣናት ያቀረበዉ ጥሪ ምላሽ አለማግኘቱን በመግለፅም አሁንም ይህንኑ ጥሪ እንደሚቀጥሉበት አመልክተዋል። በተለያዩ ጊዜያት ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋቾች በቅርቡም የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ እየከፋ መሄዱን አመልክተዋል። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ሆነ ከሀገሪቱ ዋነኛ ለጋሾች ለሚቀርብ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚተች ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ አለመስጠታቸዉን ያመለከቱት ፒየር አስተዳደሩ ትችትን መቀበል የሚከብደዉ እንደሚመስላቸዉ ነዉ የግል ትንታኔዬ ሲሉ የገለፁት።

Karte Horn of Africa

«በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ስላልሆንኩ የባለስልጣናቱ አዝማሚያ በትክክ ምን እንደሚመስል መረዳት አልችልም። ነገር ግን በኢትዮጵያ እስር ይዞታ፤ እንዲሁም በተናገሩት ወይም በፃፉት ምክንያት ስለሚታሰሩ ሰዎች ሁኔታ ዓለም ዓቀፍ ትኩረት አለ። እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያ በሀገር ዉስጥ ፖሊሲዋም ሆነ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታዋ ከዉጭ ትችት የመቀበል ፍላጎት የላትም። ምናልባት የሚሰነዙ ትችቶችና የዓለም ዓቀፍ መገናና ብዙሃን በሀገራችሁ ዉስጥ የሚከናወኑ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጋቸዉ እንዲህ ያሉ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ያደርጋቸዉ ይሆናል። በእርግጥ በትክክል አዲስ አበባ ለምን ይህን እንደምታደርግ አላዉቅም ግን  በእኔ ትንታኔ አንዱ ምክንያት ይህ ይመስለኛል።»

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ