1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

በአፍሪቃ የትምህርት አሰጣጥ

ዓርብ፣ ጥር 8 2012

አፍሪቃ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ለስራ ገበያው ብቁ እንደማያደርጋቸው በርካታ አፍሪቃውያን ይወቅሳሉ። በውጭ ሀገራት የትምህርት እድል ያገኙ ተማሪዎች እንደሚሉት አፍሪቃ ውስጥ ትምህርት በነባቤ ቃል እንጂ እምብዛም በተግባር ሲሰጥ አይታይም።

https://p.dw.com/p/3WLqm
DW The77Percent | Videostill
ምስል DW

በአፍሪቃ የትምህርት አሰጣጥ

የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ መሪ ኔልሰን ማንደላ «ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ የሚያስችል ትልቅ መሣሪያ ነው» ሲሉ በአንድ ወቅት ተናግረዋል። በኢትዮጵያም ቢሆን «የበላና የተማረ ወድቆ አይወድቅም» የሚለው አባባል ይታወቃል። ቀደም ሲል ለአፍሪቃውያን ፈተናው ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት አለመላካቸው እና አለማስተማራቸው ነበር። አሁን ላይ ይህ ችግር የቀነሰ ቢሆንም  ስራ አለማግኘት እና የትምህርት ጥራቱ የሚያማርራቸው ብዙዎች ናቸው።ወጣት ታንዛናውያን  እንደሚሉት « ታንዛንያ ውስጥ አምስት የስርዓተ ትምሕርት ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ነገር ግን ለይዘቱ አስፈላጊ የሆነው ነገር በአምስቱም ማሻሻያ ውስጥ አልተካተተም። ይህ ማለት ደግሞ የተፃፈው ስርዓተ ትምሕርት እና ከትምህርት ክፍል ውጪ እየሆነ ያለው ፍፁም አይጣጣምም። »
« ትልቁ ችግር ያለን አመራር ነው። ችግሩ ምኑ ጋር እንደሆነ እንኳን አያውቁትም።  የቀድሞ የጨቋኝ ቀኝ ገዢዎችን የትምህርት ስርዓት ነው ዛሬም ወጣቶቻችንን እያስተማሩበት ያለው። የትምህርት ስርዓታችን እንደ ቁማር አሸናፊ እና ተሸናፊ አለበት።»
« እኔ የኤሌክትሮ እንጂነሪንግ ተማሪ ነኝ። ሀገሪቷ በአሁኑ ሰዓት በቴክኖሎጂ ውጥረት ውስጥ ነው የምትገኘው። እኛ በሁለተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ስንሆን ሌሎች ሀገሮች ደግሞ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል። በሰው ሰራሽ አስተውሎት  (Artificial intelligence)  እና በሮቦት በመሳሰሉት ብዙ ቀድመውናል። ባለን የትምህርት አሰጣጥ የተነሳ ከውጭው ሀገራት ጋር ወጥ መሆን አልቻልንም። እኛ ስለኤሎክትሮኒክስ የተማርነው በተግባር የማናየውን ነው።  ክፍል ውስጥ እንዲሁ በቃል ትማራለህ ወደ ቦታው ስትሄድ ግን እንደዛ አይነት ነገር አይተህ አታውቅም። እና በጣም የተለየ ነው።»
እንደ ዮዲት ማሪኪ ያሉ ሌሎች የታንዛንያ ተማሪዎች ደግሞ  ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ጨርሶ ስራ ማግኘታቸውም ያጠራጥራቸዋል። « ከእኔ በፊት ተመርቀው የጨረሱትን ተማሪዎች ሳይ ምን ይውጠኛል ብዬ አስባለሁ። ትምህርት ሊጠቅመኝ ይገባ ነበር አይደል? የተለያዩ አቅጣጫዎች ሊያሳየኝ እና አማራጮች ሊጠቁመኝ ይገባ ነበር። ነገር ግን አንድ አማራጭ ብቻ ነው የሰጠኝ። ይህም አማራጭ አልጠቀመኝም። ያለኝን ጉጉት እና የፈጠራ ችሎታዬን በሙሉ ነው የገደለው። » ትላለች ዮዲት።  የአለም የኢኮኖሚክ መድረክ 38 የአፍሪቃ ሀገራትን ጨምሮ የ 140 ሀገራት የትምህርት ስርዓትን በገመገመበት መዘርዝር ከአፍሪቃ በትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ቀዳሚውን ቦታ የያዘችው የሲሸልስ ደሴት ናት። ከአለም 50 ምርጥ ሀገራት ውስጥ 43ኛውን ስፍራ ይዛለች። ከዛም ቱኒዚያ እና ሞሪሺየስ ይከተላሉ።  ደቡብ አፍሪቃ ደግሞ ከአፍሪቃ 4ኛውን ስፍራ ይዛለች።  ከአፍሪቃ በኢኮኖሚ ልዕለ ኃያል የሆነችው ደቡብ አፍሪቃም ብትሆን ስራ አጥነትን እየታገለች ትገኛለች። ወጣቶቿ ግን ባለ ሙሉ ተስፋ ናቸው። « እኔ በግሌ ብዙም አልጨናነቅም። እስከሚቃና ትንሽ ጊዜ ይወስዳል።  አብዛኞች በመንግስት ላይ ጥገኛ ናቸው። መንግስት ስራ ሊሰጠን ይችላል። ነገር ግን ነቃ ብሎ ለሚፈልጉት ነገር መታገል ያስፈልጋል።» ሌላዋ ተማሪ ደግሞ መንግሥት የትምህርት አሰጣጡን ሊያሻሻል ይገባል ባይ ናት።« ከአሜሪካ የትምህርት አሰጣጥ ጋር ሲነፃፀር እኛ ሁለት አመት ወደኃላ እንቀራለን። አስረኛ ክፍል የምንማረውን እነሱ 8ኛ ክፍል ተምረውታል። ግን አንዳንዴ ስራ ማግኘት እና ጥሩ ትምህርት ቤት መማር ብቻ ሳይሆን ከስር ተነስቶ ወደላይ መስራትም ያስፈልጋል። 

ከኬንያ የመጣችው ዋንጅኩ ስለ ሀገሪቷ ትምህርት አሰጣጥ ስታስረዳ ፣« በፊት የነበረው ስርዓተ ትምሕርት  ተቀይሯል። ከስምንት አራት አራት ማለትም ስምንት አመት አንደኛ እና መለስተኛ ፣አራት ዓመት ሁለተኛ ደረጃ እና ቀጣዩ አራት አመት በከፍተኛ የትምሕርት ተቋም የሚሰጥ ነበር። አሁን ደግሞ ሰባት ሁለት ሁለት ሆኗል። »
ትላለች የ DW ጋዜጠኛዋ። የስምንት አራት አራቱ  የትምህርት እና ሥልጠና ስርዓተ-ትምሕርት አስራ ሁለት የትምህርት አይነቶች ይሰጥበት ነበር የምትለው ዋንጂኩ በአዲሱ ስርዓተ-ትምሕርት የትምህርት አይነቶቹ ቁጥርም መቀነሱን ታስረዳለች።  ያኔ እኔ የተማርኳቸው የትምህርት አይነቶች እንደ ባልትና ፤ እርሻ ፣ ስዕል ፤ ሙዚቃ የመሳሰሉትን መሰጠት አቁመዋል። ስለዚህ ፈተናዎችም አይሰጡም። አሁን ትኩረቱ ሂሳብ፣ ሳይንስ ፣ እንግሊዘኛ የመሳሰሉት ትምህርቶች ላይ ሆኗል።»
ይሁንና  አሁን ብዙም አስፈላጊ አይደሉም ከተባሉትም የትምህርት አይነቶች ብዙ ነገር ቀስሜያለሁ የምትለው ዋንጅሩ መማሯ ለዛሬው ህይወቷ በር ከፋች እንደነበር ታምናለች።
ራቢኡ ደግሞ ከተወለደበት ጋና ውጪ በዴንማርክ እና ብሪታንያ የመማር እድል አግኝቶ ነበር። እዛም ትልቅ ልዩነት አስተውሏል።« ጋና ውስጥ በጣም ብዙ ተማሪዎች ስላሉ ዩንቨርስቲ ውስጥ ያለው የተማሪ እና የመምህር ቁጥር አይመጣጠንም። ጋና ውስጥ በአንድ የትምሕርት ክፍል አንድ መምህር 1000 ተማሪዎችን ሊሆን ይችላል የሚያስተምረው ። 
 ይህም መምህሩ እየተዘዋወሩ ለተማሪዎች ማስረዳትም ይሁን ምክር ለመለገስ አዳጋች እንደሆነ ራቢኡ ይናገራል። ይህንንም ብሪታንያ እና ዴንማርክ ከነበረው ተሞክሮ ጋር ሲያነፃፅር  ከቁጥሩ መብዛት ጋር በተያያዘ ከመምህር የሚገኘው ምላሽ ወይም ምክር ጋና ውስጥ እምብዛም ነው ይላል። 

የኬንያ ዩንቨርስቲ
ምስል Reuters/T. Mukoya
DW The77Percent | Videostill
ምስል DW

ናይጄራዊያን ተማሪዎችስ ምን ይላሉ?
« ናይጄሪያ ውስጥ እየሆነ ያለውን እያያችሁ ነው። ሰዎች ትግል ላይ ናቸው። »
 « አዎ ከጊዜ ጋር ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል። ልጆችንም እጅግ በሚስብ እና በሚያስደስት መልኩ ነው እያስተማሩ ወይም እየሰሩ ያሉት። »
ሌላው ወጣት ግን በዚህ አይስማማም። መንግሥት ትምህርት ሲያጠናቅቁ ስራ የማይሰጥ ከሆነ 14 የትምህርት አይነት መስጠቱ ፋይዳው ምኑ ላይ ነው ሲል ይጠይቃል። ይህ ብቻ አይደለም።
« ትምህርት ቤታችን ውስጥ የኮምፒተር ቤተ ሙከራም ሆነ ክፍል የለም። ሰዎች ኮምፒተር በተግባር እንዴት መጠቀም እንደሚቻልም አያውቁም። ነገር ግን የሚቀርብላቸው ጥያቄን መልስ በወረቀት ላይ መመለስ ይችላሉ። እዛ ላይ ነው ችግሩ። 

የጋና ተማሪዎች
ምስል Imago/F. Stark

ሌላው በተለያየ የአፍሪቃ ሀገራት የሚገኙ ወጣቶች የሚያነሱት ችግር በቂ የትምህርት መገልገያዎች ያለማግኘት ጉዳይ ነው።  በይበልጥ ስለ ትምህርት ነክ ርዕሰ ጉዳዮች የሚፅፈው ዝምባዌያዊ ጋዜጠኛ ሂላሪ ታኩድዝዋ የአፍሪቃን የትምህርት አሰጣጥን በግልፅ ይተቻል። እሱም የአፍሪቃ የትምህርት ስርዓት ነፃ መውጣት አለበት ባይ ነው።«  የአውሮጳውያን ኢምፔሪያሊዝም የትምህርት ስርዓቶችን ከሚያወድሱ የትምህርት አሰጣጥ መላቀቅ አለብን። የአፍሪቃን ታሪክ እና ስኬቶች ስጋት ውስጥ እንዳይከቱ ማለት ነው። የቀኝ ገዚዎች የትምህርት አሰጣጥ ያደረገው ነገር ቢኖር ከአፍሪቃ ይልቅ ይበልጥ ስለ አውሮጳ  ስለ አሜሪካ እና ስለ ምዕራቡ አለም እንዲወራ ነው!» እንደ ናይጄሪያዊው ፀሀፊ ማይክ ኡዞኩቺጉ ከሆነ የአፍሪቃ ሀገራት ከበጀታቸው አንድ አስረኛ የሚሆነውን ለትምህርት ለመመደብ ይቸገራሉ።« መንግሥት ለትምህርት ዘርፍ ዓመታዊ በጀት ሲመድብ ከአጠቃላይ በጀቱ ቢያንስ 12 በመቶውን ለትምህርት መመደብ አለበት።» 
ይላል ናይጀሪያዊው ፀሀፊ።

ልደት አበበ 

ሂሩት መለሰ