1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢራን ፣ ከምርጫው ማግሥት በተቃውሞ ለሞቱት ዛሬ የሚደረገው መታሰቢያ፣

ሐሙስ፣ ሐምሌ 23 2001

የኢራን የተቃውሞው ወገን መሪዎች ሚር ሁሴን ሙሳቪና መህዲ ካሩቢ፣ የአገሪቱ ገዥዎች ያወጡትን ድንጋጌ ችላ በማለት፣ ለተገደሉ ኢራናውያን ዛሬ ይፋ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት እንዲደረግ ጥሪ አስተላለፉ።

https://p.dw.com/p/J0TY
ኔዳንና የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ዓርማ በማድረግ አደባባይ እየወጡ የተቃውሞ ሰልፍ የሚያሳዩ ኢራናውያን፣ምስል AP

በምርጫው የማጭበርበር ተግባር ተፈጽሟል በማለት አደባባይ የወጡና የተገደሉ ኢራናውያን እንዲታሰቡ የተፈለገው፣ ዛሬ ህይወቷን ካጣች 40 ቀን የሆናት ኔዳ አጋ-ሶልታን የተባለችው የኢራን የተቃውሞ ዓርማ የሆነችው ወጣት ሴት በምትዘከርበት ሥነ ሥርዓት ነው። የዜና አውታሮች አንደዘገቡት የኔዳ ወላጅ እናትና የተቃውሞው ወገን መሪዎች፣ ሙሳቪና ካሩቢ ዛሬ ከቀትር በኋላ ቤሸት ኤ ዛኻራ የተባለውን መካነ መቃብር ይጎበኛሉ።--ተክሌ የኋላ--

በጥይት፣ ደረቷ ላይ ተመትታ፣ ህይወቷ ስታልፍ በቀጥታ በእጅ ስልክ አማካኝነት በተነሣ ፊልም፣ ዓለም በሙሉ ዐይቶ ያላዘነና ፣ ድርጊቱን ያላወገዘ አልነበረም። በ 19 ዓመቷ፣ በጥይት የተቀጠፈችው ኔዳ አጋ-ዞልታን ፣ በኢራን፣ ከአንድ ወር ከ 18 ቀናት በፊት በተካሄደው ምርጫ፣ ፕሬዚዳንት ማህሙድ አህማዲነጃድ ዳግም የተመረጡት ድምፅ በማጭበርበር ነው በማለት የተነሣሣው የተቃውሞ ወገን ዓርማ ሆናለች። የ ኔዳ ታሪክ በተጨማሪ፣ ወንጀል የትም ቦታ ይፈጸም ተደብቆ ሊቀር እንደማይችል ጠቋሚ ሆኗል። በአንድ የዐይን ምሥክር የእጅ ስልክ የተነሣውን አጭር ፊልም በዓለም ዙሪያ ለማዳረስ የተቻለው የንዑስ ድረ-ገጽ ባለቤቶች በሆኑ፣ በጀርመን ሀገር ኑዋሪ የሆነውን አሚር ፋርሻድ ኢብራሂሚን በመሳሰሉ የመገናኛ ብዙኀን ሠራተኞች ነው። በስደት የሚኖረው ኢብራሂሚ ፣ ያገሩ የኢራን ህዝብ ፣ እገዳ የሌለበት የመገናኛ-ብዙኀን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን ነው አጥብቆ የሚሻው። አሚር ፋርሻድ ኢብራሂሚ ከ 40 ቀን በፊት ስለተገደለችው ኔዳና ስለተሠራጨው ፊልም እንዲህ ይላል።

«ስለ ኔዳ ግድያ የሚያሳየው ፊልም የደረሰን እኩለ-ሌሊት ላይ ነበር። ፊልሙን ለመላክ በግል የኢንተርኔት ማኅደርም ሆነ የመልእክት ማሳራጫ ዘዴ ለመላክ አዘጋጀነው። በራሴ ንዑስ ድረ-ገጽም አዘጋጅቼው ነበር።»

በ Würzburg ፣ ጀርመን የወደፊቱን የኢንተርኔት አገልግሎት በተመለከተ፣ በመምክር ላይ ባለው ዓለም- አቀፍ ጉባዔ በመሳተፍ ላይ የሚገኘው አሚር ፋርሻድ ኢብራሂሚ እንደሚለው፣ በመገናኛ ብዙኀን ላይ እጅግ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ቢደረግም የኢራን መሪዎች ተቃውሞውን ሊገቱት አይችሉም። የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ፣ እገዳውን ለመቋቋም አዲስ መላ መሻታቸው አይቀሬ ነው።

«የተቃውሞ ስብሰባም ሆነ ሰልፍ በየትኛው ቦታና ሰዓት እንደሚካሄድ ለማሳወቅ ፣ ህዝቡ ንዑስ ድረ ገጾችን አዘጋጅቷል።የተቃውሞው ወገን ይፋ ድር-ገጾች በመላ ተሰናክለዋል። ወዲያውም ነው የሚታወቁት። ይሁን እንጂ፣ አንድ ድረ-ገጽ ሲታገድ ፣ ወዲያው በሌላ ቦታ ፣ እንደገና አዲስ ድረ-ገጽ ይከፈታል።»

ወጣቷ፣ ኔዳ አካን ዞልታን በተገደለችበት 40ኛ ቀን፣ ዛሬ ፣ የማጭበርበር ተግባር እንደተፈጸመበት የተነገረለትን የምርጫ ውጤት የተቃወሙና የተገደሉ እንዲሁም የታሠሩ፣ በአገር ውስጥም በውጭም በሚኖረው የኢራን ማኅበረሰብ ታስበው ነው የሚውሉት።

የተቃውሞ ወገን መሪዎች ሙሳቪና ካሩቢ፣ በመንግሥት እገዳ ሳቢያ የተቃውሞ ስልፍ እንዲደረግ ያስተላለፉት ጥሪ ሠመረም -አልሠመረ፣ ኔዳና በምርጫ ሳቢያ የተገደሉና የታሠሩ ሁሉ ዛሬ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ይፈጸምላቸዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የኢራን ባለሥልጣናት፣ 140 የሚሆኑ የተቃውሞ ሰልፈኞችን አከታትለውም 25o የሚሆኑት እሥረኞችን ለመልቀቅ ለተቃውሞው ወገን ፈቃደኛነታቸውን አሳይተው ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂልሪ ክሊንተንም፣ ትናንት ፣ ኢራን የፖለቲካ እሥረኞችን መፍታት «ግዴታዋ ነው» ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

►◄