1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ከ23 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን

ሐሙስ፣ ነሐሴ 21 2007
https://p.dw.com/p/1GMu2

በኢትዮጵያ ከ23 ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ጀርመን
« የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግብ በጣም እወዳለሁ። እንጀራ በዶሮ ወጥ መብላት ለምጃለሁ። ጥብስም በጣም እወዳለሁ። የዶም በየአይነቱ የማዘወትረዉና የምወደዉ ምግቤ ነበር። በኢትዮጵያ የገና፤ የፋሲካ በዓል አከባበር እጅግ ዉብ ነዉ።» ጀርመናዊትዋ
« ወደ ሐገሪ ስመለስ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዉያን ይዤ የምሄደዉ የበማኅበረሰቡ የሚታየዉን ሞቅ ያለ ቅርርብ ማኅበራዊ የአኗኗር ዘዴዉን ነዉ»
«ኢትዮጵያ ዉስጥ ስኖር 23 ዓመቴ ነዉ። ግማሽ እድሜዬን ያሳለፍኩትም እዚሁ ነዉ። አሁን ግን አዛዉንቶቹ ቤተሰቦቼ ጋር መሆን ስለምፈልግ ወደ ሀገሬ ወደ ጀርመን መመለስ እፈልጋለሁ። ወዲህም ልጆቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸዉን በጀርመን እንዲያጠናቅቁ፤ በዛዉም የጀርመንን ባህል እንዲማሩ በጀርመን ያለዉን አኗኗርም እንዲተዋወቁ እፈልጋለሁ።» ያሉን ጀርመናዊትዋ ኮንስታንሰ ፕሪል ናቸዉ፤ ኮንስታንተ ፕሪል አጠር ባለ ስማቸዉ «ኮኒ» ሲባሉ ነዉ የሚታወቁት። አማርኛ ቋንቋን የተማሩት በጀርመን በላይፕሲግ ከተማ ነዉ። በርግጥ አማርኛ ቋንቋ የየትሀገር ቋንቋ እንኳ እንደሆነ አያዉቁም ነበር ትምህርቱን ለመከታተል ዩንቨርስቲ ሲመዘገቡ። እንደ ኮኒ ወደዚህ ዩንቨርስቲ ያቀኑት የአፍሪቃ ጥናት «African Studies» ለመከታተል ነበር ። ከዚያም ቋንቋ መማር ስለነበረባቸዉ አማርኛን መማር ይፈልጋሉን ተብለዉ ሲጠየቁ፤ መልሳቸዉ አዎን ነበር። ስሞን ማን ልበል አልኳቸዉ፤ አይ አንቺ ብትይኝ እወዳለሁ ስላሉኝ በሃሳባቸዉ ተስማምቼ ቃለ-ምልልሳችን ጀመርን፤ በነገራችን ላይ በጀርመን ባህል ከ 15 ዓመት ጀምሮ ማንኛዉም ሰዉ በቅጡ የማይተዋወቅ ከሆነ በአንቱታ ነዉ ንግግር የሚለዋወጠዉ፤ የሰዉየዉ ፈቃድ ሆኖ አይ አንተ በለኝ አንቺ በለኝ ካልተባባለ በስተቀር፤ በዚህ ዝግጅታችን አማርኛ ተናጋሪዋን ጀርመናዊት በእንግድነት ይዘናል።