1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦት ችግር የለም ሲል መንግሥት ገለጸ

ረቡዕ፣ መጋቢት 5 2010

በኢትዮጵያ የነዳጅ አቅርቦቱን ለማስተጓጎል በኦሮምያ ክልላዊ መንግስት የተቃውሞ እንቅስቃሴ የሚያደርገው ቄሮ የተባለው የወጣቶች ቡድን በማህበራዊ ድህረ ገጾች ያስተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ የነዳጅ ማመላለሻ ከባድ ተሽከርካሪዎች በኮማንድ ፖስት በሚመሩ የጸጥታ ኃይላት ታጅበው መንቀሳቀስ መጀመራቸው ተገለጸ ::

https://p.dw.com/p/2uKB7
Afghanistan Iran Tankwagen Öl
ምስል AP

በመላው ሃገሪቱ ነዳጅን ለማስተጓጎል የተጠራ ዘመቻ

 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አልፎ አልፎ ነዳጅ ጭነው ከሱዳን እና ጅቡቲ የሚገቡ አሽከርካሪዎች ሥጋት እያደረባቸው በየመንገዱ መቆማቸው ጉዞዋቸውን ከማዘግየቱ በስተቀር በሃገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት እጥረትም ሆነ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጽሚ ለዶቼቨለ አስታውቀዋል :: ቄሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ ንጹሃን ዜጎች በመከላከያ ሰራዊት መገደላቸውን ተከትሎ ከትላንት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ በሃገሪቱ የነዳጅ አቅርቦትን ለማስተጓጎል ያቀደ የዘመቻ ጥሪ በተለያዩ ማህበራዊ ሚድያዎች ማስተላለፉ ይታወሳል :: የኦሮምያ ቄሮ ወጣቶች በተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገጾች እንደገለጹት ገዥው መንግስት ኢሃዲግ በሃገሪቱ የሚፈጽመውን ግድያ ጭቆና እና አፈና ለመግታት ከአድማ እና ህዝባዊ ተቃውሞ ሌላ አዲስ የትግል ሥልት መንደፋቸውን ገልጸዋል :: ከትላንት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ይዘልቃል ያሉትንም በመላው ሃገሪቱ ነዳጅን ለማስተጓጎል የተጠራ ዘመቻ ተግባራዊ ማድረጋቸውም በየመገናኛ ብዙሃኑ ሲዘገብ ቆይቷል :: ጥሪውን እየሰሙ ከቦታ ቦታ ነዳጅ ጭነው የሚጓዙ ተሽከርካሪዎች የጥቃት ኢላማ እንደሚሆኑ እና ለሚደርስባቸውም አደጋ ሃላፊነቱን እራሳቸው ይወስዳሉ ሲሉ ቄሮዎች ማስጠንቀቃቸውንም የማህበራዊ ድህረ ገጽ መረጃዎች ይጠቁማሉ :: ይህን የነዳጅ እቀባ ጥሪ ተከትሎ ኮማንድ ፖስት ምንም የሚከሰት ነገር እንደማይኖር በመግለጽ አሽከርካሪዎችን እና ባለንብረቶችን ለማረጋጋት ጥረት ቢያደርግም ነዳጅ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ግን የኢንሹራንስ ጉዳዮችን እያነሱ አሁንም ሥጋት እንዳደረባቸው ታውቋል :: የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለማርያም አልፎ አልፎ ነዳጅ ጭነው ከሱዳን እና ጅቡቲ የሚገቡ አሽከርካሪዎች ሥጋት እያደረባቸው በየመንገዱ መቆማቸው ጉዞዋቸውን ከማዘግየቱ በስተቀር በሃገሪቱ የነዳጅ አቅርቦት እጥረትም ሆነ ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ነው የገለጹልን ::

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ የሃገሪቱ የቤንዚን ፍላጎት በቀን 1.5 ሚልዮን ሊትር መሆኑን ገልጸው ይህ መጠን በገበያ ውስጥ መኖሩን እና ምንም የነዳጅ እጥረትም ሆነ ችግር እስካሁን በሃገሪቱ አለመከሰቱን ነው ያስረዱት :: በቤንዚን ማዲያዎች አካባቢ አልፎ አልፎ የሚታየው የአሽከርካሪዎች ሰልፍም ከነዳጅ አቅርቦት እጥረት የመነጨ ሳይሆን በተናፈሰው ወሬ ምክንያት ነው ሲሉ አብራርተዋል ::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ነዳጅ የሚጭኑ አሽከርካሪዎች እና ባለንብረቶች ደህንነት እና የሥራ ዋስትና ለማረጋገጥ በመሰል አደጋ ለሚጠፉ ንብረቶች ዋስትና ስለሚሰጥበት ጉዳይ ውይይት እና ንግግር መጀመሩ ይነገራል :: የኦሮምያ ቄሮዎች ከቤት ውስጥ አድማ እና ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ነዳጅ እቀባ የትግል ሥልት የተሸጋገሩት መንግሥት አስቸኳይ አዋጁን አስታኮ ባቋቋመው የኮማንድ ፖስት ወታደራዊ ዕዝ ንጹሃን ዜጎችን በግፍ መግደል እና ማሰር በመጀመሩ ምክንያት መሆኑን መግለጻቸው ታውቋል :: 

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ