1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች የቀጠለዉ ግጭት

ማክሰኞ፣ ጥር 1 2010

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ለወራት የዘለቀዉ ግጭት በመቀጠሉ ሁኔታዉ አሁንም ድረስ አሳሳቢ መሆኑ ተገለጸ። ይህ የተገለጸዉ ጉዳዩን እንዲያጣራ በተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመዉ ቡድን ዘገባውን ባቀረበበት ወቅት ነዉ። የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ የደረሰዉን ጉዳትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብም ምክር ቤቱ ወስኗል። 

https://p.dw.com/p/2qalB
Äthiopien | Parlament
ምስል DW/Y. G. Egziabher

Report about oromia and somali regions boarder conflict - MP3-Stereo

ለዘመናት ተከባብሮና ተፋቅሮ በኖረዉ የኦሮሞና የሶማሌ አጎራባች ህዝብ መካከል በተፈጠረዉ ግጭት ሳቢያ የበርካታ  ሰዎች ህይወትና ንብረት መዉደሙ ሲነገር ቆይቷል። ያም ሆኖ ግን መንግስት ግጭቱን በማስቆምና ተጎጂወችን በመደገፍ ረገድ ዘግይቷል በሚል እየተተቸ ይገኛል። ዘግይቶም ቢሆን ግን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከምክር ቤቱ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች የተዉጣጡ 13 አባላትን የያዘ አጣሪ ቡድን ወደ ስፍራዉ አቅንቶ በሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ሁኔታ መመልከቱንና መረጃ መሰብሰቡ ተገልጿል።

በፓርላማ የተዋቀረዉ ይህ አጣሪ ቡድን ከተፈናቃዮችና ከአካባቢዉ አመራሮች  በሰበሰበዉ መረጃ መሰረት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ሐሙስ ታህሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ ሪፖርት ማቅረቡን የቡድኑ አባል እና የምክር ቤቱ የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዓለሙ ገብሬ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭቱ ከነሀሴ መጨረሻ 2009 ዓ.ም.  ጀምሮ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ቢነገርም በሪፖርቱ የተካተተዉ እስከ ህዳር 2010 ዓ.ም. ድረስ ያለዉን ሁኔታ ብቻ የሚመለከት መሆኑ ተገልጿል። በዚህም የተነሳ ሪፖርቱ ዘግይቷል የሚልና በዜጎች ላይ የደረሰዉ ጉዳት ተጣርቶ ይቅረብ የሚሉ ጥያቄዎች በዉይይቱ  ወቅት የምክር ቤት አባላቱ በቁጭት ማንሳታቸዉ ተመልክቷል። ጉዳዩ ክልሎችን ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የፌደራል ስርዓቱንም ጭምር የሚፈታተን መሆኑም ተጠቅሷል። በነዋሪዎቹ ላይ የደረሰዉን ጉዳትም ቡድኑ በተጨባጭ ማየቱን የምክር ቤት አባሉ ገልጸዋል።

Äthiopien Flüchtlinge vor ethnischer Gewalt
ምስል DW/J. Jeffrey

በፓርላማ የተቋቋመዉ ይህ አጣሪ ቡድን በሁለቱም ክልሎች 16 ወረዳዎችን ተዘዋዉሮ የተመለከተ ሲሆን በእነዚህና በሌሎች ቦታዎች ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ መሆናቸዉን ምክትል ሰብሳቢዉ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ቡድኑ መረጃዉን በሚሰበስብበት ወቅትም ግጭቱ በመቀጠሉ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊያሻቅብ እንደሚችል ነዉ የተገለፀዉ። ስለሆነም ሁኔታዉ አሳሳቢና ፈጣንና ዘላቂ መፍትሄ የሚያስልገዉ በመሆኑ የዜጎችን ሞት ማስቆም  ቀዳሚ ስራ እንዲሆን ምክር ቤቱ  አፅንኦት ሰጥቶበታል ብለዋል። 

«አንደኛ ያስቀመጥነዉ የተቀመጠዉ የዉሳኔ ሀሳብ ይሄ መፈናቀሉና ግጭቱ የቆየ እንደሆነ ነዉ።በአንድ ጊዜ የተከሰተ አይደለም።የቆየ ስለሆነ እኛ «በሱፐር ቪዥን» ወቅት ባለንበት ሁኔታም እኛ ከወጣን በኋላም ያዉ መፈናቀሉ ግጭቱ እና የመሞቱ  ሁኔታ  ያለ ስለሆነ  በአስቸኳይ ግጭቱ መቆም እንዳለበትና በዜጎች ላይ የሚደርሰዉ ሞት መቆም እንዳለበት ነዉ። ቀዳሚ አድርጎ አስፈፃሚዉ መስራት እንዳለበት ነዉ ፤አንዱ የተቀመጠዉ አቅጣጫ።ሁለተኛዉ አጥፊወች  በአስቸኳይ መጠየቅ አለባቸዉ።በየትኛዉም የአመራር እርከን ደረጃ ያሉ አመራረሮችም ይሁን የፀጥታ ሀይሉ እንዲሁም በግለሰብና በቡድን  ደረጃ  ያለ አጥፊ  በአስቸኳይ ወደ ህግ ቀርበዉ መጠየቅ እንዳለባቸዉ ፣የህግ የበላይነት መከበርና ዜጎች  ተዘዋዉረዉ የመኖርና  ሀብት የማፍራት መብቶች ሊረጋገጡላቸዉ እንደሚገባ ነዉ ያስቀመጥነዉ።ስለዚህ ይህ ስራ መሰራት አለበት። »

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ምክር ቤቱ ዉሳኔ ማሳለፉን አመልክተዋል። የደረሰዉን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንዲሁም በወንጀል የተሳተፉ አመራሮችና ግለሰቦችን ጭምር በማጣራት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለምክር ቤቱ በአጭር ጊዜ ሪፖርት እንዲያቀርብ መወሰኑንም ገልጸዋል።

ለወራት በዘለቀዉ የሁለቱ ክልሎች ግጭት በርካቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል የዳረገ ነው። የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በቅርቡ ባወጣዉ መረጃ መሰረትም14 ሺህ የሚጠጉ ህጻናት ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ተለያይተዋል። ሰማንያ አራት ሺህ የሚደርሱት ህጻናት ደግሞ ከትምህርት ገበታ መራቃቸዉን አመልክቷል።

ፀሀይ ጫኔ

አርያም ተክሌ