1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ 10 ሽህ ታራሚዎች ተፈቱ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 26 2009

በኦሮሚያ ለ10 ሺህ የህግ ታራሚወች ይቅርታ መደረጉን የክልሉ መንግስት ዛሬ አስታወቀ ። በፓለቲካና ከባድ በሚባሉ ሌሎች ወንጀሎች የታሰሩ ሰወችን ይቅርታዉ አያካትትም ተብሏል።

https://p.dw.com/p/2VGzO
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Englisch

Oromia regional state released 10 thousand prisoners - MP3-Stereo

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ፍርድ ቤትና ከፌደራል በተሰጠዉ ዉክልና ተፈርዶባቸዉ በእርምት ላይ የሚገኙ 10 ሺህ የህግ ታራሚወች  በዛሬዉ እለት በይቅርታ መለቀቃቸዉን  በምክትል ቢሮ ሀላፊ ማእረግ የክልሉ ፍትህ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ መለሰ አባይነህ ተናግረዋል። ታራሚወቹ  በክልሉ ፕሬዝዳንት በኩል ይቅርታ የተደረገላቸዉ ሲሆን፤በክልሉ ህገመንግስት አንቀፅ  57 ድንጋጌ መሰረት የተለቀቁ ናቸዉ ተብሏል። መጭዉን የገና በአል ምክንያት በማድረግ ይቅርታዉ የተከናወነ መሆኑንም የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዉ ገልጸዋል።

እንደ አቶ መለሰ ገለጻ ታራሚወቹ በቆይታቸዉ መጸጸታቸዉና በጥሩ ሁኔታ መለወጣቸዉ በማረሚያ ቤቱ የታመነባቸዉና ወደ ማህበረሰቡ ቢቀላቀሉ ለዉጥ ሊያመጡ ይችላሉ የተባሉ ናቸዉ።

የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዉ  13 አመትና ከዚያ በላይ የታሰሩ፣ ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዉ አንድ ሶስተኛዉን ያጠናቀቁ ታራሚወችን በይቅርታዉ የተካተቱ ሲሆን፤የሀገሪቱን ህገ መንግስት አንቀጽ 28 ተላልፈዉ ወንጀል የፈጸሙና ሌሎች ከባድ በሚባሉ ወንጀሎች ፈጽመዋል ተብለዉ የታሰሩ ታራሚወችን ይቅርታዉ እንደማያጠቃልል አቶ መለሰ አብራርተዋል።                         

ጉዳዩን አስመልክቶ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ የሚከተለዉን አስተያየት ሰጥተዋል። የሞት ፍርድ የተፈረደባቸዉ፣ከዚህ በፊት በይቅርታ ተለቀዉ ድጋሚ ወንጀል ፈጽመዉ የታሰሩ ፣በህገ ወጥ የሰወች ዝዉዉርና በሙስና ወንጀል የታሰሩ ታራሚዎችም በይቅርታው አለመካተታቸዉን  ከክልሉ መንግስት የተገኘዉ መረጃ ያስረዳል።

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ