1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦጋዴን ያንዣበበዉ የምግብ እጥረትና የእርዳታ አቅርቦት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 2 2000

---ኦቻ እንደሚለዉ ከጥቅምት እስከ ታሕሳስ መጣል የነበረበት የመፀዉ ዝናብ ባለመጣሉ በተለይ የፊቅ እና የዋርዴር መስተዳድር ሕዝብን ለሌላ ተጨማሪ ችግር መጋለጡ አይቀርም።

https://p.dw.com/p/E0Wy
ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያምስል AP GraphicsBank/DW

በምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዛት በኦጋዴን ዘንድሮ በቂ ዝናብ አለመጣሉ በአካባቢዉ የተከሰተዉን የምግብ እጥረት እንደሚያባብሰዉ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት አስታወቀ።OCHA በሚል ምሕፃረ-ቃል የሚጠራዉ የተባበሩት መንግሥታት የሠብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ እንደሚለዉ ግጭት ባወከዉ በሶማሌ ብሔራዊ መስተዳድር ከጥቅምት እስከ ታሕሳስ መጣል የነበረበት ዝናብ ዘንድሮ ባለመጣሉ ወትሮም የተከሰተዉን የምግብ እጥረት ያባብሰዋል።የተለያዩ የርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት በበኩላቸዉ ለምግብ እጦት የተጋለጠዉን ሕዝብ ለመርዳት ዝግጁ ናቸዉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጦር እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አዉጪ ግንባር (ኦብነግ) ካለፈዉ አመት አጋማሽ ጀምሮ የሚያደርጉት ግጭት በልማዱ ኦጋዴን የሚባለዉን አካባቢ ሕዝብ ለስደትና ችግር አጋልጦ ነዉ-የከረመዉ።

በቅርቡ ሁለት ባልደረቦቹ የተባበረሩበት ሴቭ ዘ-ችልድረን የተባለዉ ግብረሰናይ ድርጅት የአለም አቀፍ የርዳታ ዘመቻ ሐላፊ ኬይ ኮልዌል እንደሚሉት ኦጋዴን ዉስጥ ስድስት መቶ ሺሕ ሕዝብ አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገዋል።

«ኦጋዴን ዉስጥ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ ሁኔታ ነዉ እያየን ነዉ።እኛ እንደምንገምተዉ በዚያ አካባቢ የሚኖር 6 መቶ ሺሕ ሕዝብ በሚቀጥሉት ወራት የምግብ እርዳታ ወይም የጤና አገልግሎት ድጋፍ ያስፈልገዋል።«

የመንግሥት ጦርንና የአማፂዎችን ግጭት ፍራቻና በኢትዮጵያ መንግሥት ትዕዛዝ ከአካባቢዉ ወጥተዉ ከነበሩት ግብረ ሠናይ ድርጅቶች አስራ-ዘጠኝ ያሕሉ ወደ አካባቢዉ እንዲመለሱ የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ መፍቀዱ ለችግረኛዉ ሕዝብ ተስፋ፣ ለእርዳታ አቅራቢዎቹ ደግሞ እፎይታ አይነት ነዉ የሆነዉ።

የተባበበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠብአዊ ርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ እንዳስታወቀዉ በቅርቡ እርዳታ ማቀበል ከተጀመረ ወዲሕ አስራ-አንድ ሺሕ ቶን ምግብ ወደ አካባቢዉ ተልኳል። ሌላ አስራ ሁለት ሺሕ ቶን ደግሞ በቅርቡ ይላካል።የተላከና የሚላከዉ እርዳታ የሴቭ ዘችልድረን ሐላፊ እንደሚሉት የችግረኛዉን ሕዝብ ችግር ለማቃለል ይረዳል።ግን በተለይ ለሕፃናቱ የእስካሁኑ እርዳታ በቂ አይደለም።

«በግልፅ እንደሚታወቀዉ ከሴቭ ዘ ችልድረን አኳያ፣ በተለይ በጣም የሚያሳስበን እርዳታ ከሚፈልገዉ 6 መቶ ሺሕ ሕዝብ 3 መቶ ሺዎቹ ሕፃናት መሆናቸዉ ነዉ።ሕፃናቱ ካሁን ጀምሮ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት በተገቢዉ ሁኔታ ካልተመገቡ ቀሪዉ ሕይወታቸዉ ለአደጋ ይጋለጣል።»

ዩናይትድ ስቴትስ ለኦጋዴን ሕዝብ መርጃ ሃያ-አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ እንደምትልክ አስታዉቃለች።የአሜሪካዉ የርዳታ ድርጅት USAID እንዳስታወቀዉ ምግቡ ለተረጂዉ የሚከፋፈለዉ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድርጅት በኩል ነዉ።ሴቭ ዘ-ችልድረን ሐላፊዉ እንዳሉት ችግረኛዉን ሕዝብ በተለይ ሕፃናቱን ለመርዳት መሰናዶዉን አጠናቋል።


«እኛ፣- የኢትዮጵያ መንግሥት በፈቀደዉ መሠረት እርዳታ ለመስጠት በሚደረገዉ ጥረት ለመሳተፍ ዝግጁ ነን። ኦጋዴን ዉስጥ እንዲሰሩ ከተፈቀደላቸዉ አሥራ-ዘጠኝ ድርጅቶች የኛ አንዱ ነዉ።የጤና አገልግሎት በርገጥኝነት እንሠጣለን።አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ደግሞ በዚያ አካባቢ ለተጎዱ ሕፃናት ተጨማሪ አልሚ ምግብ እንሰጣለን።ሥለዚሕ እኛ በተለይ በሚቀጥሉት ወራት ለአደጋ የተጋለጡ የኦጋዴን ሕፃናትን ለመርዳት ምግብ በማከፋፈሉ ጥሩ እገዛ እናደርግ ይሆናል።እስካሁን ግን ምግብ ማሰራጨቱን አልጀመርንም።ከኢትዮጵያ መንግሥት የመጨረሻዉን ፍቃድ እየጠበቅን ነዉ።»

ግጭት የጎዳዉን ሕዝብ ለመርዳት ጥረቱ-ሲጠናከር ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ፣ ፍቃዱ ሲጠበቅ፣ የዝናብ እጥረት ተጨማሪ ሕዝብ ለረሐብ ያጋልጣል መባሉ ነዉ-የአዲሱ ሥጋት ምንጭ።ኦቻ እንደሚለዉ ከጥቅምት እስከ ታሕሳስ መጣል የነበረበት የመፀዉ ዝናብ ባለመጣሉ በተለይ የፊቅ እና የዋርዴር መስተዳድር ሕዝብን ለሌላ ተጨማሪ ችግር መጋለጡ አይቀርም።