1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወልዲያ በተቀሰቀሰ ግጭት በሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ቅዳሜ፣ ጥር 12 2010

በአማራ ክልል ወልዲያ ከተማ የቃና ዘገሊላ በዓልን በማክበር ላይ በነበሩ ምዕመናን እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካቶች መጉዳታቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ በግጭቱ በርካቶች መቁሰላቸውን እና የሞቱ ሰዎችም እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/2rEA4
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የዓይን እማኝ በግጭቱ “አንድ ሰው ሞቶ፤ ብዙ ሰዎች መቁሰላቸውን” ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ እርሳቸው ሁለት የቆሰሉ ሰዎችን መመልከታቸውን እና “አንደኛው ከጀርባው ደም ይፈስሰው እንደነበር” እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በርካታ ቁስለኞች ወደ ወልዲያ ጠቅላላ ሆስፒታል መወሰዳቸውን መስማታቸውንም አካፍለዋል፡፡  

ሌላኛው የከተማይቱ ነዋሪ የቆሰሉ ሰዎችን ቁጥር በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም እርሳቸው ባሉበት ጎንደር በር አካባቢ ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል፡፡ በየአቅጣጫው ተኩስ ይሰማ እንደነበር የተናገሩት እኚሁ ነዋሪ በግጭቱ የሞቱ ሰዎች እንዳሉ መስማታቸውን ነገር ግን ቁጥራቸውን ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡ ሶስተኛ የከተማይቱ ነዋሪም በግጭቱ ሰዎች መሞታቸውን ለዶይቼ ቬለ ባደረሱት መልዕክት ጠቁመዋል፡፡ 

የዛሬው የወልዲያ ግጭት የተቀሰቀሰው በዓሉን በጭፈራ በማክበር ላይ የነበሩ ወጣቶች በፖሊሶች መከልከላቸውን ተከትሎ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ “ከጨፋሪዎቹ እና ከፖሊስ አካላት ነው ችግሩ የተነሳው፡፡ ጸቡ የተነሳው መጨፈር የለባችሁም እያሏቸው ስለነበር ወጣቱ ደግሞ እንጨፍራለን ብለው በመነሳታቸው ነው” ብለዋል አንደኛው ነዋሪ፡፡ ወጣቶች በፖሊሶች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ መመልከታቸውን እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ፡፡ 

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል አካባቢ መሰማት የጀመረው የተኩስ ድምጽ እስከ ምሽት 12 ሰዓት ተኩል ድረስ መዘልቁን የከተማይቱ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ አባላት እንደዚሁም የመከላከያ ሰራዊት አባላት በከተማይቱ እንደተሰማሩም አስረድተዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎቹ “ሰላማዊ ሰዎችን ጭምር ይደብድቡ እንደነበር” የተናገሩት የዓይን እማኝ “እኔም ከድብደባው ተደብቄ ነው ያመለጥኩት” ብለዋል፡፡ በከተማይቱ ምሽቱን ውጥረት እንደሰፈነ እና ሰዎች እንደልብ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡  

ግጭቱን አስመልክቶ ዶይቼ ቬለ የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ በቀለን ማምሻውን ጠይቆ ነበር፡፡ አቶ ጸጋዬ ጉዳዩን ገና በማጣራት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
    
ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ