1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወባና በፖሊዮ አንፃር የሚደረገው ትግል

ሐሙስ፣ ኅዳር 23 1997

አሁን በመገናኛ-ብዙሃን በሰፊው እንደተዘገበው፥ በወባ ወረርሽኝ አንፃር የክትባት መድኃኒት ለመከሰት ሊቃውንት ያካሄዱት የ፳ ዓመታት ምርምር አሁን ጉልሁን ተሥፋ የፈነጠቀ ሆኖ ነው የሚታየው። በዚህም መሠረት፥ በአፍሪቃዊቱ ሀገር ሞዛምቢክ አዲሱ የክትባት መድኃኒት ከ፪ሺ በሚበልጡ ሕፃናት ላይ ተፈትሾ፣ በበሽታው የመያዝን አደጋ በ፴ በመቶ ያህል ለመቀነስ እንዳስቻለ ተረጋግጧል።

https://p.dw.com/p/E0fA

እንግዲህ፣ ሊቃውንቱ እንደሚያስገነዝቡት፥ ፍተሻው ወደፊትም የተሳካውን ውጤት ካስገኘ፣ ያው ፀረወባ ክትባት-መድኃኒት ካሁን ወዲያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ለገበያው አቅርቦት ዝግጁ እንደሚሆን ነው የሚታሰበው--ይኸውም ቢፈጥን እጎአ በ፪ሺ፲ ነው ሊቀርብ የሚችለው። ይህም ሆኖ፣ ተመራማሪዎቹ ሊቃውንት አሁን ጉልሁን ተሥፋ ነው የፈነጠቁት። ይኸው የክትባት ተሥፋ በተለይ ከሰሐራ በስተደቡብ ያለውን ያፍሪቃውን አካባቢ ነው የሚመለከተው። በዓለም ውስጥ ከጠቅላላው የወባ ሕሙማን መካከል ፺ በመቶ ያህሉ የሚገኙት በሰሐራ ደቡቡ ያፍሪቃ ከፊል እንደሆን ይታወቃል።

“የሰው ልጅ በወባው ወረርሽኝ አንፃር ለሚያካሂደው የዘመናት ትግል ዛሬ ትልቅ የእመርታ ምዕራፍ ነው የተከፈተው፣ ይህ የክትባት መድኃኒት በሕዝብ ጤና ጥበቃ አኳያ ከፍተኛ ትርጓሜ ነው የሚኖረው” ይላል የተመራማሪዎቹ ሊቃውንት መግለጫ። ወባን ለመታገል የሚያስችለው የክትባት ሥራይ እንዲከሰት የተካሄደው ምርምር ሊጠናከርና የመጀመሪያውን ፍሬ ለማስገኘው የበቃው የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ ጥሪት በማስተባበር መሆኑን የሊቃውንቱ መግለጫ ያመለክታል።

እንደሚታወቀው፥ የወባው ወረርሽኝ የሚከሰተው፥ አኖፍሊስ የተባለችው ትንኝ ሰውነትን ነክሳ ደምን በምትመጥበት ጊዜ ነው። የወባው ትንኝ ሰውነት ውስጥ የሚያሰራጨው ተባይ ወደ ጉበት ይተላለፍና እዚያው እየተባዛ ቀዩን የደም ሕዋስ ይደመስሰዋል፣ ከዚያ የሚከተለው ንዳድ ወይም የትኩሳት ግለት ነው፤ ሁኔታው ከባድ በሚሆንበት ጊዜ ወደ ጭንቅላት የሚተላለፈውም ደም ሂደት የሚታወክ ይሆናል።

በዓለም ውስጥ በወባው ወረርሽኝ እየተያዙ በያመቱ ሕይወታቸውን የሚያጡት ሰዎች አሃዝ በአንድ ሚሊዮንና በሦሥት ሚሊዮን መካከል ነው የሚገመተው፤ በዚሁ ግምት መሠረት፥ በዓለም ውስጥ በያመቱ ከ፫፻ እስከ ፭፻ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ናቸው በወባው በሽታ የሚነደፉት።


የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ሰሞኑን ዠኔቭ ውስጥ የሰጠው መግለጫ እንደሚያመለክተው፥ ባለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት ውስጥ በብዙ የክትባት መድኃኒቶች ላይ ምርምር ቢካሄድም፣ ያሁኑን ያህል ጉልህ ተሥፋ የሚሰጥ የምርምር ውጤት የለም። ሕፃናት በወባው በሽታ እንዳይነደፉ ለማድረግ እንደሚቻል መጀመሪያው አነቃቂ ምልክት የታየው በአዲሱ የክትባት መድኃኒት አማካይነት ነው። ግን፣ ይኸው ፀረወባ ክትባት-መድኃኒት ለሚሊዮኖቹ ሕፃናት ደኅንነት ሊበጅ ከመብቃቱ በፊት ገና ብዙ ምርምር መካሄድ እንዳለበት የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ዘገባ ያስገነዝባል። ድርጅቱ እንደሚለው፣ የወባው ወረርሽኝ አፍሪቃ ውስጥ ከአምስት ዓመታት ዕድሜ በታች የሆኑ ሕፃናት ለሚደርስባቸው የሞት አደጋ ተጠያቂ ከሚሆኑት ከዋንኞቹ በሽታዎች አንዱ ነው።

እንግዲህ፣ ምርምሩ ወደ ብስለት ደረጃ ደርሶ ተሥፋው እውን ከሆነ፣ ወባን በመሰለ አንድ ጠንቀኛ ተባይ አንፃር ሰብዓዊ ክትባት ሲኖር መጀመሪያው ጊዜ ይሆናል። የፈንጣጣን ወረርሽኝ ለመቅረፍ ያስቻለው ዓይነቱ ክትባት ተሳክቶ ወባን ለመደምሰስ ግን፣ ገና ረዘም ያለ ጊዜ እንደሚፈጅ ነው ተመራማሪዎቹ ሊቃውንት የሚያስገነዝቡት። የክትባቱ መድኃኒት አፍሪቃ ውስጥ በሕፃናት ላይ ፍቱንነት ይኖረው እንደሆን ገና ብዙ ጥናት መካሄድ አለበት። ሊቃውንቱ እንደሚሉት፣ ወባን ሙሉ በሙሉ ለመከላከል አንድ ቅንጣት መንገድ ሊኖር አይችልም፥ የክትባት፣ የሥራይ፣ የመረብ ወዘተ ቅይጥ ነው መደራጀት ያለበት።

አፍሪቃ ውስጥ የወባው ወረርሽኝ እንደገና ስለሚስፋፋበት ዝንባሌ የተባ መ ድ ተመራማሪዎች አሁን ኢትዮጵያንም ነው የሚያስጠነቅቁት። በዚሁ ማስጠንቀቂያ መሠረት፣ ይኸው የወባ ወረርሽኝ በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ስድስት ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ የሚያዳርስ እንደሚሆን ነው የሚያሠጋው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለወባ መከላከያ የሚበጀውን መድኃኒት ለማቅረቢያና የጤና ጥበቃ ረዳቶችን ለማሠልጠኛ አሁን አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሆኖ ነው የሚታየው። ይኸው ገንዘብ ለጋሾቹ መንግሥታት እስካሁን ለዚያው በሽታ መከላከያ ዝግጁ ያደረጉት አራት ሚሊዮን ዶላር መጨመሪያ እንደሚሆን ተገልጿል።

እንደሚታወቀው፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛው የወባ መተላለፊያ ወቅት ከመስከረም እስከ ታህሣሥ ያለው ጊዜ ነው። ያው የወባው በሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ በያመቱ ከ፩፻፲ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን እንደሚበክል ነው የሚገመተው። የበሽታው ተሸካሚ በብዙ ፀረወባ መድኃኒቶች አንፃር የማይበገር እየሆነ ከመገኘቱ የተነሳ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በበሽታው የሚያዙት ሰዎች አሃዝ ጭራሹን የጨመረ መሆኑን የዓለሙ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል። አሁን በይፋ እንደተገለፀው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን የተሠራበት የወባ በሽታ ማከሚያው መድኃኒት እስከ ፷፬ በመቶ ብቻ ነበር የፈውስ ዕድል የሚሰጠው፤ ግን ዘንድሮ አገልግሎት የጀመረው ውዱ ቅይጥ ፀረወባ መድኃኒት ፺፱ በመቶ የፈውስ ዕድል የሚያስገኝ እንደሚሆን ነው ተሥፋ የተጣለበት።


ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ከወባ እና ከኤድስ ጎን የዘመቻ ትኩረት የተደረገበት ሌላው የትግል መስክ በዓለምአቀፍ መጠሪያው ፖሊዮ ተብሎ የሚታወቀውን የልጅነት ልምሻ የሚመለከት ነው። አካልን የሚያሽመደምደው በሽታ ከኢትዮጵያ ገጽ ሊቀረፍ ይበቃ ዘንድ፣ ሀገሪቱ ከቅርብ ጊዜ በፊት ለትግሉ ማጠናከሪያ የሚሆን ፲፭ ሚሊዮን ዶላር ርዳታ እንዲቀርብላት ማሳሰቧ የሚታወስ ነው። የተባ መ ጤና ጥበቃ ድርጅት ባቀረበው የፀረፖሊዮ ዘመቻ መርሐግብር ሥር ኢትዮጵያ በሽታውን እጎአ እስከ ፪ሺ፭ ድረሳ ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ በ፲፱፻፺፭ ዓ.ም. ፰፻፵፭ሺ ሕፃናትን የሚያዳርስ የክትባት ዘመቻ ነበር ያንቀሳቀሰችው። በዘመቻው የመጨረሻ ደረጃ ላይ፣ ከአምስት ዓመታት ዕድሜ በታች የሆኑትና ከ፲፬ ሚሊዮን የሚበልጡት ሕፃናት ከበሽታው ነፃ እንደሚሆኑ ነው የተገመተው። ይኸው በሽታ በተለይ ከሚያጠቃቸው ሌሎቹ ሀገሮች መካከል ሕንድ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታን እና ግብጽም እንደሚገኙባቸው የዓለሙ ጤና ጥበቃ ድርጅት መግለጫ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ያንኑ ፀረፖሊዮ ዘመቻ በማጠናከር ዘንድሮም ፯፻፶ሺ ሕፃናትን ለመክተብ መነሳሳቷን ሰሞኑን በይፋ ነው ያስታወቀችው። በመግለጫው መሠረት፣ አሁን ለዚሁ ፀረፖሊዮ ዘመቻ የሚንቀሳቀሱት አእላፉ በጎፈቃደኞች በ፳፪ የክትባት ማዕከላት ከቤት ወደቤት እየተዘዋወሩ የክትባቱን መድኃኒት ከአምስት ዓመታት ዕድሜ በታች ለሆኑት ሕፃናት ያዳርሳሉ። ይኸው የዘንድሮው ፀረፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በአዲስ አበባ ዙሪያ ፪፻፶ ኪሎሜትር የሚደርሰውን አካባቢ እንደሚሸፍን ታውቋል። የሀገሪቱ ጤናጥበቃ መሥሪያቤት በሚሰጠው መረጃ መሠረት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት በሽታው አልተከሰተም።

በተባ መ ግምት መሠረት፣ አፍሪቃ ውስጥ ከ፮፻፶ የሚበልጡ ሕፃናት ናቸው ዘንድሮ ብቻ በአሽመድማጁ በሽታ የተያዙት፤ በዚህ አኳኋን ከጠቅላላው የዓለም ፖሊዮ-ሕሙማን የአፍሪቃው ድርሻ ከ፹፭ በመቶ ይበልጣል። በ፳፫ ያፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ከ፹ ሚሊዮን የሚበልጡ ሕፃናትን በክትባቱ ዘመቻ አማካይነት ከፖሊዮ አደጋ ነፃ ለማድረግ ዘንድሮ ሠፊ ዘመቻ መንቀሳቀሱን የዓለሙ ድርጅት አስታውቋል። ታጋዮቹ ፖሊዮን ዘንድሮ ወይም በመጭው ዓመት ከአፍሪቃ ገጽ ለመደምሰስ ነበር ተሥፋ ያደረጉት፤ ግን ይኸው የልጅነት ልምሻ እንደተወገደላቸው ሲታሰቡ በነበሩ ፲፪ ሀገሮችም ውስጥ በሽታው ባለፉት ፲፰ ወራት እየተስፋፋ መገኘቱን የዓለሙ ጤና ጥበቃ ድርጅት መግለጫ አሁን ይፋ አድርጎታል።

እንግዲህ፣ በጠንቀኞቹ በሽታዎች አንፃር በየግንባሩ የሚንቀሳቀሰው ዘመቻ ለሕዝብ ጤንነት መድኅን እንደሚሆንና የሠራተኛውንም ኃይል ያምራችነት ኣቅም ለማደንደን እንደሚያስችል ጥርጥር የለውም። ለዚሁ ዓላማ የሚመደበውም ወጭ እንደ አትራፊ ውዒሎተንዋይ ነው መታየት ያለበት።