1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዉኃ የሚያድገዉን ተክል ለዉኃ ማጣሪያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2009

በመላዉ ዓለም 750 ሚሊየን የሚሆን ህዝብ ንፁሕ ዉኃ የማግኘት ዕድል እንደሌለዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2014 ዓ,ም በተባበሩት መንግሥታት የዓለም የጤና ድርጅት አማካኝነት የተሠራ አንድ ጥናት ያመለክታል። በተቅማጥ፣ በቂ ዉኃ ባለመጠጣት እንዲሁም የእጅን ንፅሕና በአግባቡ ባለመጠበቅ ምክንያት ደግሞ በዓመት የ842 ሺህ ሰዎች ሕይወት ይቀጠፋል።

https://p.dw.com/p/2VD5q
Wasserreinigung Pflanze aus Süd-Äthiopien Omo Zone
ምስል DW

ዉኃ ማጣሪያ ተክል

  

ንፁሕ መስሎ በሚታይ ዉኃ ዉስጥ ጀርሞችን ጨምሮ ለጤና እንከን የሆነ የተለያየ ነገር ሊገኝበት ስለሚችል ለመጠጥ ከመዋሉ በፊት ማጣራት የሚቻልበት መንገድ ቢኖር ይመከራል።  መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ከሎሚ እና የሙዝ ልጣጭ አንስቶ የተለያዩ ተክሎች እንደየአቅማቸዉ ዉኃን ለማጣራት ይረዳሉ። ከሳምንታት በፊት ከኢትዮጵያ ከወደ ደቡብ ኦሞ ዞን የደረሰን አንድ የዝግጅታችን ተከታታይ መልዕክት አንድ ተክል በአካባቢዉ ኅብረተሰብ ዘንድ ዉኃ ለማጣራት እንደሚዉል ያስረዳል። ለዉኃ ማጣሪያነት የሚጠቅመዉን ተክል ፎቶ ጭምር ነዉ አድማጫችን የላኩልን። እናመሰግናቸዋለን። የአፍሪቃ የዉኃ ማማ ተብላ በምትታወቀዉ ኢትዮጵያ የአባይን ልጅ ዉኃ ጠማት እንዲሉ የንፁሕ ዉኃ አቅርቦቱ ከሰሃራ በስተደቡብ ከሚገኙት ሃገራት ዝቅተኛዉ መሆኑን ነዉ መረጃዎች የሚያመለክቱት። ምንም እንኳን በዉጭ የገንዘብ ድጋፍ የዉኃና የንፅሕና መጠበቂያ ስልቱ አቅርቦት ቀድሞ ከነበረዉ እየተሻሻለ ቢመጣም በሚፈለገዉ መጠን ለህዝቡ ተዳርሷል ወይ የሚለዉ ዛሬም ጥያቄ ነ።

 ኢትዮጵያ 12 ተፋሳሽ ወንዞች እንዳሏት፤  በዓመትም 122 ቢሊየን ክዩቢክ ሜትር ዉኃ ከዝናብ እንደምታገኝ፤ እንዲሁም ከ2,6 እስከ 6,5 ቢሊየን ክዩበክ ሜትር የከርሰ ምድር ዉኃ እንዳላት ዊኪፔዲያ ላይ ሰፍሯል። ዊኪፔዲያ እንደሚለዉ ከሆነም በግለሰብ ደረጃ አንድ ሰዉ በዓመት በአማካኝ 1,575 ክዩቢክ ሜትር ዉኃ ይደርሰዋል። ይህ መጠንም ቀላል አይደለም። ነገር ግን በተለያዩ ጊዜያዊና ዘላቂ አጋጣሚዎች ምክንያት ዝናብ በመስተጓጎሉ የዉኃ እጥረት ከመከሰቱ በተጨማሪ በሚፈለግበት ስፍራም እንደልብ እንደማይገኝም ያትታል። በዚህም ምክንያት ሀገሪቱ ካላት እምቅ የዉኃ ሃብት ወደ 3 በመቶዉን ብቻ ነዉ ጥቅም ላይ መዋል የተቻለዉ።

Omo Dam Projekt in Äthiopien
ምስል Survival International

የዉኃ እጥረት በመኖሩም ችግር ብልሃትን ይወልዳል እንዲሉ ኅብረተሰቡ ተፈጥሮን እየመረመረ የራሱን ንፁሕ ዉኃ የማግኛ ዘዴ እንዲፈልግ ግድ እንዳለዉ የደቡብ ኦሞዉ ተሞክሮ ያመለክታል። በአካባቢዉ አንድ ተክል አለ፤ ጉልፍ ይባላል።

ይህን መረጃ ያካፈሉን አድማጭ እንደሚሉት አርብቶ አደሩ ድንበር ተሻግሮ ወደ ኬንያ የሚገባዉን የኦሞን ወንዝ ተከትሎ የሚኖር በመሆኑ ዋና የዉኃ ምንጩ የኦሞ ወንዝ ነዉ። እናም ዉኃ ሲፈልግ ከኦሞ እየጨለፈ የጉልፍ ተክልን እየነቀለ ሥሩን ተጠቅሞ የደፈረሰዉን ዉኃ ጭቃዉን ከንፁሑ ይለያል። ይህ የየዕለት ተግባር እንደመሆኑ መቼም ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም። ኅብረተሰቡ በሰፊዉ የሚገኘዉን ይህን ተክል እንደልቡ እንደሚጠቀምበት ነዉ ለመረዳት የተቻለዉ። ዋተር ዳት ኦርግ «ቀዉስ» ስላለዉ የኢትዮጵያ የዉኃ ችግር እንደጻፈዉ በተለይ በገጠር የሀገሪቱ ክፍል ሴቶች እና ሕፃናት ዉኃ ለመቅዳት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ይጓዛሉ። አብዛኞቹም እንስሳት ከሚጠጡባቸዉ ኩሬዎች ሌሎቹ ደግሞ ንፅሕናቸዉ ካልተጠበቀ ቅርብ ከሆኑ ጉድጓዶች ዉኃዉን እንደሚያገኙም ያብራራል። እንደ ጉልፍ ያሉት ተክሎች ዉኃን ከጭቃ መለየት መርዳታቸዉ አንድ ነገር በመሆኑ በተክል ምርምሩ ዘርፍ ስለዚህ ነገር ይታወቅ እንደሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ጥናት እና ምርምር ዘርፍ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በመሥራት ላይ የሚገኙትን ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉን ጠየቅናቸዉ።

ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደገለፁት ደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘዉ እና ኅብረተሰቡ ለዉኃ ማጣሪያነት የሚጠቀምበት ጉልፌን ጨምሮ አራት ለዉኃ ማጣሪያነት የሚዉሉ ተክሎች መኖራቸዉን ሳይንሳዊ ምርምሩም አረጋግጧል።

ዉኃን ከማጣራት አልፈዉ በዉስጡ የሚገኙ የጤና ጠንቆችን ማጥፋት የሚችሉ የተለያዩ ፍራፍሬዎች እና ተክሎች መኖራቸዉን አንዳንድ ጽሑፎች ይጠቁማሉ። በምሳሌነትም የሎሚ እና የሙዝ ልጣጭ፣ የሾርባ ቅጠል የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ለመሆኑ በምርምር ደረጃ ይህን የሚደግፍ ግኝት ይኖር ይሆን? ያልናቸዉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ እነዚህ ዉኃ ለማጣራት የሚረዱ ተክሎች ቆሻሻን ከመለየት በዘለለ ስላላቸዉ ጀርምን የማጥፋትም ሆነ መርዛማነት የተደረጉ ጥናቶች እንዳላዩ ገልጸዉልናል።

Omo Dam Projekt in Äthiopien
ምስል Survival International

በመላዉ ዓለም ከዘጠኝ ሰዎች አንዱ ንፁሕ ዉኃ የማግኘት ዕድል የለዉም። በየቀኑም የ2,300፤  ሰዎች ሕይወት ንፁሕ ዉኃ ባለማግኘት እና የእጅን ንፅሕና በተገቢዉ መንገድ ባለመጠበቅ ያልፋል።  ኢትዮጵያ ዉስጥ በአማራ እና በትግራይ ክልል ንፁሕ ዉኃን ለማዳረሱ ፕሮጀክት እንዳለዉ የሚገልጸዉ ዋተር ዳት ኦርግ፤ የዉኃ እና የንፅሕና መጠበቂያ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል። እንደ ድርጅቱ ከሕዝቡ ግማሽ ያህሉ ባልጎለበተ የዉኃ አቅርቦት የሚገለገል ሲሆን፤ የንፅሕና መጠበቂያ ስልት ተጠቃሚ የሆነዉ ወገንም 21 በመቶዉ ብቻ  ነዉ። USAID በበኩሉ ኢትዮጵያ ለ2015ዓ,ም በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር ነዉ የታቀደዉን የአምዓቱን የልማት ግብ ንፁሕ ዉኃን ለህዝቡ በማዳረስ ረገድ ማሳካቷን ይገልጻል። በዚሁ የዘመን አቆጣጠር 1990 ዓ,ም ጀምሮ ከነበረዉ ጋር ሲነፃፀርም 57 በመቶ የሚሆነዉ ህዝብ የንፁሕ የመጠጥ ዉኃ ማግኘት ችሏል ይላል።  እንዲያም ሆኖ የተሻሻለ የንፅሕና መጠበቂያ ስልት ተጠቃሚዉ ቁጥር አሁንምከ 29 በመቶ እንዳልዘለለ የጠቆመዉ ይህ ድርጅት አሁንም የመጠጥ ዉኃ፣ የንፅሕና መጠበቂያ የማዳረሱ ጉዳይ ከፍተኛ ጥያቄ እንደሆነ ነዉ ያመለከተዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ