1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለማችን የወጣት ሥራ አጥነት

ዓርብ፣ ሰኔ 21 2005

በተለያዩ የዓለማች ክፍሎች የወጣት ሥራ አጥነት ተስፋፍቷል። ምሁራን ይህ ብጥብጥ ሊያስነሳ ይችላል ሲሉ ከወዲሁ ያሳስባሉ። እንዲያም ሆኖ ለችግሩ አጠቃላይ መፍትሄ ይሆናል የሚሉት የላቸውም። ይልቁንም እያንዳንዱ ሀገር ችግሩን የሚወጣበት መንገድ ቢፈልግ ያሻዋል ባይናቸዉ።

https://p.dw.com/p/18xOF
People wait in a queue to enter a government-run employment office in Madrid April 25, 2013. Spain's unemployment rate rose to a new record of 27.2 percent in the first quarter of this year, with 6.2 million people out of work, data from the National Statistics Institute showed on Thursday. REUTERS/Sergio Perez (SPAIN - Tags: POLITICS BUSINESS EMPLOYMENT)
ምስል REUTERS

ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናቸው። ይሁንና በበርካታ ሃገሮች ወጣቱ ሥራ አጥቶ ሲባክን ይስተዋላል። እንደ ዓለም ዓቀፍ የሥራ ድርጅት በምህፃሩ ILO መዘርዝር ከሆነ በአሁን ሰዓት 73,4 ሚሊዮን ወንድ እና ሴት ወጣቶች ሥራ አጥ ተብለው ተመዝግበዋል። ይህም ቁጥር ቀን በቀን እየጨመረ ነው።
በአውሮጳ ሥራ አጥነት በሰፊው የሚስተዋልባቸው ሃገራት ስፓኝ እና ፖርቹጋል ናቸው። በነዚህ ሃገራት የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ከ50 ከመቶ ይበልጣል። ማን ቆጥሯቸው ነው እንጂ በአፍሪቃ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ፣ በእስያ እና ላቲን አሜሪካም የሥራ አጡ ቁጥሩ ከዚህ አይተናነስም። እያንዳንዱ አገር እንደ መፍትሄ የሚያነሳውም ከየራሱ አገር እና ከችግሩ መንስኤ የተያያዘ ነዉ። ማሲሚሊያኖ ማሸሪኒ ደብሊን በሚገኘው የአውሮጳ የአኗኗር እና የሥራ ሁኔታ ማሻሻያ ተቋም ተመራማሪ ናቸው። የሥራ አጥነትን ችግር በስጋት ይመለከቱታል። «ወጣቶች ለረጅም ጊዜ ሥራ አጥ ሲሆኑ በማህበረሰቡ ተፅዕኖ እያረፈባቸዉ ይሄዳሉ። ይህ ማለት ደግሞ የሥራ አጡ ቁጥር ከፍ ባለ ቁጥር ጭንቀቱ ወደ ፖለቲካዊ ትርጉም እየያዘ ሊሄድ ይችላል። አደባባይ የሚወጡ ሰዎች፣ተሟጋቾች ወይንም የአመፅ አንቀሳቃሾች እንዲህ ዓይነቶቹን ወጣቶች ሊጠቀሙባቸዉ ይችላሉ። ስለዚህ አደገኛ ሁኔታ ነው የሚኖረዉ።»
ሲሉ ያስጠነቅቃሉ ጣሊያናዊው ተመራማሪ። አውሮጳን በተመለከተ አክለው ሲናገሩም፤ ከ30 አመት በታች ያሉ 14 ሚሊዮን ሰዎች ያለ ሥራ፣ ያለ ትምህርት ወይንም ያለ ሙያዊ ስልጠና መቅረታቸው ዘላቂነት ያለው መፍትሄ እንዳልሆነ አሳስበዋል።
የአንዳንድ አካባቢዎችን የሥራ አጥ መዘርዝር ብንመለከት ከአውሮጳ የተሻለ ሁኔታ ይታያል። ነገር ግን አንዳንዴ መዘርዝሮችን ማመን ችግር ነው ይላል የዘገባው ጸሐፊ አንድሪያስ ጎርዘፍስኪ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2012 ለምሳሌ ከሰሀራ በስተደቡብ ያሉ የአፍሪቃ ሃገራት የሥራ አጥ ቁጥር 11,8 በመቶ ነበር። በኢንዱስትሪ የበለፀጉት የአውሮጳ ሃገራት ደግሞ 18,1 በመቶ። ይህንን ቁጥር በጥንቃቄ መመልከት ያሻል። ምክንያቱም በርካታ አፍሪቃውያን ሥራ አጥ ነኝ ብለው አልተመዘገቡም። ሌላም ምክንያት አለ። በተማርኩበት ሙያ ሥራ እስከማገኝ ብለውም አይጠብቁም። ለመኖር ሲሉ ያገኙትን ሠርተው ለመኖር ይጥራሉና። እንደ ILO ዘገባ እንደዚህ አካባቢ ሰው እየሠራ ፍፁም ከድህነት ያልተላቀቀበት የዓለማችን ክፍል የለም።
«በሥራ ዓለም ያለው ችግር እንደ የአገሩ እና አካባቢው ይለያያል። በሰሜን አፍሪቃ እና በመካከለኛው ምስራቅ ለምሳሌ ምንም አይነት መዋለ ንዋይ አይፈስም» ይላሉ የሥራ እና የወጣቶች ተመራማሪ ጋዳ ባርሶም፤ ካይሮ ከሚገኘው የአሜሪካ ዮንቨርሲቲ። «ስለሆነም ለአዲሱ ትውልድ አዲስ ሥራ ለመፍጠር አልተቻለም፣ በዚያ ላይ የብዙዎች ትኩረት በቢሮ ሥራዎች ላይ ይወሰናል። ያኔም ምሩቃንን በሙሉ በሥራ ለማሳተፍ በቂ ቦታ አይኖርም። ሥራ አጥነትን ለማጥፋት ለሁሉም የሚሆን ቀመር የለም» ይላሉ ባርሶም። ጣሊያኒያዊው ተመራማሪ ማሸሪኒም ቢሆኑ በዚህ ይስማማሉ። እንደሳቸው አንድ መቀየር ያለበት ነገር አለ። የሚሰጠው ስልጠና እና ሥራ ቀጣሪው ከምሩቃኑ ሊጠብቅ የሚችለው መመጣጠን ይኖርበታል። ተማሪዎች ከከፍተኛ የትምህርት ማዕከላት ተመርቀው ሲወጡ ምንም አይነት የሥራ ልምድ ላይኖራቸው ይችላል። በዚህ ምክንያትም የሚያገኙት ወረቀት እና ብቃታቸው ቀጣሪያቸው ከነሱ ከሚጠብቁት ጋ አይመጣጠን ይሆናል። ምንም ይሁን ምን ግን መፍትሄው አገር ለቆ መሰደድ አይሆንም ባይ ናቸው፤ ቋንቋን እንደምክንያት ይጠቅሳሉ።
«እኛ እያንዳንዱ ክፍለ ግዛት አንድ አይነት ቋንቋ እንደሚነገርበት እንደ ዮናይትድ እስቴትስ አይደለንም። እኛ አውሮጳውያን ነን። 21 የተለያዩ ቋንቋዎች ያሉን። በአባላቱ ሃገራት የዉስጥ እንቅስቃሴ መታየት የሚኖርበት የቋንቋ ገደብ አለ። ከአንድ የአባል ሀገር ወደ ሌላ ቦታ ሲኬድ ያለውን ችግር ነው ለማንፀባረቅ የሞከርኩት። ለምሳሌ አንዳሉዢያ ሥራ ያላገኘ ሰው የተሻለ የሥራ አጋጣሚ ወዳለበት ወደ ስፓኝ ባስካን አካባቢ ሄዶ እድሉን ሊሞክር ይችላል። ወይንም በእድሜ የገፉ ሰዎች ከሚኖሩባት ደቡብ ኢጣሊያ ወደ ሰሜኑ ሥራ ፍለጋ ሊጓዝ ይችላል።»
ጀርመን ሀገር የሚገኙ ወጣቶች ችግር ይህን ያህል አስጊ አይሁን እንጂ ችላ ሊባሉ የማይገባቸው የተወሰኑ ወጣቶች አሉ ይላሉ የሥራ ኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁር ዮህን ክሉቨ «እንደሚመስለኝ ጀርመን በአሁኑ ሰዓት በዓለም ዓቀፍ ዘንድ ጥሩ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ስዊዘርላንድን ጨምሮ የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ዝቅተኛ የሆነበት ሀገር ነን። ያ ማለት ግን ችላ ልንላቸው የማይገባን የተወሰኑ ሥራ አጥ ወጣቶች እንዳሉ ማስተዋል ይገባል። ይህ ደግሞ ያለንን የትምህርት አሰጣጥ መለስ ብለን እንድንቃኘው ያደርገናል። በብዛት በጀርመን እና በሌሎች በበለፀጉት ሃገራት ችግር የሚገጥማቸው ውጤት ያልመጣላቸው ወይንም በትምህርታቸው ጥሩ ያልነበሩ ናቸው። አንድ ወጣት በ25 ዓመቱ ለረዥም ጊዜ ሥራ ሳያገኝ ከቆየ ቀደም ሲል ባለፈበት ሂደት ላይ ችግር ነበር ማለት ነው። ስለዚህ የትምህርት ስርዓቱን መመልከት ግድ ይለናል። የሥራውን ዓለም ሊቀላቀሉ ያልቻሉት ወጣቶች 5 ወይ 7 ወይ 8 ከመቶም ይሁኑ ከነሱ እንደሚጠበቀዉ ትምህርታቸውን አላጠናቀቁም ማለት ነዉ።»
የወጣት ሥራ አጥነት እንብዛም ከማይታይባቸው ጀርመን እና ስዊዘርላንድ ወደ ደቡብ ምስራቅ አውሮጳ አልባንየን ወደ ካርላ ኤንግልሀርድ እናምራ።
አልባንያ ወደ 3 ሚሊየን የሚጠጋ ነዋሪ አላት። ብዙዎቹ ሕፃናት እና ወጣቶች ናቸው። የአውሮጳ ትንሿ አገር በቁጥር ትንሽ ብቻ ሳይሆን አማካይ እድሜያቸው 28 ዓመት የሆኑ አልባናውያን የሚኖሩባት አገር ናት። ብዙዎቹ ወጣቶች ታዲያ «ምን መሆን ትፈልጋላችሁ?» ሲባሉ መልሳቸው ሥራ አስኪያጅ ወይንም ኋላፊ መሆን ነው። ግን እነሱ የሚቀጠሩበት በቂ መሥሪያ ቤት እንኳን አገሪቱ የላትም። በዚህ ምክንያትም አንዳንዶች አገሩን ለቀው ለመሄድ ሲነሳሱ ቀሪዎቹ እጣ ፈንታቸውን ተቀብለው ለመሥራት ይጥራሉ።
መዲና ቲራና አየሩ ይሞቃል። በየቦታው ሻይ ቡና የሚባልባቸዉ ቤቶች አሉ። ሁሉም ማለት ይቻላል በወንድ ወጣቶች ተሞልተዋል። ምንም እንኳን ምሩቃን ቢሆኑም አብዛኞቹ ሥራ የላቸውም፤
«ህክምና ነው የተማርኩት። የማውቀው ሰው ስለሌለኝ ስራ አላገኘሁም።»
የሚያውቁት ሰው ቢኖርም እንኳን አንዳንዴ በዘመድ ለመቀጠርም ቢሆን ሥራውም አይገኝም። ችግሩ ይላሉ አኔተ ካስትን በአልባንያ ከጀርመን ኢንዱስትሪ የንግድ ማኅበር፤ «የኮሙኒስት ሥርዕት ካከተመ በኋላ የሚገኙት ወጣት አልባናዊያን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመከታተል ነዉ የሚመኙት። ከዚያም በሌለበት የኢኮኖሚው ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ለመሆን ይሻሉ።»
በትንሿ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጋ ነዋሪ ባላት አልባንያ ከ50 የሚበልጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ። አብዛኞቹ የግል ናቸው። በከፍተኛ ተቋም ገብቶ ለመማር በሺዎች የሚቆጠር ዩሮ ይፈጃል። አንዳንድ ወጣቶች ለትምህርታቸው የሚያወጡትን ገንዘብ እንኳን መልሰው አያገኙም።
«የሰቀቀን ትውልድ ነን። ተምረናል ግን አልተጠቀምንበትም። እኔ አፌን ከፈታሁበት ሌላ 3 ቋንቋዎችን እችላለሁ። አሁንም ግን ሥራ አጥ ነኝ። አልባንያን ጥዬ ለመሄድ እያሰብኩ ነው። ቤተሰቦቼ ውጪ ሀገር ነው ያሉት።»
ወደአንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ወጣት ወንድ እና ሴት አልባናውያን ድንበር ተሻግረው ነው በጎረቤት ግሪክ እና ኢጣሊያ የሚሰሩት። ይሁንና በሌሎቹ ሃገሮች ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ ዳግም ወደ ሃገራቸው ይመልሳቸዋል። በ20ዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው አድሚር ለሰባት ዓመት ጀርመን ኖሯል።
«በጣም ከባድ ነው። እዚህ መፈናፈኛ እንኳን የለም። ዲሞክራሲ የለም። የሚጎድለን ነገር የኑሮ ደረጃ አለመሻሻል እና ሰላም ነው። ሰላም ስል ለምሳሌ አንድ ሰው አየር ሊቀበል ወደመናፈሻ ወጥቶ፣ ወይም ወደቲያትር፣ ሲኒማ ወይ ሙዚየም ገብቶ በሰላም የሚመለስበት ሁኔታ ማለት ነው። እዚህ ሁለት ሲኒማ ቤት ነው ያለው። ይሁንና «ሀገር የሚባለዉ ተደላድሎ የሚኖርበት ቦታ ነው» ይባል የለ።»
አድሚር ለመቀየር የተቻለውን ይሞክራል። ቲራና የከፈታት የጣሊያን ምግብ ቤት የሀገሬውን እና የውጭውን ሰው ዘና ማድረጊያ ሆኗል። ወደሱ ምግብ ቤት ወጣት ፖለቲከኞች፣ አርቲስቶች እና የየመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ጎራ ይላሉ። አድሚር ከአብዛኞቹ ጋ በከተማይቱ በታወቀ አንድ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አብሮ ተምሯል። ትዉዉቁ ለዛሬ ጠቅሞታል።
በዓለም የሚታየዉንና እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሄደዉን የወጣት ሥራ አጥነት፤ በተለይም አውሮጳ ዉስጥ በአንዳንድ ሃገሮች የሚገኝበትን ደረጃ ነበር በዛሬው የወጣቶች አለም የዳሰስነው። ከድምፅ ዘገባው ታገኙታላችሁ።


አንድሪያስ ጎርዘፍስኪ እና ካርላ ኤንግልሀርድ
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ

+++ ACHTUNG: Wegen der niedrigen Qualität darf das Foto nicht als Artikelbild oder im Karussell verwendet werden! +++ The view from the joint activity with Albanian and German from Young European Federalists. Joint activity of the Albanian and German youth organization on the frame work of the Day of Europe. Foto: DW/Arben Muka, 08. 05. 2013, Tirana, Albanien
አልባንያ ያሉ ወጣቶች በስራ አጥነት ላይ ሲወያዩምስል DW/A. Muka
Arbeitslose afrikanische Männer sitzen auf einer Mauer, Germa, Libyen
ስራ አጥነት በአፍሪቃምስል picture-alliance/dpa
People line up at an employment office in Badalona, near Barcelona, April 25, 2013. More than six million Spaniards were out of work in the first quarter of this year, raising the jobless rate in the euro zone's fourth biggest economy to 27.2 percent, the highest since records began in the 1970s. The stickers on the wall read, "Unemployment". REUTERS/Albert Gea (SPAIN - Tags: BUSINESS EMPLOYMENT)
ስፓኝ እና በአውሮፓ ስራ አጦች ስራጥነታቸውን ሄደው ያስመዘግባሉ።ምስል REUTERS
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ