1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓመት ሳይሆን በየቀኑ ስለ«ኤች አይ ቪ» ይታሰብ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 21 2008

«የዓለም የኤድስ ቀን መታሰቡ መልካም ነዉ ግን ካልጠፋ ቀን በገና በዓል መዳረሻ መታሰቡን አልደግፈዉም።» ነዉ የሚሉት ዑርዙላ ፊሸር። ጀርመናዊቱ ወይዘሮ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1993ዓ,ም ነዉ «ኤች አይ ቪ» ተሐዋሲ በደማቸዉ ዉስጥ እንደሚገኝ ያወቁት።

https://p.dw.com/p/1HFOW
Welt-AIDS-Tag 01.12.2014 Indien
ምስል Reuters/R. De Chowdhuri

በዓመት ሳይሆን በየቀኑ ስለ«ኤች አይ ቪ» ይታሰብ

ዑርዙላ ፊሸር «ኤች አይ ቪ» በደማቸዉ ዉስጥ እንዳለ የተረዱት በተለየ አጋጣሚ ነዉ። ያን ጊዜ ባለቤታቸዉ ሀኪም ቤት ገብተዉ ክብደታቸዉም ቀንሶ ነበር።

«እናም የተገመተዉ የአንጀት ካንሰር ይዞታል ተብሎ ነበር። ምርመራ ሲደረግ ግን ጉዳዩ ይህ አይደለም፤ ወይም ያን ያህል የሚያደርስ አልነበረም። እናም ባለቤቴ በዚያን ጊዜ ለዶክተሩ፤ አንድ ሰዉ እንዲህ ክብደቱ ሊቀንስ የሚችለዉ በሁለት ነገሮች ብቻ ነዉ፤ አንድም ካንሰር፤ ያ ካልሆነም ኤድስ ከያዘዉ ነዉ አለዉ። ከዚያም ባለቤቴ ሲመረመር ተሐዋሲዉ በደሙ ዉስጥ ተገኘ። ያኔ እንግዲህ ለ23ዓመታት በጋብቻ ስለኖርን እኔም መመርመር ነበረብኝ። እናም የእኔም ዉጤት እንዲሁ ተመሳሳይ ሆነ።»

በዚያን ጊዜ አንድ ሰዉ «ኤች አይ ቪ» በደሙ ዉስጥ እንዳለ በይፋ ከታወቀ ከኅብረተሰቡ የሚገጥመዉ ምላሽ ራሱን ደብቆ እንዲኖር የሚገፋ ይመስላል። ፊሸር የያኔዉን አሁን ወደኋላ ዞረዉ እንዲህ ያስታዉሳሉ።

«ያኔ አንድ ሰዉ ተሐዋሲዉ በደሙ እንዳለ አረጋገጠ ማለት የሞት ፍርድ ተፈረደበት እንደማለት ነዉ። ኅብረተሰቡን ከተመለከትን ደግሞ ማንም ምንም አይልም ነበር። ሰዉ ዝምታን ይመርጣል፤ እኔም ብሆን እጅግ ቅርብ ለሆኑ ዘመድ ወዳጆች ነዉ የነገርኩት ያዉም እሱም ከአንድ ዓመት በኋላ ነዉ፤ እንጂ ዝም ነዉ ያልኩት። »

ፊሸር እና ባለቤታቸዉ በ«ኤች አይ ቪ» ሊያዙ የቻሉበት አጋጣሚ እሳቸዉ እንደገለፁት ከተጠቀሙት ደም እና የደም ምርቶች ጋር በተያያዘ ምክንያት ነዉ። በወቅቱም ወደቦን ከተማ መጥተዉ የተፈጠረዉ ስህተት ያስከተለዉን መዘዝ ለማሳየት ለመንግሥት በእማኝነት ቀርበዋል። ጉዳዩን ይዘዉ ሲሟገቱም ለእነሱ ብቻ ሳይሆን በተመሳሳይ ችግት ለበሽታዉ ለተጋለጡ ወገኖች መብት መከበር ጭምር እንደሆነ ያስረዳሉ።

Blutabnahme für HIV-Test in Südafrika
ለHIV ተሐዋሲ ምርመራምስል picture alliance/dpa/J. Hrusa

«ያኔ በ1988ዓ,ም ነዉ በይፋ ስለጉዳዩ ለመናገር አደባባይ የወጣነዉ። ያንንም ያደረኩት ለራሴ ብቻ ሳይሆን ለመሠረታዊዉ ጉዳዩ ስል ነዉ። «ኤች አይ ቪ» ይፋ እንዲሆን ነዉ የታገልነዉ፤ ዛሬም የማደርገዉ እሱኑ ነዉ። ለመብታችን ነዉ የታገልነዉ። አንድ ሰዉ በመርፌ ወይም በሌላ ምክንያት በተሐዋሲዉ ሊያዝ ይችላል። ይህ ደግሞ አሁንም ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነዉ። በዚያን ጊዜ ግን እኔና ባለቤቴ ስለጉዳዩ በይፋ ለመናገር አደባባይ የወጣነዉ በድፍረት ነዉ። አሁንም ግን በሽታዉ ዛሬም እንደነዉር በይፋ የማይወራለት በሽታ ነዉ። በጥቅሉ ሰዎች ስለዚህ በሽታ በይፋ ለመናገር አይደፍሩም።»

በዚያን ወቅት የ«ኤች አይ ቪ» በደሙ ዉስጥ መኖሩን በአደባባይ የሚገልጽ ወይም ለሰዎች የሚናገር ራሱ መልሶ መሳቀቅ እና ጭንቀትን እንደሚያተርፍ ነዉ ዑርዙላ ፊሸር የሚናገሩት። ለምን ይሆን ስለ«ኤች አይ ቪ» መነጋገር እንደነዉር የሚታየዉ? ምላሽ አላቸዉ፣

«እኔ እንደሚመስለኝ በዋናነት በወሲብ የሚተላለፍ ስለሆነ ነዉ። ወሲብ ሰዎች በይፋ ከማይነጋገሩባቸዉ ጉዳዮች አንዱ ነዉ። ይህ የእኔ አስተያየት ነዉ። እናም በእኔ አስተያየት እንዲህ ያለዉ አመለካከት ጊዜዉ ያለፈበት ይመስለኛል። እኔ እንዲህ ነዉ የሚገባኝ።»

ከ20ዓመታት በፊት ስለፀረ «ኤች አይ ቪ» መድኃኒቶች በስፋት መገኘት አይደለም፤ ተሐዋሲዉን ሊያዳክም እና የታማሚዎቹን የበሽታ መከላከል አቅም ለመገንባት ስለመቻሉ አይወራም ነበር። መድኃኒት የሌለዉ በሽታ የሚለዉ አገላለፅ በራሱ ወይዘሮዋ እንዳሉት ከሞት ፍርድ ያልነተናነሰ ፍርሃትን የሚያነግስ ነበር። በርካታ በተሐዋሲዉ የተያዙ ወገኖች እንዲህ ባለዉ አገላለፅ ብቻ ተጨንቀዉ ዕለተ ሞታቸዉን ተስፋ በመቁረጥ ጠብቀዋል። ዑርዙላ ፊሸር እሳቸዉ በተሐዋሲዉ መያዛቸዉን ባወቁበት ወቅት እንዳሁኑ ባይሆንም ጀርመን ሀገር መድኃኒት እንደነበር ያስታዉሳሉ።

Brasilien AIDS Schleife zum Welt AIDS Tag in Brasilia
ምስል ANTONIO SCORZA/AFP/Getty Images

«በ1993፤ 94 ጀርመን ዉስጥም ሆነ በአንዳንድ ሃገራት የነበረዉ አንድ መድኃኒት ብቻ ነበር። በዚያን ጊዜ አንድ ሰዉ በደሙ ዉስጥ ያለዉን የተሐዋሲ መጠንም መለካት አይችልም ነበር። የመድኃኒት ፋብሪካዎች በ1995ዓ,ም ነዉ መመርመሪያዉን የፈለሰፉት። ከዚያ በኋላ ግን በHIVም ሆነ ኤድስ ላይ በጀርመንም እና በመላዉ ዓለም ብዙ ተሠርቷል። እናም በአሁኑ ጊዜ ከ20 የሚበልጡ መድኃኒቶች አሉ። በዚህ ረገድ ያለዉ መሻሻልም እየቀጠለ ነዉ።»

በአሁኑ ጊዜ መድኃኒቶቹ መኖራቸዉ አንድ ነገር መሆኑን የሚገልፁት ፊሸር መድኃኒቱ በየቦታዉ እንደልብ የሚገኝ ከሆነ ለታማሚዎቹም ሆነ ለኅብረተሰቡ አንድ ሸክም እንደቀለለ ይቆጠራል ይላሉ። መድኃኒት መበርከቱ፤ ምርምሩ መጠናከሩ መልካም ሆኖ ሳለ «ኤች አይ ቪ» ተሐዋሲን በሚመለከት ወጣቶች ያላቸዉ ግንዛቤ ግን ያሳስባቸዋል።

«ከ20 ዓመታት በላይ ተሐዋሲዉን መከላከል ላይ እንደሠራ ሰዉ ስመለከተዉ፤ አስፈላጊዉ መረጃ በሚገባ ተዘጋጅቷል። ስለHIV እና ኤድስ ለማወቅ የሚፈልግ ሁሉ በዚያ አማካኝነት ማወቅ ይችላል። ነገር ግን በርካታ ወጣቶች ስለዚህ የማወቅ ፍላጎት እንደሌላቸዉ አረጋግጫለሁ። ወይም ደግሞ ይሰማሉ ግን መልሰዉ ይዘነጉታል። እናም እንዳልኩት ከ20 ዓመታት በላይ መከላከል ላይ እንደሚሠራ ግለሰብ፤ ጀርመን ዉስጥ በየዓመቱ በምርመራ HIV በደማቸዉ የሚገኝ ሰዎች ቁጥር አለመለወጡ ያሳስበኛል። በተቃራኒዉ ይጨምራል፤ በዚያ ላይ በርካታ ወጣቶች አሁን መድኃኒት አለ፤ የተወሰኑ መድኃኒቶች ወስጄ ያበቃል ብለዉ ያስባሉ፤ ሆኖም ግን እንዲያ ሳይሆን ሲቀር ያዝናሉ።»

ከ20ዓመታት በፊት ስለበሽታዉ የነበረዉ እና አሁን የሚታየዉን ልዩነት አስመልክተዉ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤

«በህክምናዉ ረገድ ያለዉ ልምድ እየዳበረ ሄዷል፤ በተቃራኒዉ ግን ሰዎች ዛሬም ጥንቃቄ የሚወስዱ ዓይነት አይደሉም። ሆኖም ግን ከዕለታት አንድ ቀን በሚገኘዉ መድኃኒት ይህ በሽታ ሊድን ይችላል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ።»

Symbolbild Aids
ፀረ HIV መድኃኒትምስል Colourbox

በህክምናዉ ዓለም ብዙ እንደሚነገረዉ ካንሰርም እንደHIV ይህ ነዉ የሚባል ፍቱን መድኃኒት ያልተገኘለት በሽታ ነዉ። ነገር ግን ከካንሰር ይልቅ «ኤች አይ ቪ» ኤይድስ ብዙ ይወራለታል፤ ትልቅ ስፍራም ይሰጠዋል። ዑርዙላ ፊሸር ስለበሽታዎቹ የሚሰጠዉ ግምት ልዩነት አለዉ ባይናቸዉ፤

«አንድ ሰዉ ካንሰር ተገኘብኝ ቢል በተበላሸዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ምክንያት የመጣ ስቃይ እንደሆነ ይታመናል። ነገር ግን አንድ ሰዉ «ኤች አይ ቪ» በደሜ ዉስጥ አለ ብሎ ቢናገር፤ ሰዎች በራሱ ጥፋት ያመጣዉ ነዉ ብለዉ ያስባሉ። በስርዓትም የኖረ ይሁን እራሱን የጠበቀ ቢሆን ማለት ነዉ እናም ይህ ሊገባኝ ያልቻለ ጉዳይ ነዉ። ለዚህም ነዉ «ኤች አይ ቪ» እንደማንኛዉም በሽታ እንዲታይ የምንታገለዉ። ሆኖም ግን አሁንም የጥፋት በሽታ ተደርጎ ነዉ የሚወሰደዉ።»

ዑርዙላ ፊሸር ቀጠሉ፤ ዛሬ የዓለም የኤድስ ቀን ነዉ፤ ዕለቱ መታሰቡ አንድ ነገር ቢሆንም ሰዎች ትኩረታቸዉ በገና በዓል ላይ በሆነበት ወቅት መደረጉ ትኩረት ያሳጣዋል።

«የዓለም የኤድስ ቀን ለገና በዓል ጥቂት ቀናት ሲቀሩት መታሰቡ ያሳዝናል። ምክንያቱም ዓመቱን ሙሉ ስለኤድስ መነጋገር ሲቻል፤ ገና ተቃርቦ በየቦታዉ የተለያዩ ዝግጅቶች ለዚሁ ትኩረት በሚስቡበት ጊዜ ቀኑ እንዲታሰብ ተደርጓል። ስለእሱ ብዙ መነጋገር እንዲቻል በዓመቱ መካከል ወይም መባቻ ላይ መደረግ ነበረበት። እንዲያም ሆኖ የዓለም ኤድስ ቀን የሚባል መኖሩ ጠቃሚ ነገር ነዉ። አንዱ ወይም ሌላዉ ሊድን የማይችል በሽታ መኖሩን በዚህ ጊዜ ማስታወስ መቻሉ በራሱ አንድ ነገር ነዉ።»

Symbolbild AIDS HIV Afrika Jugendliche
ምስል Getty Images/AFP/T. Kitamura

ከተሐዋሲዉ ጋር የሚኖሩ ወገኖችን ዛሬ ብዙም ባይጠናም የማግለሉ አካሄድ ለመረጃ ብዙም ቅርበት የሌላቸዉ በሚባሉ ሃገራት ብቻ ሳይሆን ሰለጠኑ በሚባሉት ጭምር መሆኑን ዑርዙላ ፊሸር አልሸሸጉም። ለዚህም በዚህ ዕለት የሚመኙትን እንዲህ በማለት ዘረዘሩ፤

«ሰዎች ስለበሽታዉ ያላቸዉ አመለካከት ግልፅ እንዲሆን እና «ኤች አይ ቪ» በደማቸዉ የሚገኝ ወገኖችን ማግለል እንዲያቆሙ እመኛለሁ። በሽታዉ እንደማንኛዉም በሽታ ታይቶ ሰዎች በየጊዜዉ በይፋ የሚነጋገሩበት እንዲሆን፤ አንድ ሰዉ «ኤች አይ ቪ» በደሙ መኖሩ ሲታወቅም በሃኪሞች ወይም ደግሞ በጉዳዩ ላይ በሚሠሩ የሩቅ ሰዎች ብቻ እንዲረዳ ባይተዉ እመኛለሁ። ምርምሩም በስፋት እንዲቀጥል፤ በተሐዋሲዉ የሚያዙት ሰዎችም ቁጥር እንዲቀንስ እመኛለሁ።»

ስለ«ኤች አይ ቪ»እና «ኤድስ» በየመገናኛ ብዙሃን የሚቀርበዉ ዘገባና መረጃም ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን በተለይ ደግሞ ዓመታዊዉ የዓለም የኤድስ ቀን ሲታሰብ እንደሚበረክትም ሳይጠቁሙ አላለፉም። እሳቸዉ እንደታዘቡትም በዚህ ወቅት ብቻ ለበሽታዉ ትኩረት መስጠቱ ታርሞ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ጊዜያት እያሰለሰ ቢወሳ አስተማሪነቱ የበለጠ እንደሚሆንም እምነታቸዉን ገልጸዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ