1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዩክሬን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተካሄደ

እሑድ፣ ግንቦት 17 2006

የሩስያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬይን ሊደረግ የታቀደዉን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የማጨናገፍ ፍላጎት አላቸው የሚለውን አመለካከት ማጥፋት እንደሚፈልጉ ተዘገበ።

https://p.dw.com/p/1C6Fr
Wahl in der Ukraine Kiew Stadtteil Petschersk
ምስል DW/R. Goncharenko

የክሬምሊኑ መንግሥት ዋና ተጠሪ ቭላድሚር ፑቲን ትናንት ባደረጉት ንግግራቸዉ «በዩክሬይን የሚደረገዉን የምርጫ ዉጤት እንደሚያከብሩ» ገልፀው ነበር። ፑቲን ምርጫዉን እንደሚያከብሩ ይናገሩ እንጂ «እውቅና እንደሚሰጡ» ግን አልገለፁም። በሩስያ ዓይን፤ አሁንም የካቲት ላይ ከመንበረ ሥልጣናቸዉ የተባረሩት፤ የቀድሞዉ የዩክሬይን መሪ ፕሬዚዳንት ቪክተር ያኑኮቪች፤ በሕጋዊ መንገድ የተመረጡ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆናቸዉን አመላክተዋል። በሌላ በኩል ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ በሩስያ ላይ የሚጣለዉ ማዕቀብ፤ ከባድ መዘዝ እንዳያስከትል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኪይቩ ጊዜያዊ የመንግሥት አስተዳደር፤ በምስራቃዊ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ታፍነዉ መወሰዳቸዉን፤ ይፋ አድርጎአል። ግጭት አይሎ በሚታይባቸዉ በምሥራቃዊዉ የዩክሬይን ግዛቶች የምርጫ ጣብያዎች ላይ ጥቃት ተጥሎአል፤ የምርጫ ቅፆች እና ጽህፈት ቤቶች ወድመዋል። የዩክሬይን ምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይፋ እንዳደረገዉ በተለይ መፍቀሬ-ሩስያ ተገንጣዮች በሚበዙበት በሉአንስክ እና ዳኔስክ አዉራጃዎች ዉስጥ፤ ከሚገኙ 34 የምርጫ ጣብያዎች መካከል 20ዉ በመፍቀሬ-ሩስያ ተገንጣዮች ቁጥጥር ሥር ወድቀዋል።

የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩስያን ከዓለም ምጣኔ ሀብት ማግለል ፈጽሞ የማይታሰብ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ሩስያ ከተቀረው ዓለም ጋር ወደ ቀዝቃዛ የዓለም ጦርነት ዳግም እየገባች ነው የሚባለውን አስተያየት አጣጥለዋል። ፑቲን ዩክሬን ወደ ለየለየለት የርስ በርስ ጦርነት እያዘቀጠች ነዉ ሲሉ ትናንት አስጠንቅቀው ነበር። የዩክሬን መንግሥት ጦርና ምሥራቃዊ ዩክሬን የሸመቁ ደፈጣ ተዋጊዎች ዶንሴክ አጠገብ በገጠሙት ዉጊያ በትንሹ ስባት ሰዎች ተገድለዋል። ከትናንት በስትያ እዚያዉ ምሥራቅ ዩክሬን ዉስጥ አማፂያን በከፈቱት ጥቃት አስራ-ሥምንት የመንግሥት ወታደሮች ተገድለዉ ነበር።

ዩክሬን ዉስጥ ዛሬ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመደረግ ላይ ነዉ ። 35 ሚሊዮን የሚጠጋ የዩክሬን ነዋሪ በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲሳተፍ ጥሪ ተደርጎለታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ

Ukraine Wahlen
ምስል DW/G. Stadnyk