1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ሱዳን የቀጠለው የኃይል ተግባር

ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2007

በደቡብ ሱዳን መንግሥት ብዙ ሴቶች እና ልጃገረዶች በመንግሥቱ ወታደሮች በወሲብ መደፈራቸው፣ ህፃናትም በግዳጅ ለውጊያ ተግባር መመልመላቸው ተሰምቷል። በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞው ምክትላቸው ሪየክ ማቸር መካከል የተጀመረው የሰላም ድርድርም እስካሁን ውጤት አላስገኙም፣ እና ደቡብ ሱዳን ወዴት እያመራች ይሆን?

https://p.dw.com/p/1FrEK
Afrika Bildergalerie Kindersoldaten im Süd-Sudan
ምስል DW/A. Stahl

[No title]

በደቡብ ሱዳን የክብረ ንፅሕና ድፍረት፣ ግድያ፣ የግዳጅ ምልመላ ሆን ተብሎ እየተፈፀመ መሆኑን የተመድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ያይን ምስክሮችን አነጋግሮ ያወጣው አስደንጋጭ ዘገባ አስታውቋል። በዘገባው መሠረት፣ የመንግሥቱ ወታደሮች እና ተባባሪዎቻቸው ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ከደፈሩ በኋላ ከነሕይወታቸው በእሳት ማቃጠላቸው ተገልጿል። የሺሉክ ሚሊሺያ ቡድን ተዋጊዎች በዚህ በሰኔ ወር ብቻ እስከ 1,000 ሕፃናትን፣ የ13 ዓመት ሳይቀር አግተው ወደ አንድ ማሠልጠኛ ጣቢያ እንደወሰዱዋቸው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ፣ «ኢጋድ» አስታውቋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የ«ዩኒሴፍ» ቃል አቀባይ ክሪስቶፍ ቡሉአራክ በደቡብ ሱዳን በዩኒቲ፣ አፓር ናይል እና ጆንግሌይ ግዛቶች የሚኖሩ ህፃናት በግዳጅ ምልመላ እና ባልተመጣጠነ አመጋገብ ችግር ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ደቡብ ሱዳን በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝም በምህፃሩ «ጊጋ» የተባለው በሀምበርግ ከተማ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ቲም ግላቪዮን አረጋግጠዋል።

Salva Kiir und Riek Machar unterzeichnen Abkommen
ምስል AFP/Getty Images

« የሚያሳዝነው፣ የደቡብ ሱዳን ሁኔታ እየተሻሻለ አይደለም። እያንዳንዱ ቀን ባለፈ እና ውዝግቡም እየተባባሰ በሄደ ቁጥር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የጦር መኮንኖች የኃይሉን ተግባር ሲያጠናክሩ ይታያል። እና ደቡብ ሱዳን በመሻሻል ጎዳና ላይ አይደለም የምትገኘው፣ በዚህ ፈንታ በሀገሪቱ የጭካኔ እና የኃይሉ ተግባር እየተስፋፋ ሄዷል። »

በደቡብ ሱዳን በፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና በቀድሞው ምክትላቸው ሪየክ ማቸር ደጋፊዎች መካከል እአአ በ2013 ዓም መጨረሻ ውጊያ ከተጀመረ ወዲህ ፣ ሁለት ሚልዮን ሕዝብ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለ ሲሆን፣ ከዚሁ መካከል 500,000 ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰዶዋል። ሀገሪቱን ለማረጋጋት የተኩስ አቁም ደንብ ለማስገኘት እና ተቀናቃኞቹን ወገኖች ለማስታረቅ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ፣ «ኢጋድ» ሸምጋይነት በርካታ የሰላም ድርድሮች ቢደረጉም ፣ ጥረቶቹ ውጤት አልባ ሆነው የቀሩት። እርግጥ፣ ባለፈው የሳምንት መጨረሻ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና የቀድሞው ምክትላቸው ሪየክ ማቸር ናይሮቢ ላይ ቢገናኙም እና ምንም እንኳን ሁለቱን ተቀናቃኞች ለማገናኘት የሸምጋይነቱን ሚና የተጫወቱት የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ግንኙነቱ ራሱ አዎንታዊ እንደነበር ለማመልከት ቢሞክሩም፣ ተጨባጭ ውጤት ላይ መድረስ አለመቻሉን ያማፅያኑ ቡድን ቃል አቀባይ ማቢዮር ጋራንግ አስታውቀዋል። ግን ካሁን ቀደም በተደረጉ ድርድሮች ለምሳሌ የተኩስ አቁም ስምምነቶች እና የሥልጣን ክፍፍል ውይይትን የመሳሰሉ ተጨባጭ ውጤቶች ቢገኙም፣ የተኩስ አቁሙ ስምምነቶች ሁሉ ተግባራዊ ከሆኑ ከጥቂት ጊዜ በኋላ መጣሳቸው የሚታወስ ነው። ቲም ግላቪዮን እንደሚገምቱት፣ ተቀናቃኞቹ ወገኖች ዋነኛ ትኩረት ያረፈው ሀገሪቱን በማረጋጋቱ ላይ ሳይሆን ሥልጣናቸውን በማጠናከሩ ላይ ነው።

« ጉዳዩ የሥልጣን ጥያቄ ነው። ሥልጣን ሲኖር ደግሞ የተፈጥሮ ሀብትን ፣ ብሎም፣ በደቡብ ሱዳን የነዳጅ ዘይቱን ሀብት መቆጣጠር ይቻላል። ችግሩ ደቡብ ሱዳን ውስጥ የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ነው ያለው፣ ሳልቫ ኪር እና ሪየክ ማቸርም የዚሁ ፓርቲ አባላት በመሆናቸው፣ የፓርቲው ሊቀ መንበር እና የሀገሪቱ ፕሬዚደንት መሆን የሚፈልጉት ያማፅያኑ መሪ ማቸር ይህን ዕቅዳቸውን ገሀድ ማድረግ የሚችሉበት ዕድላቸው የመነመነ ሆኖ ማየታቸቸው ነው። ለዚህም ነው የብረቱን ትግል የጀመሩት። ሳልቫ ኪርም ቢሆኑ ሥልጣናቸውን ማጣት አይፈልጉም። »

በወታደራዊ ርምጃ ማሸነፍ የሚችሉ ስለመሰላቸው ለድርድሩ ያን ያህል ትኩረት ያልሰጡት ሁለቱም ወገኖች በደቡብ ሱዳን ውጊያውን አጠናክረው መቀጠሉን መርጠዋል።

Karte Südsudan DEU
ምስል DW

መጀመሪያ ላይ ከመንግሥቱ ወታደሮች ጎን ተሰልፎ ሲዋጋ የነበረው እና ካለፈው ግንቦት ወዲህ የማቸር ዓማፅያን ቡድንን መደገፍ የጀመረው በጀነራል ጆንሰን ኦሎኒ የሚመራው የሺሉክ ሚሊሺያ ቡድን ለሕፃናት የግዳጅ ምልመላ ተጠያቂ መሆኑን የተመድ ያወጣው ዘገባ አሳይቷል።

የተመድ በሶስት የመንግሥቱ እና በሶስት ያማፅያኑ ቡድን ጀነራሎች ላይ ማዕቀብ በመጣል፣ በዝውውር ነፃነታቸው እና የባንክ ሂሳባቸውን ለማገድ እያሰላሰለ ነው። እንደ ግላቪዮን አስተሳሰብ ይህ ዓይነቱ ስልት የተሳሳተ ነው፣ ምክንያቱም፣ የሰላሙ ድርድር ውጤት አልባ ለሆነበት እና በሲቭሉ ሕዝብ ላይ የኃይሉ ተግባር ለቀጠለበት ድርጊት በፖለቲካው ዘርፍ ያን ያህል ተሰሚነት የሌላቸው ስድስቱ ጀነራሎች ተጠያቂ አይደሉም። ለደቡብ ሱዳንን ችግር በርግጥ መፍትሔ ለማስገኘት እና ሲቭሉን ማህበረሰብ ለማጠናከር ከተፈለገ፣ አሁን እንደሚሰማው በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ መጣል ሳይሆን ውጊያው ለቀጠለበት ድርጊት ተጠያቂ የሆኑትን የጦር ኃይሉን መሪዎች የገንዘብ ምንጭ ማድረቅ፣ ብሎም፣ ከነዳጅ ዘይት ሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ ማስቆም ያስፈልጋል። የጦር ኃይሉ መሪዎች ላይ ጠንካራ ርምጃ መውሰድ ተገቢ ይሆናል።

ዛራ ሽቴፈን/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ