1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ሱዳን ያገረሸው ውጊያ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 25 2008

በደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ እና የብሔራዊው አንድነት መንግሥት ከተቋቋመ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ፣ አንድ አዲስ የዓማፅያን ቡድን ውጊያ መጀመሩን የመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1JHej
Südsudan Schutzzone Malakal
ምስል Getty Images/AFP/A.-G. Farran

በደቡብ ሱዳን ያገረሸው ውጊያ

ይኸው በዓሊ ታሚም ፋርታክ የሚመራው እና ራሱን የራጃ ነፃነት እስላማዊ ንቅናቄ ብሎ የሚጠራው የሚሊሺያ ቡድን ከመዲናይቱ ጁባ 650 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው የዋው አካባቢ ከመንግሥቱ ጦር ጋር ባለፉት ጥቂት ቀናት ባካሄደው ውጊያ ከአርባ የሚበልጡ ሰዎች ሲገደሉ፣ 70,000 ደቡብ ሱዳናውያን ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፣ ከነዚህም በአስር ሺህ የሚቆጠሩት በተመድ ተልዕኮ ሰፈሮች ወይም በቀይ መሥቀል ሰፈሮች ከለላ ጠይቀዋል።

በቀድሞው በደቡብ ሱዳን የተመድ ልዩ ልዑክ ፔተር ሹማን ለዶይቸ ቬለ እንዳሉት፣ የራጃ ነፃነት እስላማዊ ንቅናቄ በደቡብ ሱዳን ከሚንቀሳቀሱት በርካታ ያካባቢ ቡድኖች መካከል አንዱ ነው።

«አዲስ ያማፅያን ቡድን ነው ብዬ አላስብም፣ በዋው ግዛት ውስጥ በመንግሥቱ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ፣ «ኤስ ፒ ኤል ኤም» እና በተቃዋሚዎቹ የ«ኤስ ፒ ኤል ኤም፣ ኤን» ቡድኖች መካከል ግጭቶች ሁሌም ሲካሄዱ አይተናል፣ ከዚሁ ጎን ደግሞ ሌሎች ያካባቢ ቡድኖች የራሳቸውን ሚና ሲጫወቱ ተመልክተናል። እነዚህ ቡድኖች ባካባቢው ደረጃ የሚጫወቱት ሚና በኔ አመለካከት የተለመደ እና በሌሎች የደቡብ ሱዳን አካባቢዎችም የሚታይ ነው። »

Südsudan Schutzzone Malakal
ምስል Getty Images/AFP/A.-G. Farran

ፔተር ሹማን እንዳስረዱት፣ የራጃ ነፃነት እስላማዊ ንቅናቄን የመሳሰሉት እነዚህ ያካባቢ ቡድኖች የግል ጥቅማቸውን የሚያራምዱ ብሔራዊ አጀንዳ የሌላቸው ናቸው።

« እኔ እንደማየው ከሆነ፣በወቅቱ ደሞዛቸውን ያልተከፈሉ ብዙ ወታደሮች እና ሚሊሺያዎች አሉ፣ እና ራሳቸውን ለመርዳት ብቻ በማሰብ ዝርፊያን ዋናው ዓላማቸው አድርገዋል። »

ይኸው የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ያስቀደሙ የታጠቁ ቡድኖች የጫሩት የቅርብ ጊዜው ግጭት በዋው የሚገኘው ርዳታ ጠባቂ ተፈናቃይ ሕዝብ መከራ እና ስቃይን አባብሶዋል፣ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ሪየክ ይህንኑ ሁኔታ በጥብቅ አውግዘዋል።

« በዋው ባፋጣኝ ምላሽ ማግኘት የሚገባው አሳሳቢ የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ ተፈጥሮዋል። በተመድም ሆነ በቀይ መሥቀል ስር ከለላ ላገኙት ብቻ ሳይሆን፣ በብዛት በ«ኤስ ፒ ኤል ኤ፣ አይ ኦ» ቁጥጥር ስር ወደሚገኘው የገጠሩ አካባቢ ለሸሹት ተፈናቃዮችም አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ያስፈልጋቸዋል። በተለይ፣ ውጊያው ባለፈው ሚያዝያ ወር በይፋ አቁሞዋል መባሉ ሲታሰብ፣ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው፣ ይህን በጥብቅ አውግዘነዋል። በዋው ይህ ዓይነት ሁኔታ ይከሰታል ብለን አልጠበቅንም ነበር። »

የሰሞኑ ግጭት እና ውጊያ ለተፈናቃዮቹ የታሰበው የዓለም የምግብ ድርጅት፣ በምህፃሩ፣ የ«ዳብል ዩ ኤፍ ፒ» ርዳታ ለሕዝቡ እንዳይደርስ አስተጓጉሎዋል። ይህ ባጠቃላይ በደቡብ ሱዳን የሚታየው አሳሳቢ የኤኮኖሚ ቀውስ ውጤት አመላካች መሆኑን እንዳጎላ ሹማን አስረድተዋል። በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞቹ ወገኖች የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ቢጀምሩም በሀገሪቱ ፀጥታ እና መረጋጋት የሚወርድበት ጊዜ ገና ሩቅ መሆኑን ሹማን አመልክተዋል።

Peter Schumann
ምስል Torsten Hönig

« በሀገሪቱ ያለመረጋጋቱ ሁኔታ፣ ሚሊሺያ ቡድኖችም ሕዝቡን የሚያሸብሩበት ርምጃ ተባብሶ መቀጠሉ አይቀርም። ከ«ዩኤንኤችሲአር» ያገኘሁት መዘርዝር እንደሚያሳየው፣ በጎረቤት ሀገራት ከሰባት እስከ ስምንት መቶ ሺህ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ብዙዎቹ በሱዳን ይኖራሉ። ግማሹ ያህል የደቡብ ሱዳን ሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለው ለማለት ይቻላል፣ ከረሀብ፣ ችግር እና ከቁጥጥር ውጭ ከሆነው የኃይል ተግባር ሽሽት ላይ ነው። እና በሀገሪቱ መረጋጋት ሊወርድ ይችላል የሚያስችል አንዳችም ምልክት አይታይም። »

በነገራችን ላይ፣ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ሀምሌ ዘጠኝ፣ 2011 ዓ.ም. ነፃነቷን ያገኘችው የደቡብ ሱዳን መንግሥት ሀገሩ በገጠማት ኤኮኖሚያዊ ችግር ሰበብ አንድ ሳምንት የቀረውን አምስተኛው የነፃነት ዓመት ክብረ በዓልን ሰርዞዋል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ