1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ላይ ግፊቱ አይሏል

ረቡዕ፣ ሐምሌ 29 2007

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በቅርቡ ከስምምነት ካልደረሱ «የማያዳግም» ያሉት አማራጭ መዘጋጀቱን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት አስጠነቀቁ። ኦባማ ከተመድ ዋና ጸሐፊ በዚህ ላይ ከተነጋገሩ በኋላ እንደተናገሩት ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪርና የአማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቻር ስልጣን ለመጋራት መስማማት ካቃታቸዉ ሰላም ለማስፈን ብቃት የላቸዉም ማለት ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GAR5
Süd Sudan Gipfel im Präsidentenpalast von Addis Abeba
ምስል Yohannes G/Eziabhare

[No title]

ዩናይትድ ስቴትስ ደቡብ ሱዳን ከሰሜንዋ ተገንጥላ ነፃነትዋን እንድታዉጅ «በአዋላጅነት» ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተች የአደባባይ ምሥጢር ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011,ም ርዕሠ-ከተማዋን ጁባ ስታደርግም የአሜሪካን ዶላርና ድጋፍ ጎርፎላታል። ግን ደግሞ እንደሀገር ለመራመድ በለጋነቷ ስትዉተረተር ብዙም መጓዝ ሳትችል ወትሮ በለመደችዉ የእርስ በርስ ጦርነት አዙሪት ተጠለፈች። ደቡብ ሱዳንን እንደሀገር ሲሞሽር የቆየዉ የዩናይትድ ስቴትስ በተለይም የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደርም በቋፍ የነበረችዉን ሰበበኛ ሀገር ችላ ብሏል በሚል ወቀሳ ይሰነዘርበታል።ኦባማ ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ዉስጥ የኢጋድ አባል ሐገራትን ሲያነጋግሩ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ባስቸኳይ ከስምምነት እንዲደርሱ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ያ ካልሆነም ሌላ አማራጭ እቅድ ተግባራዊ ሊደርግ እንደሚችል ትናንት ከተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ጊ ሙን ጋ ከተወያዩ በኋላ ይፋ አድርገዋል። ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ሲዋጉ ዓመታት ያሳለፉት የአሁኑ የጁባ ገዢዎች በአንፃሩ ማዕቀብ ሊጣልባቸዉ እንደማይገባ እና ባስቸኳይ የሚባል የሰላም ስምምነት ሊኖር እንደማይችል ነዉ የተናገሩት። ይህም እነዚህ ወገኖች ላይ የሚደረገዉ ግፊት ዉጤት ሊያመጣ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄን አስነስቷል። በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ማለትም ኢጋድ የደቡብ ሱዳንን የሰላም ስምምነት ገቢራዊነት የሚከታተልና የሚያጣራዉ ዘርፍ ኃላፊ አምባሳደር ተፈራ ሻዉል፤ ስምምነት ላይ እንዲረስ የተደረጉት ጥረቶች ያስገኟቸዉን ዉጤቶች ተግባራዊ ወደማድረጉ ሲደረስ በፖለቲከኞቹ መካከል መተማመኑ መጥፋቱ ዋና ችግር መሆኑ ነዉ ያመለከቱት።

Fahnen der IGAD-Mitgliedsländer
ምስል Yohannes G/Eziabhare

አምባሳደር ተፈራ እንደሚሉትም የደቡብ ሱዳንን ሁኔታ በሚመለከት በቀረበዉ ዘገባ መሠረት አብዛኞቹ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ማዕቀብ ሊጣልባቸዉ የሚችል ናቸዉ። ይህ ርምጃ ከመወሰዱም በፊት የችግሩ መንስኤዎች እነሱ እንደሆኑ ሁሉ መፍትሄዉንም ማምጣቱ በእጃቸዉ መሆኑን ነዉ አፅንኦት የሰጡት። የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ረዥም ጊዜ እንደተጠበቁ እና እድሉን ካልተጠቀሙበት ግን ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሌላ እቅድ እንዳለዉ ይፋ ማድረጉን አመልክተዋል።

የእቅዱ ምንነት አልተገለፀም ይበሉ እንጂ ከማዕቀብ የተለየ ሊሆን እንደማይችል ግምታቸዉን አልሸሸጉም። ከዋሽንግተን የወጡ የተለያዩ ዘገባዎችም ይህንኑ ነዉ የሚያጠናክሩት። ከዛሬ ጀምረዉ አዲስ አበባ ይገባሉ ተብለዉ የሚጠበቁት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች እስከነሐሴ 11ቀን ድረስ ከስምምነት መድረስ የግድ ይኖርባቸዋል ተብሎም ይጠበቃል። ቀደም ሲል ፕሬዝደንት ኦባማ ላስተላለፉት ማሳሰቢያ የጁባ ፖለቲከኞች በጎ ምላሽ አለመስጠታቸዉ ይታወቃል። አምባሳደር ተፈራ እንደሚሉት የሰላሙ እንቅፋት የሆኑት ጥቅማቸዉ የሚነካዉ ወገኖች ናቸዉ።

Barack Obama Addis Abeba Afrikanische Union Äthiopien
ኦባማ አፍሪቃ ኅብረት አዳራሽምስል Reuters/J. Ernst

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ባሳሰቡት መሠረት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በተሰጣቸዉ የጊዜ ገደብ ወደሚጠበቀዉ የሰላም ስምምነት ካልመጡ ከመሣሪያ ማዕቀብ አንስቶ፣ የመጓጓዝ ዕገዳን ያካተተ ማዕቀብና በዉጭ ያለ ንብረታቸዉ እንዳይንቀሳቀስ ማስቆምን የሚያካትት ሰፋ ያለ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። በፖለቲከኞቿ ዉዝግብ ጦርነትና ግጭት የደራባት ደቡብ ሱዳን ዜጎች ሁለት ሚሊየን ያህሉ ለስደት በበርካታ ሺዎች የሚገመቱት ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል። ከ800 ሺህ የሚልቁ ልጆችም በትምህርት ገበታ ላይ ከመገኘት ታግደዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ