1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ የተገረሰሰበት 20ኛ ዓመት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 18 2006

በደቡብ አፍሪቃ አፓርታይድ ከተገረሰሰበ በነገው ዕለት 20 ዓመት ይሆናል። የፀረ ዘር አድልዎው ትግል ታሪክ እና ስለ ሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/1Bof7

የዘር አድልዎ አመራር፣ አፓርታይድ ታሪክ በአንፃሩ የተዋጉ ሁሉ ታሪክ ነው። ውሁዳኑ የነጮች መንግሥት በደቡብ አፍሪቃ እአአ በ1920 ዎቹ ዓመታት ልክ ሥልጣን ከያዘ በኋላ የአፓርታይድን ሕግ ማስተዋወቅ ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ጥቁሮች፣ክልሶች፣ እንዲሁም፣ ነጮች ያልሆኑ አፍሪቃውያን በዚሁ ሕግ አንፃር ራሳቸውን በማደራጀት የነፃነት ትግላቸውን ጀመሩ። የዉሁዳኑ ነጮች መንግሥትም የተቃውሞ ሰልፎችን ለማስቆም የተደራጁትን ቡድኖች በማገድ እና መሪዎቻቸውንም በማሰር፣ ባጠቃላይ አስፈላጊ ባለው የኃይል ርምጃ ሁሉ በመጠቀም ተቃዋሚዎቹን እስከመግደል ድረስ ርቆ ሄዶዋል።ያም ቢሆን ግን ታዋቂው ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ለጨቋኞቻቸው የሰላም ጥሪ ነበር ያቀረቡላቸው።

Nelson Mandela tot
ምስል Picture-Alliance/Photoshot

« እጆቻችንን ለደበደቡን እንዘርጋ እና ሁላችንም ደቡብ አፍሪቃውያን መሆናችንን እንንገራቸው። ጥሩ ትግል አካሂደናል። አሁን ግን የድሮ ቁስል የሚሽርበት ጊዜ እና አዲሲቱን ደቡብ አፍሪቃ የምንገነባበት ጊዜም ነው እንበላቸው። »

ብዙዎች የአፓርታይድን ሥርዓት ለመገርሠሥ ያደረጉት ትግል ፍሬ ማስገኘቱ ኔልሰን ማንዴላ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት በሆኑበት እአአ በ1994 በግልጽ ታየ።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ለአንድ ምዕተ ዓመት ያህል የነፃነት ንቅናቄዎች በዘረኝነት እና በአግላይ በሆነው ሥርዓት አንፃር ትግል አካሂደዋል። በሥርዓቱ አንፃር የተነሱት ታጋዮች ማን ናቸው?

Kalenderblatt ANC Logo
ምስል AP


አፓርታይድ በይፋ የሀገሪቱ ሕግ የሆነው እአአ በ 1948 ዓም ነበር። ገዢው ብሔራዊ ፓርቲ ከዚያ በተከተሉት ዓመታት የዘር አድልዎ መርሁን በጉልህ አስፋፋ። ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ከከተሞች እየተገፉ እንዲወጡ ተደረገ፤ በነፃ የመዘዋወር መብታቸውንም ተነፈጉ፤ ከነጮቹ ጋ እንዳገናኙም ሲባል በተለዩ አውቶቡሶች እና መፀዳጃ ቤቶች እንዲጠቀሙም ተደርጓል።መጠቀም ተደርጓል፤ ይሁንና፣ በኔልሰን ማንዴላ የተመራ ወጣት የነፃነት ታጋዮች ትውልድ ይህንኑ ሥርዓት በጥብቅ በመቃወም የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ ፣ በምሕፃሩ « ኤ ኤን ሲ » የተባለውን የጥቁሮች ንቅናቄ ተቀላቀሉ። የታሪክ ምሁር ክርስቶፈር ማርክስ እነዚህን ወጣት ታጋዮች ከቀድሞው የታጋዮች ትውልድ የተለዩ እንደነበሩ ያስረዳሉ።

« ወጣቶቹ ታጋዮች እንደ ቀድሞዎቹ የ «ኤ ኤን ሲ» ታጋዮች በሚስዮናውያን ሰፈሮች ያደጉ አልነበሩም፤ ያደጉት በትላልቅ ከተሞች መዳረሻ ላይ ለጥቁሮች ብቻ በተቋቋሙ ከተሞች ውስጥ ነበር። እና ከሰፊው ጥቁር ሕዝብ ጋ የሚጋሩት ተሞክሮ ነበራቸው፤ ይኸውም በየቀኑ የሚያጋጥማቸው አድልዎ ነው። »

ዋነኛ የሆነው የጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ፀረ አፓርታይድ ንቅናቄ « ኤ ኤን ሲ » እአአ በ1955 ዓም ፀረ አፓርታይድ ቻርታ አወጣ። ይሁንና፣ የ « ኤ ኤን ሲ » ትግል እአአ በ 1960 ዓም ፖሊሶች በሻርፕቪል ተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ ተኩስ ከፍተው 69 ሰልፈኞች በገደሉበት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ባቆሰሉበት ርምጃቸው ትልቅ ምት ደረሰበት። ከዚሁ ግድያ በኋላ የውሁዳኑ ነጮች መንግሥት « ኤ ኤን ሲ » ን ሕገ ወጥ በሚል በማገድ መሪውን ኔልሰን ማንዴላን በዕድሜ ልክ እስራት ቀጣ። ይህ በንቅናቄው ስራ ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልነበር ክርስቶፈር ማርክስ ያስታውሳሉ።

« ከዚያ በኋላ « ኤ ኤን ሲ » ከደቡብ አፍሪቃ ይፋ የፖለቲካ መድርክ ከሞላ ጎደል ጠፋ ለማለት ይቻላል። ድርጅቱ ወደ ውጭ ሀገራት ለመሰደድ ተገደደ። « ኤ ኤን ሲ » በሀገሩ እንደገና ለማንሰራራት እና አዲስ መዋቅር ለመትከል በጣም ብዙ ጊዜ ነበር የወሰደበት። »

በ«ኤ ኤን ሲ » አካሄድ ላይ ወሳኙ ለውጥ የታየው እአአ እስከ 1976 ዓም ድረስ ነበር።

ከጆሀንስበርግ ከተማ ወጣ ብሎ በምትገኘው የሶዌቶ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥቁሮች ሕፃናት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁሉም በአፍሪካንስ ቋንቋ እንዲማሩ መወሰኑን በመቃወም አደባባይ በወጡበት ጊዜ ፖሊስ ከፍቶ 500 ሰው ገደለ። ከዚያ በኋላ በሀገሪቱ የቀጠለው ተቃውሞ እና መንግሥትም በዚሁ አንፃር የወሰደው ጠንካራ ርምጃ ደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት እንድታገኝ አድርጓል። የጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ዓመፅን እና የውሁዳኑን ነጮች መንግሥት ርምጃ ፎቶ አንሺው ፒተር ሙጋባና በቦታው በመገኘት ተመልክቶዋል።

« እአአ ሰኔ 16 ቀን በደቡብ አፍሪቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጓሜ የያዘ ቀን ነው። የአፓርታይድ ሥርዓት ለብዙ ዓመታት ተጠናክሮ እንዲቆይ ያስቻሉት ምሰሰዎች መሰነጣጠቅ የጀመሩበት ዕለት ነው። የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሰስ ሲጀምር ተመልክተናል። ደቡብ አፍሪቃ ተለወጠች፣ የድሮዋ መሆኗምም አቆመች። »

ሥርዓቱ ቀስ በቀስ መፈራረስ ሲጀምር በዚያን ጊዜ ፕሬዚደንት የነበሩት ፒተር ቪሌም ቦታ ሥልጣናቸውን ለፍሬድሪክ ቪሌም ደ ክለርክ እንዲያስረክቡ ግፊት አረፈባቸው። ደ ክለርክ የተሀድሶውን ለውጥ በማንቀሳቀስ ሥልጣን ከያዙ ከአራት ወራት በኋላ አዲስ ሕገ መንግሥት ወጣ፤ በሕግ የታገዱ ፓርቲዎችም ሕጋዊ ሆኑ። ይህን ተከትሎም ፕሬዚደንት ደ ክለርክ ቀጣዩን መግለጫ ሰጡ።

de Klerk Bekanntgabe Mandela-Freilassung 1990
ምስል picture-alliance/dpa

« መንግሥት፣ ሚስተር ማንዴላን፣ ካላንዳች ቅድመ ግዴታ ከእስር ለመፍታት ፅኑ ውሳኔ መድረሱን በግልጽ ለመናገር እወዳለሁ። »

ደ ክለርክ ይህን ካሉ ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት እስራት በኋላ ተፈቱ። ማንዴላ ከተፈቱ በኋላ ያሰቃዩዋቸውን እን በሕዝባቸው ላይ ግዙፍ በደል ያደረሱትን ሁሉ ይቅር ለማለት እና ሥልጣን ከያዙም በኋላ የእርቅ ሰላም እና የሀቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ለማቋቋም የወሰዱት ውሳኔአችው ለመላው ዓለም ትልቅ ትምህርት ነው የተወው። ማንዴላ እና ደ ክለርክ፤ ብሎም « ኤ ኤን ሲ » እና ብሔራዊው ፓርቲ የመራው የዉሁዳኑ ነጮች መንግሥት ባካሄዱዋቸው ተከታታይ ድርድሮች አፓርታይድ ቀስ በቀስ ተገረሰሰ። እአአ ሚያዝያ 27፤ 1994 ዓምም የዘር አድልዎሥርዓቱ በይፋ አከተመለት።

Nelson und Winnie Mandela
ምስል Getty Images/AFP

ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪቃ በተካሄደው የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባሸነፉበት ጊዜ የ « ኤ ኤን ሲ » መዝሙርም ይፋው የሀገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር እንዲሆን ተወሰነ።

በዚሁ ከ20 ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ በአፓርታይድ አንፃር የታገሉት ሁሉ ትግላቸው ፍሬ እንዳስገኘላቸው ቢረጋገጥም እና በሀገሪቱ አንዳንድ ሁኔታዎች ቢሻሻሉም፤ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ኔልሰን ማንዴላ ድህነት እና ዘረኝነት የሌለበት ሰላማዊ ህብረተሰብ ይፈጠራል በሚል ያሳደሩት ራዕያቸው ገና ገሀድ አልሆነም። እርግጥ፤ ብዙ ደቡብ አፍሪቃውያን፣ በተለይም ፣ ጥቁሮቹ፣ በኑሮዋቸው የጠበቁትን ለውጥ ገና ባለማግኘታቸው ቅሬታቸውን ሲገልጹ ቢሰሙም፣ በሀገራቸው ባለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ኩራት እንደሚሰማቸው ከመግለጽ አልቦዘኑም። የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ከጥቂት ጊዜ በፊት ስላለፉት 20 ዓመታት በሰጡት መግለጫ ላይ ደቡብ አፍሪቃ የተረጋጋች፣ ዴሞክራሲያዊ እና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት ሀገር መሆኗን ያረጋገጡበትን አነጋገር ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝብ የሚጋራው ነው።

Mandela Trauerfeier Johannesburg 10.12.2013
ምስል Reuters

ሀገሪቱን እአአ ከ1994 ዓም በማስተዳደር ላይ ባለው ገዢው የ«ኤ ኤን ሲ» ፓርቲ አሰራር ላይ ብርቱ ነቀፌታ የሚሰነዝሩት የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ዴዝመንድ ቱቱም እንኳን ሀገራቸው በፈጣኑ የዕድገት ጎዳና ላይ ከሚገኙት ቱርክን፣ ህንድና፣ ብራዚልና ፣ ናይጀሪያን ወይም ሩስያን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋ ስትነፃፀር፣ ያሳየችው የመሻሻል ሂደት የሚሞገስ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሬዚደንት ዙማ በሀገራቸው ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ 3,3 ሚልዮን ቤተሰቦች ከመንግሥት መኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል። እአአ በ1994 ዓም 60% የሚሆነው ሕዝብ ኮሬንቲ እና ውሀ ባልነበራቸው ጊዚያዊ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር የሚኖረው፤ ዛሬ ይኸው አሀዝ ቀንሶ አሁን 14% ከመቶ ብቻ ነው። ሕፃናት በጨቅላ ዕድሜአቸው በሚሞቱበት አንፃር የተጀመረው ትግል፤ ማይምነትን የማጥፋቱ፣ ትምህርት የሚያቋርጡትን ወጣቶች ቁጥር የመቀነሱ እና በኤድስ አስተላላፊው «ኤ ች አይ ቪ » aአንፃር የተጀመረው ትግል የተሳካ ውጤት እያስገኘ ነው። መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረቱ 16 ሚልዮን ሰዎች ከመንግሥት ርዳታ፣ አዘውትረውም፣ የሕፃናት ማሳደጊያ ድጎማ ያገኛሉ።

ይህም ቢደረግ ግን ባለፉት 20 ዓመታት የሕዝቡን ችግር ሁሉ ማስወገድ አልተቻለም፤በሀገሪቱ ግዙፍ ማህበራዊ ችግሮች አሉ። የስራ አጡ ቁጥር 25% ነው፣ ከጥቁሩ የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ መካከል 40%፣ ከሁለት ወጣት ጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያንም መካከል አንዱ ስራ የለውም፣። የሀገሪቱ ነጮች የበላይነትን ያበቃል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የመሬት ተሀድሶ፣ እንዲሁም፣ የኤኮኖሚው ዘርፍ ጥቁሮችን በከፍተኛ ቦታ እንዲያስቀምጥ መንግሥት ያደረገው ሙከራም የተጠበቀውን ውጤት እንዳላላስገኘ ነው የሚሰማው። ይኸው የመንግሥቱ ጥረት ከዩኒቨርሲትዎች እና ከፍትሑ አውታር የሚወጣውን የሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በተለይም፣ ነጮችን ያገለለ እና ለሙስና በር የከፈተ አሰራር እንደሆነ ነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በ«ኤ ኤን ሲ » ቅር የተሰኙ የቀድሞ ፀረ አፓርታይድ ታጋዮች የሚናገሩት።

ያም ቢሆን ህን ፕሬዚደንት ዙማ ለውዝግቦች ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት እና ተቻችሎ በሰላም ለመኖር ለሚፈልጉ ሁሉ በዘር አድልዎ ሥርዓት ስር ወድቃ የነበረችው እና አሁን ያንን ሥርዓት በመገርሰስ ሰላማዊውን ጎዳና በመከተል ላይ የምትገኘው ሀገራቸው አርአያ ልትሆን ትችላለች ብለው ያምናሉ።

ክርስትያን ሮማን/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ