1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ጎንደር ሐሙሲት ነዋሪዎች መንገድ ዘግተው ዋሉ

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2011

በአማራ ክልል፣ ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ሐሙሲት ከተማ ዛሬ መንገዶች ተዘግተው መዋላቸውን የከተማዋ ነዎሪዎች ተናገሩ፡፡ የደቡብ ጎንደር ዞን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ሐሙሲት ላይ ተዘግቶ የነበረው መንገድ ባለስልጣናቱ ከህብረተሰቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መግባባት ላይ በመደረሱ አመሻሹን ለትራፊክ ክፍት መሆኑን ለDW ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/3Eolk
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በደቡብ ጎንደር ሐሙሲት ነዋሪዎች መንገድ ዘግተው ዋሉ

የዐይን እማኞች ለDW እንደገለፁት የሐሙሲት ነዋሪዎች ዛሬ ከተማይቱ ወደ ባሕር ዳር እና ወደ ጎንደር የሚወስደውን አውራ ጎዳና ከጠዋት ጀምረው በድንጋይና በሌሎች ባዕድ አካላት በመዝጋት የትራንስፖርት ፍሰቱን አስተጓጉለውት ውለዋል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ ለDW እንደገለፁት የከተማው ነዋሪ እርምጃውን የወሰደው ከአመታት በፊት በመንግስትና በተባባሪ አካላት የተገነባው የከተማዋ የመጠጥ ውሀ አገልግሎት እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ቢጠየቅም ተግባራዊ መሆን ባለመቻሉ ነው ብለዋል። ነዋሪዎቹ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር የመንገድ መዝጋት እርምጃውን መውሰዳቸውንም ገልጸዋል። 

የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ችግሩን ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ የተናገሩት አቶ ጥላሁን ዛሬ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታትም የዞኑ አመራሮች ወደቦታው መሄዳቸው አስረድተዋል። አመሮቹ ከህብረተሰቡ ውይይት ካደረጉ በኋላ መግባባት ላይ በመደረሱ ተዘግቶ የነበረው መንገድ አመሻሽ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ለትራፊክ ክፍት መሆኑን ጠቁመዋል።  

ሐሙሲት በአማራ ክልል፣ ደቡብ ጎንደር ዞን የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ስትሆን ከክልሉ ርእሰ ከተማ ባሕር ዳር 30 ኪሎ ሜትር ያህል ትርቃለች፡፡

ዝርዝር ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ። 

ዓለምነው መኮንን

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ