1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የእርዳታ ሠራተኞች በፆታዊ ጥቃት ተከሰሱ 

ሐሙስ፣ መስከረም 21 2013

በዲ/ሪ/ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የተሰማሩ የዓለም የጤና ድርጅት እና ሌሎች የርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞች ከ50 በላይ በሆኑ ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት ፈፅመዋል ሲሉ ሁለት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አጋልጠዋል። የተ መድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ በበኩላቸው በቀረቡት ክሶች ላይ ሙሉ በሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። 

https://p.dw.com/p/3jIWk
Symbolbild | UN-Logo
ምስል Getty Images/AFP/N. Roberts

«ከ700 በላይ ክሶች የቀረቡት በኮንጎ ብቻ ነው»

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምስራቅ ቤኒ የኢቮላ ወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ማዕከል 51 የሚሆኑ ሴቶች በስራ ቅጥር ሰበብ በዓለም አቀፍ የእርዳታ ስራተኞች ወሲባዊ ጥቃት እንደፈፀሙባቸውና ይህንን የተቃወሙ ደግሞ የስራ ውላቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ተናግረዋል። ጉዳዩን በተመለከተ ቶማስ ሮይተርስ ፋዉንዴሽን እና ኒው ሂውማኒተሪያን የተባሉ ሁለት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባደረጉት ምርመራ ፤የዓለም ዓቀፉ ጤና ድርጅት፣የዓለም አቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ ፣ ኦክስፋም ፣ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን ፣ ወርልድ ቪዥንና ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅትን በመሳሰሉ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ወንዶች በማዕከሉ በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃትና እና በደል አድርሰዋል። 
ሴቶቹ በእርዳታ ድርጅቶቹ ውስጥ በምግብ አብሳይነት ፣በፅዳት ሰራተኝነት እና በማህበረሰብ አገልግሎት ሰጭ ሰራተኝነት የሚያገለግሉ ሲሆን፤ በቢሮዎች፣በሆስፒታሎችና እና በወንድ የእርዳታ ሰራተኞች ክፍል ውስጥ በመጠጥ ሀይል ጥቃት እንደሚፈፅሙባቸው ተናግረዋል። ጥቃቱ ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ የተፈጸመ ቢሆንም በሀፍረትና ስራችንን እናጣለን በሚል ፍራቻ ሴቶቹ የደረሰባቸውን በደል ለህግ አካላት አለማሳወቃቸዉን ገልፀዋል ፡፡ 
ሴንተር ኦላሜ ቡካቩ(COB) የተባለው የአካባቢው የሴቶች መብት ተሟጋች ድርጅት በሴቶቹ ላይ የደረሰውን ወሲባዊ ጥቃት ያወገዘ ሲሆን፤ይህ መሰሉ ጥቃት ሴቶች በነፃነት እንዳይሰሩና የሙያ እንቅስቃሴና ተሳትፎአቸውን የሚያግድ ነው ብሏል።ድርጅቱ ጉዳዩን ለማጋለጥ ከአለም የጤና ድርጅት ጋር ለመተባበር ዝግጁ ቢሆንም ለሴቶቹ ደህንነት ግን ስጋት እንዳለው የድርጅቱ ዳይሬክተር ቴሬስ ሜማ ማፔንዚ ገልፀዋል። 
«በብዙ ጉዳዮች እዚህ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ተጠቂዎች ጥበቃ የሌላቸው መሆኑን ተመልክተናል።ስለዚህ የወሲብ ትንኮሳና ጥቃት ሰለባዎችን በጭራሽ ይፋ አናደርግም።አንዳንድ ጊዜ ጥቃት አድራሾቹ በጣም ሀይለኞች በመሆናቸው ተጠቂዎቹ በፍትህ ከለላ ከማግኜት ይልቅ በተቃራኒው በራሱ በፍትህ ይወገዛሉ።» 
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ በበኩላቸው በቀረቡት ውንጀላወች ላይ ሙሉ በሙሉ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። 
የኢቦላ ወረርሽንን ለመቆጣጠር ከኮንጎ መንግስት ጋር ከ1 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን ያሰማራው የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ ተፈፀሙ በተባሉት ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ምርመራ መጀመሩን ገልጿል። 
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ፋዴላ ቻይብ እንደገለጹት «ይህን መሰል ድርጊት በየትኛውም ሰራተኛ ወይም አጋር ቢፈፀም አንታገስም» ብለዋል። 
ሌሎቹ የእርዳታ ድርጅቶችና የኮንጎ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ገልፀው እርምጃ ለመውሰድ ተጨማሪ መረጃና ምርመራ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። 
ይህ መሰሉ ጥቃት በልጆች፣ በወጣት ልጃገረዶችና በሴቶች ለዓመታት በአፍሪቃ ሀገራት በአንዳንድ የረድኤት ሰራተኞችና የሰላም አስከባሪ ሀይሎች ሲፈፀም መቆየቱን የሚያሳዩ መረጃዎች ቢኖሩም ጥቃት ፈፃሚዎቹ የውጭ ሀገር ዜጎች በመሆናቸው የተጠያቂነት ችግር መኖሩን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት የሂዩማን ራይትስ ዎች የመካከለኛው አፍሪካ ዳይሬክተር ሉዊስ ሙድጌ ገልፀዋል። 
«የተጠያቂነት ችግር አለ።የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ለሚፈጽሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች በብሄራዊ ህጎች ተጠያቂነት የላቸውም፡፡ ወንጀል ከፈፀሙ የሚጠየቁት በሀገራቸው ሕግ ብቻ ነው።» 
በአፍሪቃ ከጎርጎሪያኑ ከ2005 እስከ 2017 ዓ/ም ባሉት አመታት ብቻ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ሰራተኞች ላይ 2,000 የወሲብ ጥቃትና ብዝበዛ ክሶች መቅረባቸውን የአሶሸትድ ፕሬስ ዘገባ ያሳያል። ከ700 በላይ የሚሆኑት ክሶች የቀረቡት ደግሞ በኮንጎ መሆኑን የዜና ምንጩ አመልክቷል ። 
ፀሀይ ጫኔ 
ነጋሽ መሀመድ