1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በድሬዳዋ ውጥረት ሰፍኖ ውሏል

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2011

በድሬደዋ ከትናንት በስትያ ምሽት ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ሁለት ሰዎች መሞታቸውን የህክምና ባለሙያዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ግጭቱ በነበረባቸው በተለምዶ ደቻቱ እና አምስተኛ በሚባሉ የከተማይቱ ሰፈሮች ዛሬም ውጥረት ሰፍኖ ውሏል።

https://p.dw.com/p/3KmuD
Äthiopien Stadansicht Dire Dawa
ምስል DW/M. Teklu

በድሬዳዋ ውጥረት ሰፍኖ ውሏል

በድሬደዋ ከትናንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ በተለምዶ ደቻቱ እና አምስተኛ በሚባሉ ሰፈሮች የተፈጠረ ግጭት ትናንት እና ዛሬም በከፊል ውጥረት እንደፈጠረ ሲቆይ ለሰዎች ህይወት ህልፈትና ለአካል መቁሰል ምክንያት ሆኗል። ከመደበኛ የመስተዳድሩ ፖሊስ አባላት በተጨማሪ የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ተሳትፎም ጠይቋል - የተፈጠረውን ረብሻ ማረጋጋት።

በሁለቱ አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች መካከል ተፈጠረ በተባለ ግጭት የተቀሰቀሰው የአካባቢው ሁከትና ረብሻ በተለይ ትናንት ተባብሶ በመዋሉ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በዛሬው ዕለት አካባቢው ላይ የተፈጠረውን ግጭት ለመቆጣጠርና ለመከላከል የፀጥታ ኃይሉ ያልተቋረጠ ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆኑን ተመልክተናል። 

የድሬዳዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱረህማን አቡበከር በትናንትናው ዕለት በነበረው ግጭት አራት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የመጡ መሆናቸውንና አንደኛዋ ግን ህይወቷ አልፎ መምጣቷን ለDW ተናግረዋል። ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እየተከታተሉ ከሚገኙ ተጎጂዎች ክትትል ቢያስፈልጋቸውም በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር አብዱረህማን ተጎጂዎቹ ሙሉ በሙሉ በጥይት ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን አረጋግጠዋል። 

Äthiopien Stadansicht Dire Dawa
ምስል DW/M. Teklu

በሌላ በኩል የአካባቢው የዓይን እማኞች ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በተባራሪ ጥይት ህይወቱ ያለፈ አንድ ወጣት መኖሩን እና በዛሬው ዕለት የቀብር ስነስርዓቱ መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡ ይህን ጨምሮ የአስተዳደሩ ፖሊስ ስለተፈጠረው ግጭት መንስዔም ሆነ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት መረጃ እንዲሰጠን በስልክም ሆነ በአካል ያደረግነው ጥረት ባይሳካም አንድ የአካባቢው ነዋሪ ግን በአካባባቢው በተፈጠረው ግጭት ዝርፊያ መፈፀሙን ገልፀዋል።  በእርሳቸው ላይ የደረሰውን በአብነት ጠቅሰዋል። 

ነዋሪው እንደሚሉት በአካባቢው የተፈጠረው ግጭት መንስዔ "የብሄር ነው" በሚል የሚያነሱ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ምክንያቱ ግን እሱ አይደለም ብለዋል። የከተማዋ ዋነኛ የገበያ ቦታ የሆነውን የቀፊራ አካባቢ ባካለለው ግጭት ሱቆች ተዘርፈዋል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም ባንኮችን ጨምሮ የአካባቢው የንግድ እንቅስቃሴ ተገቶ ውሏል። የተፈጠረው ግጭት ተባብሶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት የሰጉ መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች በዛሬው ዕለት አንፃራዊ ሰላም ታይቶበት መዋሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል። አካባቢ ከትንሽ አለመግባባት ተነስቶ በፍጥነት ወደ ብሄር ግጭት የሚሸጋገረው የድሬዳዋ ችግር መነሻና መፍትሄ እንዴትነት ጥያቄ ውስጥ እንደገቡ ቀጥለዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

መሳይ ተክሉ 

ተስፋለም ወልደየስ 

እሸቴ በቀለ