1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ በፍራንክፈርት

ቅዳሜ፣ ጥር 2 2012

በጀርመን ነዋሪ የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለፈው ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በሞጣ ከተማ በመስጂዶች እና በሙስሊም ንብረቶች ላይ የተፈፀመውን የእሳት ቃጠሎ ጥቃት በማውገዝ በዛሬው ዕለት በፍራንክፈርት ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ::

https://p.dw.com/p/3W36N
Äthiopier in Deutschland verurteilen das Verbrennen von Moscheen in Äthiopien
ምስል DW/E. Fekade

በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ በፍራንክፈርት

በጀርመን ነዋሪ የሆኑ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ታኅሣሥ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በሞጣ ከተማ በመስጂዶች እና ሱቆች ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ በማውገዝ ዛሬ ከቀትር በኋላ በፍራንክፈርት ከተማ አደባባዮች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል:: ከዋናው የባቡር ጣቢያ ሃብትባኖፍ እስከ መዲናይቱ ዋና የገበያና የቱሪስቶች መናኸሪያ ሃቭትቫኸ ድረስ በዘለቀው በዚህ የተቃውሞ ጥቃቱን የሚያወግዙ ልዩ ልዩ መፈክሮች እና መልዕክቶችን ሰልፈኞቹ አሰምተዋል:: በመፈክሮቻቸው ካስተጋቧቸው መልዕክቶች መካከልም "መስጂዶችን አቃጥሎ መጨፈር አሳፋሪ እና ነውር ነው ! ፍትህ ለሞጣ ሙስሊሞች ፍትህ ለአክሱም ሙስሊሞች! የአማራ ክልል የፌደራል መንግሥት እና የሰላም ሚኒስቴር በሞጣ ጥቃት ላይ ባሳዩት ቸልተኝነት አፍረናል! የአማራ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ ወገንተኝነቱን ያቁም! የመስገጃ እና የመቀበሪያ ቦታዎች ለአክሱም ሙስሊሞች! ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ ! " የሚሉት ይገኙበታል::

በኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መስጂዶችን የማቃጠል እንዲሁም የኢስላም እና ሙስሊም ጠል ሰበካዎችን የማስፋፋት እኩይ ተግባራት እየተስተዋሉ ነው ያሉት ሰልፈኞቹ መንግስት እንዲህ ዓይነቱን አገርን ቀውስ ውስጥ ሊከት የሚችል እና የአብሮነት እሴቶችን የሚሸርሸር ሴራ በአፋጣኝ እንዲያስቆም የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር እና ድብቅ አጀንዳ ያላቸው የጥፋቱ  ኃይሎችም ተገቢውን የሕግ ቅጣት እንዲያገኙ ጠይቀዋል:: ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል ያነጋገርናቸው ለዶይቼ ቨለ "DW" እንደገለፁት በሞጣም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች በሙስሊሙ ዕምነት ላይ የተፈፀሙት አስነዋሪ ተግባራት ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ፤ የአገሪቱንም ሰላም የሚያናጋ ነው ብለዋል::

ከአሁን ቀደምም በተለያዩ አካባቢዎች መስጂዶችን የማቃጠል ,የሙስሊሙን ንብረት የመዝረፍና የማውደም የወንጀል ተግባራት ቢፈፀሙም የክልሉ መስተዳድርም ሆነ የፌደራል መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሕጋዊ እርምጃ አለመውሰዳቸው እንዳሳዘናቸው የገለፁት ሰልፈኞቹ ፤ ይህን የተገነዘቡት የጥፋት ኃይሎች በሞጣም በተቀናጀ እና በታሰበበት መልኩ በርካታ ሱቆችን ሆቴል እና መኪናዎችን ባጋዩበት ወቅት የፀጥታ አካላት ድርጊቱን በዝምታ መመልከታቸውም ሕዝበ ሙስሊሙን እንዳስቆጣው ተናግረዋል:: 

Äthiopier in Deutschland verurteilen das Verbrennen von Moscheen in Äthiopien
ምስል DW/E. Fekade

ኢትዮጵያውያን የክርስትና ዕምነት ተከታዮችም ለሙስሊም ወገኖቻቸው ያላቸውን አጋርነት ለመግለፅ እና በመስጂዶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማውገዝ በሰልፉ ላይ ተካፍለው ነበር:: "እኔ የኦርቶዶክስ አማኝ ነኝ :: እህቴን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰቦቼ አባላትም የሙስሊም ዕምነትን ይከተላሉ :: አሁን በኢትዮጵያ በየትኛውም እምነት ላይ እየተከሰተ ያለው ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ቤተሰብን ከቤተሰብ ጭምር የሚያጋጭ አገርንም ለአደጋ የሚያጋልጥ እጅግ አሳሳቢ ነው :: መንግሥት በአጥፊዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ እጃቸውን በሃይማኖት ግጭት ያስገቡ የመንግሥት አካላትም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማስገንዘብ ነው የመጣሁት" ሲሉ አንድ የሰልፉ ተካፋይ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል:: በቅርቡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት መግለጫ እግረ መንገዳቸውን በሞጣ በመስጂዶችና ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ሚዛኑን ያልጠበቀ ፣ የጉዳቱ ሰለባዎችን እና ህዝበ ሙስሊሙንም ያሳዘነ መሆኑን ሰልፈኞቹ በመግለፅ ዕርምት እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ጥቃቱ በተመለከተ ላቀረበው ጥያቄም የክልሉ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አሳስበዋል:: 

ከዚህ ሌላ በጀርመን የተለያዩ ከተሞች ነዋሪ የሆኑት እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በዛሬው የፍራንክፈርቱ ሰልፍ ማጠቃለያ ፤  የአማራ ክልል መንግሥት የተቃጠሉ መስጅዶችን እንዲገነባ፤ ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች ካሳ እንዲከፍል እና መልሰው የሚቋቋሙበትን መንገድ እንዲያመቻች ፤  አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የመገናኛ ብዙኃን እና የማኅበራዊ ድረ-ገፆች በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ላይ የሚያቀርቡትን የተዛባ ዘገባ እና ወገንተኝነት የተሞላው ዘገባ እንዲሁም የሚያደርጉትን የመከፋፈል እና የጥላቻ ዘመቻ በአስቸኳይ እንዲታረም ፤  የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ለአገር ሠላም እና ኅልውና አደገኛ ስለሆነ እጃቸውን ከሃይማኖት ጉዳይ እንዲያወጡ፤ መስጂዶች እና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንዲቆሙ ፤በአገሪቱ የኃይማኖት ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች እና የፖለቲካ ኃይሎችም ከዕኩይ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል:: የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክርቤት ጥቃቱ በተመለከተ ያቀረበው ጥያቄ ሕጋዊ እና አፋጣሽ ምላሽ እስኪያገኝም ሰላማዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለፁት::

እንዳልካቸው ፈቃደ

እሸቴ በቀለ