1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጃፓን፣ የምድር ነውጥና «ሱናሚ» ያደረሰው ብርቱ አደጋ

እሑድ፣ መጋቢት 4 2003

በ Richter መለኪያ 8,9 የደረሰ ብርቱ የምድር ነውጥና ከባድ የውቅያኖስ ማዕበል («ሱናሚ» )ክፉኛ በመታው ሰሜን ምሥራቅ ጃፓን ፣ ከ 10 ሺ በላይ ህዝብ ደብዛው እንደጠፋ መሆኑ እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/R8Xu
ተሽከርካሪዎቹን የገለባበጠዉ ሱናሚምስል dapd

የነፍስ አድኑ ተግባር እንደቀጠለ ሲሆን፣ ከዩናይትድ እስቴትስ፣ ጀርመን ፣ብሪታንያ፣ ሩሲያና ሌሎችም ሀገራት በዚህ ረገድ ትብብር እየተደረገ ነው። የጃፓኑ አደጋ ፤ በተለይ በኢንዱስትሪ የበለጸጉትንና ለኤሌክትሪክ አቅርቦት በአቶም ኃይል ምንጭ የሚገለገሉትን ሀገራት ማሳሰቡና ማነጋገሩ አልቀረም።

ተክሌ የኋላ

የኑክልየርን ቦንብም ሆነ የአደገኛ የአቶም ጨረርን ምንነት በዓለም ታሪክ ፣ የጃፓናውያንን ያህል ግንዛቤ ያለው የለም። ለዚህ ምሥክሮቹ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ፤ እ ጎ አ ነሐሴ 6 እና 9 , 1945 ፣ በአቶም ቦምብ የተመቱት ሒሮሺማና ነጋሳኪ የተባሉት ከተሞች ናቸው። በሒሮሺማ ፤ ያኔ፣ 92,000 ያህል ህዝብ ወዲያው እንደቅጠል ሲረግፍ፣ 130,000 የሚሆኑ በ 5 ወራት ውስጥ እየተሠቃዩ ህይወታቸው አልፏል። በነጋሳኪም 73 ሺ ወዲያው ሲሞቱ74,909 ነበሩ የቆሰሉት። ከ 66 ዓመት ገደማ ወዲህ ጃፓን በጦነት ሳይሆን ፤ጠ/ሚንስትር ናዖቶ ካን ባሰሙት ንግግር ላይ እንዳሉት ተፈጥሮ ባስከተለው የምድር ነውጥና ኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል ሳቢያ አሰቃቂ አደጋ ደርሶባታል።

በባህር ወለል በደረሰ የምድር ነውጥ ሳቢያ የተቀሰቀሰ እጅግ ኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል፣በሰሜን ምሥራቅ ጃፓን፣ ህንጻዎችን፤ መኖሪያ ቤቶችን ፣ ደርምሷል፤ ጀልባዎችን፤ መርከቦችን ፣ አኤሮፕላኖችንና አውቶሞቢሎችን እያገላበጠ በመውሰድ ከጥቅም ውጭ አድርጓል።በሰውና ንብረት ከደረሰው ቅጽበታዊ ጥፋት ባሻገር መላውን ዓለም ያስፈራውና በማነጋገርም ላይ ያለው ፣ ከቶኪዮ በስተሰሜን ምሥራቅ 240 ኪሎሜትር ራቅ ብሎ በሚገኘው ቦታ እንደተፈራው፣ የፈነዳው የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ነው። የፓፓን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ፤ፉኩሺማ ላይ በአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሩ ላይ የደረሰው ፍንዳታ ደረጃው 4 በመሆኑ ፤ የአደጋው መጠን ፤ በአውታሩ ዙሪያ ያለውን አካባቢ ብቻ የሚመለከት ነው ። በቸርኖቢል፣ ዩክሬይን፤ በሚያዝያ ወር 1978 (ከ 25 ዓመት በፊት)የፈነዳው የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ፣ የአደጋው ደረጃም ሆነ መጠን 7 እንደነበረ ነው የሚነገረው። የፉኪሺማው የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ፍንዳታ የመንግሥት ቃል አቀባይ ዩኪቶ ኤዳኖ እንደሚሉት ከሆነ ፣ ከኑክልየር ፍንዳታ ጋር የሚመሳሰል አይደለም።

«በአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሩ ዙሪያ ፤ ከፍንዳታው በኋላ የነበረው የአቶም ጨረር እንደገና ቀንሷል። እጅግ አስከፊ ጥፋት እንዳይደርስም ከጥቅም ውጭ የሆነውን አቶም የሚብላላበትን ጋን ፤ ለማቀዝቀዝ በውቅያኖስ ውሃ እንዲሞላ ተደርጓል። ይህ እርምጃ እንዲወሰድ ያደረጉት የኤኮኖሚ ሚንስትሩ ካይዳ ናቸው»።

ለሰላማዊ አገልግሎት እየተባለ የሚተከለው የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ምንም ዓይነት ጥንቃቄ ቢደረግለት፤ በጃፓን የደረሰው ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ ካጋጠመ፣ መቶ በመቶ እስተማማኝ ሊሆን እንደማይችል አሁን፤ ጀርመንን የመሳሰሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሃገራትን ማነጋገሩ፣ ማከራከሩ አልቀረም። የጀርመን መራኂተ-መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል ትናንት ማታ እንዲህ ነበረ ያሉት።

«በጃፓን የደረሰው የኑክልዬር አደጋ ፤ የተለያዩ እርስ-በርስ የሚጋጩ መግለጫዎች ቢሰጡበትም፣ አንድ ፍጹም የማያከራክር ጉዳይ አለ። በጃፓን የደረሰው ሁኔታ ለዓለም አንድ እንከን ነው። ብዙ ሰዎች ፤ እኔም የምለው ነው። በጣም ከፍተኛ ደረጃ ባለው አደጋን በሚከላከል አስተማማኝ ዘዴ የምትሠራ ፣ ጃፓንን የመሰለች ሀገር ፤ በምድር ነውጥና ማዕበል ሳቢያ ይህን አደጋ መግታት ካልቻለች፤ መላው ዓለም ፤ አውሮፓ፤ እዚህም ላይ ጀርመን ፣ ከፍተኛ አደጋ የመከላከል ዘዴ አለኝ ብላ በቸልታ የምትመለከተው ጉዳይ አይሆንም።»

በአቶም ጉዳይ ሊቅ የሆኑት ፤ የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ድርጅት (ግሪንፒስ) ባልደረባ ቶቢያስ ሪድል፤ በጃፓን የምድር ነውጥ ሳቢኢ በአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር የደረሰውን አደጋ አስመልክተው እንዲህ ነበረ ያሉት።

«ባለፉት ሰዓቶች፣ ሁኔታው የሚያረጋጋ ሳይሆን፣ እያሠጋ መምጣቱን ነው የምንገነዘበው።

ሁኔታውን በፍጹም መቆጣጠር አልተቻለም። የሚመስለው፣ በሁለት የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች፤ የአቶም ግለትና የፍንዳታ አደጋ እንደሚያጋጥም ነው። የውቅያኖስ ውሃ በመቸለስ፣ የፉኩሺማውን፣ አንደኛውን፣ የአቶም ኃይል ማመንጫ ጋን ለማቀዝቀዝ እየተሞከረም ነው። የሚሣካ ስለመሆኑ ማንም በእርግጠኛት መናገር አይችልም ። እስከመቼ ሁኔታው በአንዲህ ይቀጥላል? መቼ የፍንዳታው አደጋ ያጋጥማል?፤ እስካሁን የሚታውቅ ነገር የለም።»

ተክሌ የኋላ

አዜብ ታደሰ