1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን እና ፈተናቸው

ዓርብ፣ መስከረም 26 2010

ሳውዲ አረቢያ ምንም እንኳን  ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ሀገሯን ባስቀመጠችው የጊዜ ገደብ ለቀው ካልወጡ ርምጃ በአንጻራቸው እንደምትወስድ ብታስጠነቅቅም፣ አሁንም ድረስ ሀገሪቷን ለቀው ያልወጡ ብቻ ሳይሆን እንደ አዲስ በህገወጥ መንገድ የሚገቡም አሉ።

https://p.dw.com/p/2lGYR
Illegale aus Äthiopien in Saudi-Arabien
ምስል DW/Sileshi Sibiru

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

ሳውዲ ዐረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ሀገሯን በ90 ቀናት ለቀው እንዲወጡ ባለፈው  ትዕዛዝ ማስተላለፏ ይታወሳል። ይኸው አዋጅ  ለሁለት ጊዜ የተራዘመ ሲሆን፣  እስካሁን ሀገሯን ለቀው ባልወጡት ላይ ሳውዲ ዐረቢያ ምን ዓይነት ርምጃ እንደወሰደች ወይም እንደምትወስድ በይፋ አይታወቅም። በዚህም የተነሳ ስጋት ያደረባቸው በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳውዲ የገቡ ስደተኞች ሀገሪቷን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ግን አሁንም በህገወጥ መንገድ ወደ ሳውዲ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም። ይህን በኢትዮጵያ አጎራባች ሀገር ጅቡቲ የሚኖሩት እና የሚሰሩት ኑርየ በየዕለቱ የሚታዘቡት ነገር ነው። « በቀን ቢያንስ ከ 80 ሰው በላይ ሲጓዝ አያለሁ» ይላሉ። የጅቡቲውን ነዋሪ ይበልጥ የሚያሳስባቸው ግን በስደተኞቹ ላይ ሲፈጸም የሚያዩት እንግልት እና በደል ነው። ሌላው ደግሞ  በሴቶች ላይ የሚፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ነው።ኑርየ እድል ገጥሟቸው ካነጋገሩዋቸው ስደተኞች ያገኙት ምላሽ እሳቸው እንደሚሉት የሚያስገርም ነው። « ከሳውዲ አረቢያ ተይዘው ኢትዮጵያ ገብተው ወር ሳይሞላቸው ተመልሰው በጅቡቲ የሚሰደዱት ናቸው።»

ከጅቡቲ በመነሳት በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል አድርጎ የመን ከገባ በኋላ  ሳውዲ አረቢያ ከገቡት ስደተኞች መካከል  አህመድ አንዱ ነው። በስደት ጉዞ ወቅት ሴት ስደተኞች በግዳጅ እንደሚደፈሩ አይቷል። « ሚስቱ ወይም እህቱ ያልሆነች ሴት ሊተባበር እና ሊያግዝ የሚሞክር ማንም የለም።» ይላል። የስደቱ ጉዞ ኢትዮጵያ እያለን ሲወራ እንደሰማነው ቀላል አልነበረም፣ እንኳንስ ለሴቶች ለወንዶችም ሳይቀር ከባድ ነው። ብዙ መከራ አለው ይላል ከሀገሩ የተሰደደው አህመድ ያለፈበትን ጉዞ መለስ ብሎ ሲያስታውስ።

Saudi Arabien Dschidda
ህገ ወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሳውዲ የሚገቡት ለደላላ ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ ነው።ምስል Getty Images/AFP/K. Saad

አህመድ የህገ ወጥ ጉዞ ለደላሎች ገንዘብ ከፍሎ በማለፍ ብቻ የማያበቃ መሆኑን፣ ችግሩ በራሱ ላይ ሲደርስ ነበር ያወቀው። አህመድ ለደላሎች  ገንዘብ የከፈለው ከቤተሰቦቹ ወስዶ ነው። ገንዘቡን አምጡ ያለው በአጋቾች ከተያዘ በኋላ ነው።karta

አለም እንዲሁ በጅቡቲ በኩል ወደ ሳውዲ አረቢያ ከገቡ ሴት ኢትዮጵያውያን አንዷ ናት። መጀመሪያ ላይ በህጋዊ መንገድ ለስድስት ዓመታት ዱባይ ከኖረችና ከሰራች በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ነበር። አማራጭ ስላጣው ነው ወደ ሳውዲ በባህር የተመለስኩት ትላለች። አለም በጎዞ ላይ ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈፀምም ታዝባለች።  በወሲብ ከመደፈር ጥቃት ያተረፏት አብረዋት በስደት ጉዞ ላይ የነበሩ ወንዶች ናቸው።

Brasilianische Hausmädchen Haushälterinnen
በርካታ ሴት ኢትዮጵያውያን ሳውዲ ሲደርሱ በቤት ሰራተኝነት ይቀጠራሉምስል Getty Images/AFP/Y. Chiba

ለረዥም ጊዜ በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩት አቶ ሙሉጌታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ሲገቡና ሲወጡ ተመልክተዋል። ከወንዶች ይበልጥ በተለይ በሴት ስደተኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንደሚያመዝን ያብራራሉ።በአጠቃላይ መንገድ ላይ ስደተኞች የሚገጥማቸው ችግር እንዳለ ሆኖ አሁን ደግሞ እዚህ ሲገቡ ያለው ሁኔታ ተቀይሯል ይላሉ አቶ ሙሉጌታ። ምክንያቱም የሳውዲ አረቢያ ህግ በመጠናከሩ ነው። ዜጎች የሚሰደዱበት ድርጊት እስካሁን ድረስ ያልቆመበት ምክንያት እንደ አቶ ሙሉጌታ አስተያየት፣ በአንድ በኩል ስደተኞቹ ስደትን ቀላል አድርገው መመልከት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሳውዲ አረቢያ ህጋዊ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠችውን የጊዜ ገደብ በየጊዜው ማራዘሟ ነው።

በጅቡቲ በኩል እያደረጉ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሚገቡ ስደተኞች በመንገድ ላይ ስለሚገጥማቸው ፈተና የቃኘው ይህን ዘገባን በድምፅ መስማት ይችላሉ።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ