1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጋምቢያ የተጠናከረው ተቃውሞ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 18 2008

በምዕራብ አፍሪቃዊቱ ጋምቢያ አንድ የተቃዋሚ ቡድን አባል በወህኒ ቤት ሕይወቱ አልፋለች የተባለበት ድርጊት በሀገሪቱ ብርቱ ቁጣ ቀስቅሶዋል። የሀገሪቱ ፀጥታ ኃይላት ባለፈው እሁድ በሰበቡ የተካሄደውን ተቃውሞ በኃይል በትነውታል።

https://p.dw.com/p/1IZd7
Gambia Proteste in Banjul
ምስል Getty Images/AFP/Stringer

[No title]

ከሀያ ሁለት ዓመት ወዲህ በስልጣን ላይ የሚገኙት የጋምቢያ ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜ የሚመሩት መንግሥት የሚከተለው የማያፈናፍን ፖሊሲ፣ የመብት ተሟጋች ቡድኖች እንደሚሉት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የጋምቢያ ዜጎችን ለስደት እየዳረገ ነው።


ብዙ የጋምቢያ ዜጎች ሀገራቸውን ሲያቆላምጧት «የምትስቀው የአፍሪቃ ጠረፍ» እያሉ ይጠሩዋታል፣ ምንም እንኳን በትንሿ የአፍሪቃ ሀገር ብዙም የሚያስቅ ነገር ባይኖርም። ሰሞኑን ከጋምቢያ እንደተሰማው፣ በመንግሥቱ ላይ ጠንካራ ትችት በመሰንዘራቸው ይታወቁ የነበሩት የተቃዋሚው የተባበረው ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል ሶሎ ሶንዴንግ በእስራት በነበሩበት ወህኒ ቤት ውስጥ መሞታቸው ጋምቢያን ካለፉት ጥቂት ጊዜያት ወዲህ የመገናኛ ብዙኃን ትልቅ ርዕስ አድርጓታል። ሶንዴንግ ከሌሎች የመብት ተሟጋቾች ጋር ባንድነት በመሆን ሀሳብን በነፃ ለመግለጹ መብት እና በምርጫው ሕግም ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ በመጠየቅ ከአስር ቀናት ግድም በፊት በመዲናይቱ ባንጁል አቅራቢያ በወጡበት ጊዜ ነበር የታሰሩት። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሶንዴንግ በፖሊስ ምርመራ ስር እንደነበሩ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ ሕይወታቸው ማለፏ ሂደቶች እየተበላሹ ሊሄዱ የሚችሉበትን ስጋት መፍጠሩን የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የምዕራብ አፍሪቃ ተመራማሪ ዛብሪና ማሃታኒ አመልክተዋል።
« ጋምቢያ ውስጥ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ባጠቃላይ ትችት በሚሰነዝሩ አንፃር ከብዙ ጊዜ ወዲህ እየተፈፀሙ ካሉት በደሎች መካከል የሰሞኑ አሳዛኝ ሁኔታዎች ጥቂቶቹ ናቸው። በአምነስቲ ዘገባ መሰረት፣ ጋምቢያ ከብዙ ዓመታት ጀምራ የሀሳብ ነፃነትን ታፍናለች። ይኸው የሶንዱንግ ሞትም የጋምቢያ መንግሥት በሚቀጥለው ታህሳስ ወር ምርጫ ከመደረጉ በፊት በነፃ ድምፆች አንፃር ጭቆናውን ያጠናክራል በሚል በተለይ አሳስቦናል።
እጎአ በ1994 ዓም የጦር ኃይሉ ባካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የያዙት እና ከዚያን ጊዜ ወዲህ
የጭቆና አገዛዛቸውን ያስፋፉት ፕሬዚደንት ያህያ ጃሜ፣ ሥርዓተ ዴሞክራሲን በመፃረር፣ በታህሳሱ ምርጫ ለአምስተኛ ጊዜ በተወዳዳሪነት የመቅረብ እቅድ አላቸው። ባለፈው ታህሳስ ወር በድንገት እስላማዊውን መንግሥት ያወጁት ጃሜ፣ የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሀይንሪኽ ቤርግሽትሬሰር እንደሚሉት፣ በወቅቱ የሚመሩት አሸባሪ መንግሥት ነው።
« በወቅቱ በጋምቢያ እየታየ ያለው ከዴሞክራሲ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። እንዲያውም፣ በዘፈቀደ የሚወሰደውን ርምጃ ስንመለከት፣ በዚያ ያለው መንግሥት ከቀድሞው የስታሊን አገዛዝ ጋር የሚመሳሰል ነው። ጃሜ በ22 ዓመቱ የስልጣን ዘመናቸው ሀገሪቱን እንደሻቸው ሲገዙ ይታያል። ለርሳቸው እንዳመቸም በየጊዜው ሚንስትሮችን አባረው በአዲስ ይተካሉ። ገዢው ፓርቲያቸው በምክር ቤት ሁሌ አብላጫውን ድምፅ እንደያዘ ነው፣ በአንድ ወቅትም ፓርቲያቸው ሕገ መንግሥቱን ማሰቀየር እና ያሰኛቸውን ማድረግ ያስቻላቸውን ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ይዞ ነበር። »
ግብረ ሶዶማውያንን በይፋ የሚያሳድዱት ወይም ኤድስን የመፈወስ ችሎታ እንዳላቸው የሚነገሩት የ50 ዓመቱ ጃሜ መሀን ሴቶች ልጅ እንዲወልዱ የሚያደርግ መድሀኒት ማግኘታቸውንም ይገልጻሉ፣ ይሁንና፣ የጋምቢያ ሕዝብ ይህን ሳይሆን መሪው ለሀገሪቱ ችግሮች መፍትሔ እንዲያስገኙለት ነው ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የሚጠብቀው። በተመድ ግምት መሰረት፣ ከሁለት ሚልዮኑ የጋምቢያ ሕዝብ መካከል ከግማሽ የሚበልጠው በከፋ ድህነት ውስጥ ነው የሚገኘው። ከሌሎች ሀገራት ሲነፃፀር የጋምቢያ የትምህርት፣ የሕዝቧ አማካይ የዕድሜ ዘመን ወይም የነፍስ ወከፍ ገቢ በጣም የወደቀ ነው። በሀገሪቱ ኢንዱስትሪ አልተስፋፋም፣ ሕዝቡም በግብርና እና በቱሪዝም ላይ ጥገኛ ነው። ጦርነትም ሆነ ተላላፊ በሽታ የሌለባት ጋምቢያ የቱሪስት መስሕብ ናት። ይሁን እንጂ፣ ብዙዎቹ ዜጎችዋ ከሀገር መውጣት ነው የሚፈልጉት። ከምዕራብ አፍሪቃ የሰሀራ በረኃን እና የሜድትሬንየን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮጳ ከሚፈልሱት በተለይ በ18 እና በ30 ዓመት መካከል ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ብዙዎቹ ጋምቢያውያን ናቸው። ለምሳሌ፣ በጀርመን የፍልሰት እና ስደት ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ዘገባ መሰረት፣ በ2012 ዓም ወደ ጀርመን የመጡት 244 ነበሩ በ2015ዓም 3,110 ደርሰዋል። ዛብሪና ማሃታኒ እንደሚሉት፣ የተሻለ የወደፊት እድል ያለማግኘቱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የነገሠው የፍርሀት ድባብም ጋምቢያውያኑ ወጣቶች ሀገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል። ይህን ገሀድ አምነው ለመቀበል የማይፈልጉት ፕሬዚደንት ጃሜ የሚሰደዱትን ጋምቢያውያን የማይረቡ ወይም መጥፎ ሙስሊሞች ብለው ነው የሚጠሩዋቸው። ይሁን እንጂ፣ ከአስር ቀናት ግድም በፊት አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎች የታሰሩበት፣ እንዲሁም፣ በሀገሪቱ ምን ያህል የመንግሥት ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾችም በእስራት እንደሚገኙም ሆነ እንደ ሶሎ ሶንዴንግ የሞተ ሰው ስለመኖር አለመኖሩ በወቅቱ በውል ያልታወቀበት ድርጊት የጋምቢያ ዜጎች የሚገኙበትን ከባድ ሁኔታ አሳይቶዋል። የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙን በሶሎ ሶንዴንግ ሞት ማዘናቸውን ገልጸው ፣ ገለልተኛ አካል ጉዳዩን እንዲያጣራ እና በእስራት የሚገኙ ተቃዋሚዎች በጠቅላላ እንዲፈቱ አሳስበዋል።

Deutschland Gambische Flüchtlinge
ምስል picture-alliance/dpa/J. Büttner
Elfenbeinküste Präsident Yahya Jammeh in Yamoussoukro
ምስል Getty Images/AFP/I. Sanogo
Gambia Proteste in Banjul
ምስል Getty Images/AFP/Stringer

ዩሊያ ሀን/አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ