1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመናውያኑ ግድያ ራሱን "እስላማዊ መንግሥት" ብሎ የሚጠራው ታጣቂ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 8 2009

ዓርብ ሁለት እንስት ጀርመናውያን በግብፅ በስለት በተፈጸመ ጥቃት ተገድለዋል። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር ጥቃቱ በውጭ አገር ዜጎች ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን እንደማይቀር ገልጧል።

https://p.dw.com/p/2gb3s
Ägypten Messerattacke in Hurghada
ምስል Reuters/M. Aly

ሁለት ሴት ጀርመናውያን ትናንት ግብፅ ውስጥ በስለት ለተገደሉበት ጥቃት ኃላፊነት ወሳጁ ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን እንደሆነ ፍንጭ ተገኘ። ጥቃት ፈፃሚው በተቻለው መጠን የውጭ ዜጎችን እንዲገድል ትዕዛዝ ተላልፎለት ነበር ይላል የጀርመን ዜና ድርጅት ከካይሮ ባገኘው መረጃ። በዚህም መሰረት ጥቃት ፈፃሚው የ 27 ዓመቱ አብደል ራህማን ነው። ግብፃዊው ሁርጋዳ በተሰኘ የመዝናኛ ስፋራ ሁለት ሴት የጀርመን ሀገር ጎብኝዎችን በስለት ወግቶ ሲገድል፣ ሌሎች አራት ሰዎችን አቁስሏል። ግለሰቡም የዛው ዕለት በቁጥጥር ስር ውሎ ቃሉን እንዲሰጥ ተደርጓል። በዚህም መሰረት በአካባቢዉ የነበረዉን ባሕር በዋና አቋርጦ ሐገር ጎብኚዎቹ ወዳሉበት ሆቴል በመግባት ሰዎችን በስለት ሊገል እና ሊያቆስል ችሏል። ጥቃቱን ሲፈፅም የተመለከተ አንድ የሱቅ ባለቤት ሊገላግል ሲሞክር ጥቃት ፈፃሚው አላማው ግብፃዊያንን ማጥቃት እንዳልሆነ መግለፁን የዓይን እማኙ የፖሊስ ገልጸዋል።"ካሰባሰብንው መረጃ ጥቃቱ በውጭ አገር ዜጎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ተረድተናል" ያለው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒሥቴር በጥቃቱ ማዘኑን፤መደንገጡን እና መቆጣቱን ገልጧል። ጀርመናውያኑ ላይ የተፈጸመው ግድያ የተሰማው በግብፅ የጊዛ ከተማ አምስት ፖሊሶች በጥይት ተመትተው ከተገደሉ በኋላ ነው። 

በሌላ በኩል የግብፅ የሀገር ደህንነት ባለስልጣናት ተወንጃዩ ይህንን ጥቃት የፈፀመበት ምክንያት እስካሁን ግልፅ አይደለም፤ ከመላምት ተቆጠቡ ሲሉ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።   

ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ