1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአድማው ጋር በተያያዘ ወጣቶች ታስረዋል ተብሏል

ማክሰኞ፣ የካቲት 13 2010

በጎንደር ከተማ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ መዋሉን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ አድማው ነገም እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ሰኞ ዕለት የስራ ማቆም አድማ የተካሄደባት ባህርዳር ከተማ ከትላንት አመሻሽ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሳለች ተብሏል፡፡

https://p.dw.com/p/2t0l1
Äthiopien Notstände in Amhara
ምስል DW/J. Jeffrey

ከአድማው ጋር በተያያዘ ወጣቶች ታስረዋል ተብሏል

በአማራ ክልል ከሰኞ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ እንዲደረግ በማህበራዊ ድረገጾች መልዕክቶች መሰራጨታቸውን ተከትሎ በጎንደር ከተማ ትላንት የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ዛሬም ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በከተማይቱ የአገልግሎት ሰጪዎች ዛሬም ተዘግተው መዋላቸውን፣ ትራንስፖርትም እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ 

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ የንግድ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች አገልግሎት ሰጪዎች ተዘግተው መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ የህዝብ ማጓጓዣዎች በመንገድ እንደማይታዩ የገለጹት እኚሁ ነዋሪ ባሉበት አካባቢ ያስተዋሉትን እንዲህ ይገልጹታል፡፡ 

“አሁን መሀል ከተማ ፒያሳ እምብርቱ ላይ ነው ያለሁት፡፡ መስቀል አደባባዩ ላይ ማለት ነው፡፡ ባለሁበት ቦታ የስራ ማቆም አድማው እንደቀጠለ ነው፡፡ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም፡፡ ሰዎች ጥግ ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ ከፖሊሶች ጋር ተፋጠዋል፡፡ ሊከፍት ፍቃደኛ የሆነ ምንም ዓይነት ድርጅት የለም፡፡ የትራንስፖርት ሰጪ ነገሮች የሉም፡፡ ጋሪዎች ናቸው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ጋሪዎች ደግሞ ያው የዕለት ፍጆታቸውን፣ ለፈረሶቻቸው የሚሆን ምግብ ማግኘት ስላለባቸው፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ማለፍ በማይችሉባቸው አስፋልት መንገዶች ሁሉ እየተጓጓዙ ነው ያሉት” ይላሉ፡፡

ማንነታቸው እንዳይነገር የሚሹ ሌላኛው የጎንደር ነዋሪም ተመሳሳይ የትራንስፖርት ችግር በከተማይቱ አስተውለዋል፡፡ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ከትላንት ጀምሮ ከአገልግሎት መታቀባቸውን ይገልጻሉ። የዛሬው የስራ ማቆም አድማ በጎንደር ከተማ በሞላ መተግበሩን ሶስተኛው የከተማይቱ ነዋሪ ያስረዳሉ፡፡

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የከተማይቱ ነዋሪዎች የስራ ማቆሙን አድማ ማን እንደጠራው በግልጽ እንደማይታወቅ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ህብረተሰቡ እርስ በእርስ በመነጋገር መረጃውን እንደተቀባበለ ይስማማሉ፡፡ የስራ ማቆም አድማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመቃወም የተጠራ ነው በሚል በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተሰራጨው መረጃ ትክክል አይደለም ሲሉ የመጀመሪያው ነዋሪ ያስተባብላሉ፡፡ ከአድማው በስተጀርባ ያሉ ጥያቄዎችንም ያብራራሉ፡፡ 

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

በጎንደር ዛሬ አድማ ቢኖርም ከተማይቱ ምንም ችግር አለመፈጠሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ አባላት በከተማይቱ በብዛት እንደሚታዩም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የከተማይቱ አስተዳደር ሰራተኞች ከትላንት ጀምሮ ስራ ባቋረጡ የንግድ ተቋማት እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ በቀይ ቀለም የኤክስ ምልክት ሲያደርጉ እንደተመለከቱም እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመንግስት መስሪያ ቤቶችም ስራ ያልገቡ ሰራተኞችን ስም እየዞሩ የሚመዘገቡ ሰዎች ነበሩ ባይ ናቸው፡፡ ከአድማው ጋር በተያያዘ ትላንት እና ዛሬ ወጣቶች እንደታሰሩም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ነዋሪዎች የስራ ማቆም አድማው ነገም እንደሚቀጥል መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡

በአድማው  የመጀመሪያ ቀን ተሳትፋ የነበረችው የአማራ ክልል መቀመጫ ባህር ዳር ከትላንት ምማሻውን ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ተዘግተው እንደሚስተዋሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ጠቁሟል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉ አንድ የከተማይቱ ስለ ባህር ዳር የትላንት እና ዛሬ ውሎ አብራርተዋል፡፡ 

የጎንደር የስራ ማቆም አድማን በተመለከተ ምላሽ ለማግኘት ወደ ከተማይቱ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ብንደውልም የሚመለከታቸው አካላት ቀኑን ሙሉ ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተገልጾልናል፡፡ የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንንም በተመሳሳይ ምክንያት ልናገኛቸው አልቻልንም፡፡ 

ዝርዝር ዘገባውን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ 

ሂሩት መለሰ