በጎ ፍቃደኛ የእግር ኳስ አሰልጣኞች
ዓርብ፣ ኅዳር 6 2006እግር ኳስ ኃብታም ወይም ደሀ ፤ ጥቁር ወይም ነጭ አይልም። የቻለ በስታዲዮም ያልቻለ በአፈር ሜዳ ላይ፤ ያለው በመደበኛ የሌለው በጨርቅ ኳስ ይጫወታል።
ለእግር ኳስ በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተርና የሚወደድ ጨዋታ ነው። ክርስትያን ማሞ የእግር ኳስ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚያውቀውን የእግር ኳስ አጨዋወት ደንብ እና ስልትን ለሌሎች ማካፈል ከወሰነ አንድ አመት ሆኖታል። ክርስትያን በአዲስ አበባ መኖር ከጀመረ ሰባት አመቱ ነው። ከዛ በፊት ወላጆቹ በስራ ምክንያት በተለያዩ ሀገራት መኖር ስለነበረባቸው በአምስት ሀገራት ነው ያደገው።
ክርስቲያን ሌሎች ወጣቶችን የእግር ኳስ ጨዋታ ለማሰልጠን ከዓመት በፊት ሲነሳሳ ሀሳቡን ያጋራው ለትምህርት ቤት ጓደኛው ቀና ሳምሶን ነው። ቀና ዛሬ ከክርስትያን ጋር አብሮ ወጣቶች ያሰለጥናል። ሌሎችን ለመርዳት የተነሳሱት የእግር ኳስ አሰልጣኞቹ እና ሰልጣኞቹ እግር ኳስ የሚጫወቱ ከትምህርት ቤት መልስ ነው። ሁለቱም በግል ስለሚንቀሳቀሱ ብዙ ወጣቶችን በቡድናቸው ሊያቅፉ አልቻሉም። ስለሆነም ለቡድኑ አባላት አመራረጥ የራሳቸውን መስፈርት አስቀምጠዋል።
ከሰልጣኞቹ አንዱ የማነ ገብረ መድህን ይባላል። የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነው። የማነ አጥቂ ነው ። ከልጅነት ጀምሬ እግር ኳስ እጫወታለሁ የሚለው የማነ በዚህ ቡድን ውስጥ መሰልጠኑ እንደጠቀመው ይናገራል።
አንድ ቀን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ተስፋ ያላቸው አንድ ሶስት ልጆች አሉን ይላል ቀና። ክርስትያን ደግሞ ይህንን ዕድል የሚያገኙበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል። ስለክርስትያን እና ቀና የበለጠ ከድምፅ ዘገባው ያገኛሉ።
ልደት አበበ
አርያም ተክሌ