1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በፕሬዚዳንት ዴቢ ላይ ያየለው ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 17 2008

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በቻድ የነገ ሳምንት እሁድ ሣምንት ሚያዝያ 2 ቀን፤ 2008 ዓም ይኪያሄዳል። በቻድ የምርጫ ዘመቻ ዋዜማ ግን ከወዲሁ የሀገሪቱ መንግሥት ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢን በመቃወም ሠልፍ የሚያደራጁ ተቃዋሚዎችን ማሠር ጀምሯል። የሲቪል ማኅበረሰቡ ቢያንስ አራት ታዋቂ ተወካዮች ወህኒ መውረዳቸው ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1IJfX
Sudan Khartum Idriss Deby Präsident Tschad
ምስል picture-alliance/dpa/E. Hamid/Ausschnitt

[No title]

እየቀለድን አይደለም። የቻዱ የደኅንነት ሚንሥትር አኅመት ማሓማት ባለፈው ሣምንት የተናገሩትን የሰማ ንግግራቸውን በአጭሩ ቢያሰፍረው ድምጸቱ ይኸው ነው። ሚንሥትሩ በሀገሪቱ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ባስተላለፉት መግለጫ ዕጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ዘመቻ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አስጠንቅቀዋል።

«በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከምርጫ ቅስቀሳ ውጪ ማናቸውም የአደባባይ ሰልፍ በአጭሩ ክልክል ነው። የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ሆኑ የጸጥታ አስጠባቂዎች ይኽን ውሳኔ በንቃት ሊከታተሉት ይገባል።»

በቻድ ካለፉት ሣምንታት አንስቶ የጀመረው ተቃውሞ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊደረግ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅትም እንደቀጠለ ነው። የሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ተወካዮች እና ተቺዎች ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ዳግም ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ ማለታቸውን አጥብቀው በመቃዋም ላይ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ ካለፉት 26 ዓመታት አንስቶ በሥልጣን ላይ ይገኛሉ። ዴቢ ከ12 ዓመት በፊት፤ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2004 ዓመት ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት አሻሽለውት ነበር፤ ዛሬ ለአምስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ማን ከልክሎኝ ሲሉ ቀርበዋል።

ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢን በመቃወም የቻድ ሕዝብ በመዲናይቱ ኒያሚ በአደባባይ
ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢን በመቃወም የቻድ ሕዝብ በመዲናይቱ ኒያሚ በአደባባይምስል DW/B.Dariustone

አብዛኛው የቻድ ነዋሪ የፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ዘመን እስኪያበቃ የታከተው ይመስላል። በሀገሪቱ በርካታ የተቃውሞ ንቅናቄዎች እና ሰልፎች በተደጋጋሚ ተደራጅተዋል። ከእነዚህ መካከል በፈረንሣይኛ «በቃ» የሚለው እና፤ «ሲበዛ በዛ ነው»፣ እንዲሁም «ታክቶናል» የተሰኙት ይገኙበታል። ናጆ ካይና በቻድ ዐረብኛ «ታክቶናል» የሚል ትርጓሜ የተሰጠው ሕዝባዊ ንቅናቄው ቃል-አቀባይ ናቸው።

«የዛሬው መግለጫ እንደውም በውሳኔያችን እንድንጸና ነው ያደረገን። የታቀደው ሰልፍ ይደረጋል። ዴቢ ለዳግም ሥልጣን እንዳይወዳደሩ ጥሪ አስተላልፈናል። ያ ድርጊታቸው የከፋ መዘዝ ያስከትላል ብለናል። የመጥፎ አመራራቸው ውጤትን በቅርቡ ሊያገኙ እና ሊሰናበቱ ይገባል።»

በቻድ በተለይ «ታክቶናል» የሚል ትርጓሜ የተሰጠው ሕዝባዊ ንቅናቄ በርካታ ሠልፈኞችን ማደራጀት ችሏል። እንዲህ ከቀን ቀን የተቃውሞ ሰልፍ እየተደረገባቸውም ቢሆን ፕሬዚዳንት ዴቢ ግን ቃውሞውን ከቁብም የቆጠሩት አይመስል። «የቻድ መንግሥት የመወዳደር መብት አለው። እናሣ ለምን ሲባል ነው የሲቪል ማኅበረሰቡ የሚቃወመው?» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ዘመቻ ወቅት በመዲናይቱ ኒያሚ ለተሰበሰቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ጥያቄ አቅርበዋል። «የፖለቲካ መርሐ-ግብር አለን፤ በዚያም ብዙ አሳክተናል። የተረጋጋ፣ ሠላማዊ እና የሚያብብ አገር ነው ያለን» ሲሉም ተናግረዋል።

የ«ታክቶናል» ሕዝባዊ ንቅናቄ በቻድ ከሚገኙ ሌሎች በርካታ ንቅናቄዎች ጋር የፊታችን ማክሰኞ የአደባባይ ሠልፍ ለማድረግ ጥሪ አስተላልፏል። «በቃ» ከተሠኘው የሰብአዊ መብት ኅብረት ንቅናቄ ማሓማት ኑር አህመት ኢቤዱ የተቃውሞ ሠልፍ ጥሪ ወረቀት በትነዋል በሚል በፖሊስ ጥበቃ ሥር ናቸው። የቻድ የሠራተኛ ማኅበራት ጥምረት ምክትል ሥራ አስኪኢጅ ሚሼል ባርካ የቻድ መንግሥት ድርጊትን ኮንነዋል።

በቻድ የታሠሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች፦ ማሓማት ኑር አህመት ኢቤዱ (በስተግራ)ናጆ ካይና ፓልመር(በስተቀኝ)
በቻድ የታሠሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች፦ ማሓማት ኑር አህመት ኢቤዱ (በስተግራ)ናጆ ካይና ፓልመር(በስተቀኝ)ምስል (c) DW/B. Dariustone

«የቻድ ሕገ-መንግሥት የመሰለፍ እና በትረ-ሥልጣኑን ዝንት-ዓለም ጨብጦ ለመቆየት የሚሟሟት መንግስትን የመቃወም መብት አጎናጽፎናል። እናም መንግሥት ራሱ ሕገመንግሥቱን እየጣሰ ነው።»

ሚሼል ባርካ የጥምረታቸው ዋና ሥራ አስኪያጅ በቅርቡ ወህኒ በመውረዳቸው የተነሳ አመራሩን የሚሰጡት እሳቸው ናቸው። የሥራ ባልደረባቸው የደረሰባቸው የእሥር ዕጣ የእኔም ይሆናል ሲሉ በፍርሃት እንዳላፈገፈጉ ተናግረዋል፤ ሆኖም ግን ሁሉንም ነገር «ነቅተው» እንደሚጠብቁ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

«ንቅናቄው ሠላማዊ እና በሕገመንግሥቱ ጥበቃ የተደረገለት ነው። ያቀረብነውን ጥያቄያችንን ችላ ብለን ዝም አንልም።»
እስካሁን የሲቪል ማኅበረሰቡ አራት ዋነኛ ተወካዮች እሥር ቤት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ። የቻድ መንግሥት ተቃውሞ የሚያስነሱበት በሙሉ ልሣናቸውን ለመዝጋት የቆረጠ ይመስላል።

ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በዘለቀው ዘመነ-ሥልጣናቸው እንዲህ ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸው አያውቅም። ሆኖም ፕሬዚዳንቱ አንዳችም ቁብ አልሰጣቸውም። እንደውም ከወዲሁ ምርጫውን «በዝረራ ነው የማሸንፈው» ሲሉ መዛት ጀምረዋል። በእርግጥ ምርጫው እና ይዞት የመጣው ተቃውሞ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለማወቅ ጥቂት ቀናት መጠበቅ የግድ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ