1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡሩንዲ፤ በማዕቀብ ወደ ሠላም ድርድር?

ረቡዕ፣ ጥቅምት 10 2008

ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት የአፍሪቃ ኅብረት የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት በቡሩንዲ ቀውስ ተጠያቂ ናቸው ያላቸው አካላት ላይ የማዕቀብ ውሳኔ አስተላልፏል። ማዕቀቡ የጉዞ እና የገንዘብ መሆኑ ተገልጧል። በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ደጋፊዎች እና ባላንጣዎች መካከል ካለፉት ጥቂት ወራት አንስቶ ተደጋጋሚ ግጭት ተከስቷል።

https://p.dw.com/p/1GsFU
Burundi Anschlag in Bujumbura's Ntahangwa
ምስል picture-alliance/Anadolu Agency/Y. Rukundo

[No title]

የግጭቱ መንስዔ ሚያዝያ ወር ውስጥ ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በተቃራኒ ለሦስተኛ ተከታታይ የፕሬዚዳንትነት ዘመን እወዳደራለሁ ማለታቸውን ተከትሎ ነው። የዓለም አቀፍ የቀውስ ተመልካች ቡድን «ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ» ባልደረባ ቲዬሪ ቪርኮላን የማዕቀቡን ዋነኛዓላማ ለዶይቸ ቬለ አብራርተዋል።

«ማዕቀቡ የተጣለው መንግሥት ወደ ውይይት ጠረጴዛው እንዲመጣ ለማስገደድግ ታስቦ ነው። በአፍሪቃ ኅብረት ውሳኔ መሠረት ውይይቱን ከቡሩንዲ ውጪ በአዲስ አበባ ወይንም በካምፓላ ለማስጀመር ታስቧል።»

የቡሩንዲ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አላይን አይሜ ንያሚትዌ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ሆኖም የመንግሥት ተወካዮች ከተቃዋሚዎች ጋር የሚነጋገሩበትን ቦታ መምረጡን በተመለከተ ግን ልንነጋገርበት ይገባል ብለዋል። ሚንሥትሩ ከራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ የአፍሪቃ ኅብረት የማዕቀብ ውሳኔ ላይ የደረሰው በራሱ ተነሳሽነት አይደለም ብለዋል። በእርግጥም ቀደም ብሎ ማለትም ከዛሬ ሦስት ሣምንት በፊት የአውሮጳ ኅብረት በአራት ሰዎች ላይ የጉዞ እና የገንዘብ ማዕቀብ አድርጓል። ማዕቀቡ የጉዞ እና የገንዘብ ዝውውር እንዳይደረግ የሚያስገድድ ነው።

አዲስ አበባ የአፍሪቃ ኅብረት የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባ
አዲስ አበባ የአፍሪቃ ኅብረት የሠላምና ፀጥታ ምክር ቤት ስብሰባምስል picture-alliance/dpa/D. Getachew

በቡሩንዲ ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ140 በላይ መሆኑ ተዘግቧል። በመዲናይቱ ቡጁምቡራ በአውራ ጎዳናዎች ላይ የተዘረጉ አስክሬኖችን በየቀኑ መመልከት የተለመደ መሆኑም ተገልጧል። ባለፉት ሣምንታት ውስጥ የፕሬዚዳንቱ ታማኞች እና ታዋቂ የመንግሥት ባለሥልጣኖች ላይ ዒላማ ያደረገ ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘሩ ተዘግቧል። ባለፈው ዐርብ ደግሞ የፀረ-ሙስና ተሟጋቿ እና የተቃዋሚ ፖለቲከኛዋ ሻርሎቴ ዑሙግዋኔዛ ድንገት መጥፋታቸው ከተነገረ ከአንድ ቀን በኋላ ሞተው ተገኝተዋል። ኬኒያዊው የደህንነት ባለሙያ ሰሚዩ ወሬጋ የአፍሪቃ ኅብረት የጣለው ማዕቀብ ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችል ይሰማቸዋል።

«የአፍሪቃ ኅብረት የመረጥኩት ይኽን መንገድ ነው ብሎ ከወሰነ እና አባል ሃገራቱም ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ ቆራጥ ከሆኑ በርካታ ውጤቶችን እንመለከታለን።»

ፒየር ንኩሩንዚዛ ኬንያ ውስጥ ለስብሰባ
ፒየር ንኩሩንዚዛ ኬንያ ውስጥ ለስብሰባምስል Getty Images/AFP/T. Karuma

በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ መሪነት የቡሩንዲን ቀውስ በተመለከተ ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጓል። ሆኖም አባል ሃገራቱ የተለያየ አቋም በማራመዳቸው እስካሁን ድረስ ውጤት አልባ ሆነው ቆይተዋል። ዓለም አቀፍ ተንታኞች ቡሩንዲን በተመለከተ አንዳንድ የአፍሪቃ ኅብረት አባል ሃገራት በሁለት ተከፍለዋል ይላሉ። በአንድ ወገን ራሷ ቡሩንዲን ጨምሮ ታንዛኒያ እና ኬንያ ሲገኙ፤ በሌላኛው ወገን ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ በጋራ ተሰልፈዋል ሲሉ ተንታኞቹ ያብራራሉ። በቡሩንዲ ዓመፃው አሁንም እንዳልተቋረጠ ይነገራል። ሆኖም የአፍሪቃ ኅብረት ልዩ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በአሁኑ ወቅት ወደ ቡሩንዲ መላኩ አስፈላጊ አለመሆኑ ተጠቅሷል።

«በአሁኑ ወቅት በቡሩንዲ የአመፃው ተግባር በአንስተኛ ደረጃ ነው የሚፈፀመው። እናም የእርስ በእርስ ጦርነት የሚባል አይነት ግጭት አይደለም።»

የአፍሪቃ ኅብረት ወደ ቡሩንዲ የሚላክ ልዩ ሰላም አስከባሪ ቡድን መዘጋጀት እንደሚገባው ግን ጥሪ አስተላልፏል። በቡሩንዲ ግጭቱ ወደ ከፋ ደረጃ የሚሸጋገር ከሆነ ልዩ ኃይሉ በፍጥነት ተግባሩን ይጀምራልም ተብሏል።

የቡሩንዲ ቀውስን በተመለከተ ከበርካታ ወራት በፊት ድምፁን ያሰማው የአፍሪቃ ኅብረት የአሁኑ የማዕቀብ ውሳኔ ላይ የደረሰው በቡሩንዲ መንግሥት ተስፋ በመቁረጡ የተነሳ እንደሆነ ተገልጧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ