1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቡና ምርት ለወጣት ኬንያውያን የከፈተው እድል

ረቡዕ፣ ጥር 23 2010

በኬንያ መዲና ናይሮቢ ከሚገኘው ሰው መካከል ከግማሽ የሚበልጠው በጎስቋሎቹ ሰፈሮች ነው የሚኖረው። ይኸው ቁጥርም ከፍ እያለ በመሄድ ላይ ነው። ይህ ክስተት ግን ናይሮቢ ከተማን ብቻ የሚመለከት አይደለም።

https://p.dw.com/p/2rq1d
Afrika Kaffeeanbau Illustration
ምስል picture alliance/Tone Koene

ወጣት ኬንያውያን ገበሬዎች

እንደ የተመድ ዘገባ፣ ብዙ የአፍሪቃ ከተሞች በሚቀጥሉት ዓመታት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ ያጋጥማቸዋል። ከተሞች በሕዝብ ቁጥር ጭማሪ እንዳይጨናነቁ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ኬንያ በምሳሌነት አሳይታለች። በዓለም ገበያ የቡና ዋጋ  መጨመርን ተከትሎ ብዙ በናይሮቢ ይኖሩ የነበሩ ወጣቶች ወደ ገጠሩ በመመለስ በግብርናው ስራ ተሰማርተዋል።   

ወጣቱ ጃክሰን ሩጋራ ከናይሮቢ ወደ ገጠሩ በመሄድ የግብርናውን ሙያ ተያይዞታል። ጃክሰን እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጥሩ ምክንያት እንደነበረው ይናገራል። 
« በግብርናው ስራ ለመሰማራት የመረጥኩት ብዙ ትርፍ ላገኝበት እና የራሴም አዛዥ ለመሆን እንደምችል በማወቄ ነው። ማንም ከስራ ሊያባርረኝ አይችልም። »
በ20 ዓመት አጋማሽ ላይ የሚገኘው እና ብዙ የወደፊት እቅድ የወጠነው ጃክሰን  ወጣት ገበሬዎች በጋራ ቡና የሚያመርቱበት የአንድ የህብረት እርሻ አባል ነው። የህብረቱ እርሻ ከቡና  ምርት ከሚገኘው ትርፍ ለወጣቶቹ ገበሬዎች ህብረቱ እርሻ አባላትው ንዑስ ብድር ይሰጣል። ጃክሰን ባገኘው ብድር  አንዲት ላም ገዝቶ አሁን ሁለተኛ ጥጃ ልትወልድለ ጥቂት ጊዜ ቀርቷታል። ከወተት ሽያጭ ጥሩ ገቢ በማግኘቱም ብድሩን ሳይቸገር መክፈል እንደሚችል ነው የገለጸው። ከዚህ በተጨማሪም፣ እሱና ጓደኞቹ ንቦች ለመግዛትና የማር ምርትም ለመጀመር ይፈልጋሉ።  ለግብርና ሙያ ዘግይቶ ፍላጎት ያሳደረው  ጃክሰን ትምህርቱን ሲጨርስ በሰለጠነበት የኤሌክትሪክ ሰራተኛነት ሙያ ናይሮቢ ውስጥ  ሁለት ዓመት ተቀጥሮ ከሰራ በኋላ ነበር በኬንያ በፍሬያማነቱ ወደሚታወቀው ወደ ካንጎቾ የሄደው። የናይሮቢ ኑሮውንም ከገጠሩ ጋር ሲያወዳድረው ብዙ ልዩነት አይቶበታል።
«  ናይሮቢ ውስጥ ፣  እርግጥ ሰርተህ ብዙ ገንዘብ ታገኛለህ። ግን ለሁሉም ነገር መክፈል አለብህ፣ ለውሀ፣ ለኮሬንቲ፣ ለኪራይ፣ ለሁሉም፣ እዚህ ገጠር ግን ብዙ ወጪ የለብንም። ለምሳሌ የሚያስፈልገንን አትክልት ራሳችን እናመርታለን። ስለዚህ ከናይሮቢ የተሻለ ብዙ እናተርፋለን። »
ለብዙ ጊዜ ኬንያ ውስጥ ግብርና በእድሜ የገፉ ሰዎች ሙያ ሆኖ ነበር የሚታየው። ይህ አመለካከት ግን አክትሞለታል፣ ቢያንስ ቡና በሚመረትበት የኬንያ አካባቢ።  በሚያመርተው ምርጥ  የቡና  ዓይነት  በዓለም አቀፍ ደረጃ  በሚታወቀው  የካንጎች አካባቢ የተቋቋመው የህብረት እርሻ ለወንድ እና ሴት ወጣት የቡና አምራች ገበሬዎች ምርታቸውን ማሳደግ የሚችሉበትን ስልጠና ይሰጣል፣ ለምሳሌ ምርት የሚያበላሹ ተባዮችን እንዴት መከላከል እንደደሚችሉ ያስተምራል። ገበሬዎቹ በአማካይ ከአንድ ዛፍ በአምስትና 15 ኪሎ ቡና የሚያመርቱ ሲሆን፣ ምርታቸውን ከፍ ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ገበሬ ቻርልስ ዋንጆሂ ተናግሯል።
« ብዙ ገንዘብ ለማግኘት የሚፈልግ ብዙ ቡና ማምረት ይኖርበታል። ለዚህም ጠንክሮ መስራት የግድ ስለሚል፣ እርሻዬን በሚገባ እንከባከባለሁ።  በየቀኑ እየመጣሁም የተክሉን ሂደት እከታተላለሁ።»
ቻርልስ ከአንድ ዛፍ 12 ኪሎ ቡና ያገኛል፣ ግን የምርቱን መጠን በመጨመር እና የጥራቱንም ዓይነት በማሻሻል  ገቢውን የማሳደግ እቅድ እንዳለው  ገልጿል። በወቅቱ አንድ ኪሎ ቡና 105 የኬንያ ሺሊንግ ይሸጣል።  ገበሬው ለኪሎው ቡና 10 ሺሊንግ ከሀምሳ ብቻ የሚያገንበት ዓመታትም እንደነበር ይታወሳል።  ግን፣ የህብረቱ እርሻ ገበሬዎቹ ፍትሓዊ ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ ካመቻቸ ወዲህ ጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ዋንጆህ አስታውቋል።
« በቡና አምራችነት የተሰማራሁባቸው ያለፉት 20 ዓመታት ለኔ ጥቅም አስገኝተውልኛል። ሌላ የእርሻ ቦታ መግዛት ችያለሁ፣ ባቅራቢያዬም አንድ የተክል ቦታ ገዝቻለሁ። ምንም የማርረው ነገር የለኝም። »
ወጣት ገበሬ ጃክሰን እና ባልተቤቱ ሼልሚ ጋቲኬም በኑሯቸው ደስተኞች ናቸው።  ለሁለት ልጆቻቸው ወደፊት የትምህርት ቤት ክፍያን መክፈል እንደሚችሉ የሚተማመኑት ጃክሰን እና ሼልሚ ከካንጎቾ ውጭ ሌላ ቦታ፣  ናይሮቢም ሆነ አውሮጳ የመኖር ህልምም ሆነ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

Afrika Kaffeeanbau Illustration
ምስል picture alliance/Tone Koene
Nairobi Skyline Kenia Stadtansicht
ምስል Fotolia/Natalia Pushchina

አርያም ተክሌ/ቤቲና ሪውል

ሂሩት መለሰ