1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡኻሪና ዳዉራ

ዓርብ፣ ግንቦት 21 2007

የሳሕል በረሐን የተንተራሰችዉ ዳዉራ-እንዲሕ አይነት ፌስታ፤ድግሥ፤ክብር ዝና ብዙም አግኝታ አታዉቅም።ነዋሪዋ-ትንሽ ነዉ።ሃያ-አምስት ሺሕ።ከእንግዲሕ 173 ሚሊዮኑን ናይጄሪያዊ የሚመሩት መሐመዱ ቡኻሪ ከዚያ ሕዝብ መሐል በዚያች ከተማ ተወለዱ።የዛሬ ሰባ-ሁለት ዓመት።

https://p.dw.com/p/1FZBw
ቃለ-መሐላ
ምስል Reuters/A. Sotunde

[No title]

የሰሜን ናይጄሪያዋ ትንሽ ከተማ ዳዉራ ለዉትሮዉ ብዙም እንቅስቃሴ የማይታይባት፤ የሐዉሳ ሕዝብ መንፈሳዊ ማዕከል፤ የካስቲና ክፍለ-ግዛት ዋና ከተማ ናት።ዛሬ ቃለ መሐላ ፈፅመዉ የናይጄሪያን የፕሬዝደንትነት ሥልጣን በይፋ የተረከቡት የመሐመዱ ቡኻሪ የትዉልድ መንደር።ቡሐሪ ባለፈዉ መጋቢት ናጄሪያ ዉስጥ በተደረገዉ ምርጫ ካሸነፉ ወዲሕ የዚያች ትንሽ ከተማ ሥም በተደጋጋሚ ይጠራል።ነዋሪዎችዋ በኩራት ደስታቸዉን ይገልጣሉ።የዶቸ ቬለዋ ካትሪን ገንስለር እንደዘገበችዉ ደግሞ ቡኻሪን ለመሸኘት ሠሞኑን የተዘጋጀዉ ድግስ ያቺን ትንሽ የምታንቀላፋ ከተማ እድምቋት ነዉ የሠነበተዉ።ነጋሽ መሐመድ

ከተማይቱን ካደመቁት ዋንኞቹ አነሱ ቸዉ።ሙዚቀኞቹ።አምስት ናቸዉ።በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወሩ-በመዝፈን፤መጨፈር፤ ማስጨፈር የታወቁ ናቸዉ።ሰሞኑን ግን ዳዉራ ከትመዋል። በሳምንት አንዴ በሚዉለዉ የገበያ ሁዳድ ላይ ከበሯቸዉን እየጎሰሙ፤ ይዘፍናሉ፤ይጨፍራሉ፤አላፊ አግዳሚዉም ይሸልማቸዋል።ገንዘብ።የሮቡ ግን ልዩ ነበር። የትንሺቱ ከተማ ትልቅ ሰዉ ትልቅ ሽኝት።

«ጄኔራል ቡኻሪን እንደ አዲስ ፕሬዝደንት ለመሸኘት ወደ ዳዉራ በመምጣትችን በጣም ደስ ብሎናል።ባሕላዊ ሙዚቃ እንጫዎታለን።እኛ እራሳችን ማየት የምንፈልገዉ የቦክስ ግጥሚያም ይደረጋል።»

ዳዉራ-ገበያ ላይ
ምስል DW/K. Gänsler

ሙዚቀኛዉ አብዱከሪም አባሙ።የሳሕል በረሐን የተንተራሰችዉ ዳዉራ-እንዲሕ አይነት ፌስታ፤ድግሥ፤ክብር ዝና ብዙም አግኝታ አታዉቅም።ነዋሪዋ-ትንሽ ነዉ።ሃያ-አምስት ሺሕ።ከእንግዲሕ 173 ሚሊዮኑን ናይጄሪያዊ የሚመሩት መሐመዱ ቡኻሪ ከዚያ ሕዝብ መሐል በዚያች ከተማ ተወለዱ።የዛሬ ሰባ-ሁለት ዓመት።የተወለዱበት ከጡብ የተሠራዉ ቤት ዛሬም ወይባማ ቀለሙን እንደያዘ አለ።የልጅነት ባልጀራ-ጎረቤታቸዉ ለዋል አልዩም-እዚያዉ ናቸዉ።

«መጀመሪያ የተገናኘንበትን ጊዜ ጭራሽ አላስታዉስም።ቤቶቻችን ጎን ለጎን የቆሙ-ጎረቤታሞች ነን።ያኔ መተዋወቅ በጣም ቀላል ነበር።በእድሜ ይበልጠኛል።ግን አብረን ሥንጫወት ነዉ ያደግነዉ።ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያየነዉ እሱ ከኔ ቀድሞ ትምሕር ቤት ሲገባ ነበር።»

ግንኙነታቸዉ ግን እንደቀጠለ ነዉ።የልጅነት ባልጀራቸዉ ለትልቁ ሥልጣን በመመረጣቸዉ ደስታቸዉ ጥልቅ ነዉ።እርግጥ ነዉ ቡኻሪ ከዳዉራ ለመሸኘት፤ ሐገር ለመምራትም እንግዳ አይደሉም።ከ1984 እስከ 85 (,,) ትልቂቱን፤ ሐብታሚቱን ግን በሙስና የተዘፈቀችዉን ሐገር መርተዋል።በምርጫ ግን አልነበረም።በመፈንቅለ መንግሥት እንጂ።በየኔዉ አገዛዛቸዉ በተለይ የዉጪ ተቺዎቻዉ ሰዎችን አንገላተዋል ብለዉ ይወቀሷቸዋል።የቡኻሪ የቅርብ ተባባሪና የካስቲና ምክትል አገረ-ገዢ ሙኒር ያኩቢ እንዲሕ አይነቱን አስተያየት ሲሰሙ ይናደዳሉ።

«አዎ እዉነት ነበር።ግን ከዚያ በሕዋላ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ታይቶ ተወስኗል።መዘንጋት የሌለበት ያኔም ልክ እንዳሁኑ ሙስና አለቅጥ ተንሰራፍቶ ነበር።ያን ለማጥፋት እርምጃ መወሰድ ነበረበት።»

የተወለዱበት ቤት
ምስል DW/K. Gänsler

ጄሪያዉያን ሰዉዬዉን ባንድ ነገር ያዉቋቸዋል።ለሙስና ያኔም-አሁንም ምሕረት የላቸዉም።አብዛኞቹ የናጄሪያ ፖለቲከኞች፤ጄኔራሎችና ቤተሰቦቻቸዉ ከሌጎስ-አቡጃ አልፈዉ ለንደን፤ፓሪስ፤ ዱባይ ሲንደላቀቁ ቡኻሪ ከዳዉራ አልወጡም።በሠፊ የአትክልት ሥፍራ የተከበበዉ ቤታቸዉ እንደነገሩ የተሠራ ነዉ።ብዙ ቁሳቁስም የለዉም።የዳዉራ ነዋሪዎች ድሮም-እንዲሕ ነበር ይላሉ።አሁንም ያዉ ነዉ።ሙኒር ያኩቡ ደግሞ ሰዉዬዉስ ቢሆኑ ይላሉ።

«ጄኔራሉ ያኔም-አሁንም ያዉ ናቸዉ።ዝምተኛ፤ ቀጥተኛ፤ እዉነተኛ። የሚያስቡትን የሚናገሩ ናቸዉ።አነጋገራቸዉ ቀላል፤ ለተራዉሰዉ የሚገባ፤ አለባበሳቸዉ የተራ ሰዉ ነዉ።ለዚሕ ነዉ ብዙ ሰዉ የሚወዳቸዉ።»

የሚወደዉን ለመምርጥ የታደለዉ ብዙ ናይጄሪያዊ መረጣቸዉ።ዛሬ ትልቁን ሥልጣን በይፋ ተረከቡ።የሕዝቡ አደራ-ለመወጣት ቃል ገቡም።ፕሬዝደንት መሐመዱ ቡኻሪ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ