1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቡጁሙቡራ፤ በቡሩንዲ ዋና ከተማ ከባድ ተኩስ መሰማቱ

ዓርብ፣ ግንቦት 7 2007

በቡሩንዲ ዋና ከተማ ቡጁሙቡራ በሚገኘዉ መንግሥታዊ የቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያ አቅራቢያ ዛሬ ከባድ ተኩስ መካሄዱን ዘገባዎች እያመለከቱ ነዉ። የመንግሥት ግልበጣዉን የሚደግፉ ወታደሮች የተጠናከረ የማጥቃት ርምጃ የወሰዱት ከሀገር ዉጭ የሚገኙት ፕሬዝደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ መልዕክት በራዲዮ ከተሰራጨ በኋላ መሆኑን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከስፍራዉ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/1FPoY
Burundi Militärputsch Polizei
ምስል picture-alliance/AP Photo/G. Ngingo

ንኩሩንዚዛ ሥርዓት የሚያስከብሩትን ወታደሮችን በማመስገን በመፈንቅለ መንግሥቱ ቢሳተፉም እጅ ለሚሰጡት ደግሞ ይቅርታ እንደሚያደርጉ መናገራቸዉ ተጠቅሷል። የራዲዮ ጣቢያዉ ኃላፊ በባድ ጥቃት ምክንያት ስርጭት ማቋረጣቸዉን በስልክ መግለፃቸዉ ከተዘገበ ከሰዓታት በኋላም መልሶ ማሰራጨት መቀጠሉን ዘገባዎች ያመለክታሉ። በተመሳሳይ የቡጁምቡራን አዉሮፕላን ማረፊያን ለመቆጣጠር በመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል የተኩስ ልዉዉጥ መካሄዱ ተዘግቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለም ስለቡሩንዲ ጉዳይ ዳሬሰላም ላይ ከሚወያዩት የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት አንዷ የሆነችዉ የታንዛኒያ ፕሬዝደንት ጃካያ ኪክዌቴ የተካሄደዉ መፈንቅለ መንግሥት የሀገሪቱን ችግር እንደማይፈታ በማመልከት ጉባኤዉ ማዉገዙን አመልክተዋል።

Burundi Militärputsch Polizei
ምስል picture-alliance/AP Photo/G. Ngingo

«ቡጁሙቡራ ዉስጥ አዳዲስ ለዉጦች መከሰታቸዉን ተረድተናል። ጉባኤዉ ቡሩንዲ ዉስጥ የተካሄደዉን መፈንቅለ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ አዉግዟል። በጉባኤዉ እይታም ይህ የቡሩንዲን ችግር ሊፈታ አይችልም። መንግሥት ግልበጣዉን አንቀበልም። በከፍተኛ ደረጃ እናወግዘዋለን፤ ሀገሪቱም ወደሕገመንግሥታዊ ሥርዓት እንድትመለስ ጥሪ እናቀርባለን።»

ከዚህም ሌላ ቡሩንዲ ዉስጥ ያለዉ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ ምቹ አለመሆኑን በማመልከትም የምርጫ ኮሚሽኑ ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፈዉም ጥሪ አስተላልፈዋል። ዘግይተዉ የወጡ ሌሎች ዘገባዎች የመንግሥት ራዲዮ ጣቢያዉን የፕሬዝደንት ንኩሩንዚዛ ታማኞች መልሰዉ መቆጣጠራቸዉን ያመለክታሉ። በአንድ የቀድሞ የብሩንዲ ጀነራል የተመራ የጦር ሐይል ቡድን የሐገሪቱን ፕሬዝደንት ከስልጣን ማስወገዱን ባሳወቀ በማግስቱ ዛሬ በብሩንዲ ፀጥታው ደፍርሷል ። በዋና ከተማይቱ በቡጁምቡራ በመንግሥት ታማኞችና በመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።

Pierre Nkurunziza, Präsident von Burundi
ፕሬዝደንት ንኩሩንዚዛምስል B. Smialowski/AFP/GettyImages

ፕሬዝዳንት ፕየር ንኩሩንዚዛ ዛሬ በመንግሥት ራድዮ ጣቢያ መፈንቅለ መንግሥቱን ማውገዛቸውና እጃቸውን ለሚሰጡ ወታደሮችም ምህረት እንደሚያደርጉ መናገራቸው ተሰምቷል ።ቀደም ሲልም ከዳሬሰለም ታንዛኒያ ህዝቡ እንዲረጋጋ በትዊተር ጠይቀው ነበረ ።ብሩንዲ አሁን ያለችበትን ህገ መንግስትን የመጣስ ወይም የመቀልበስ አዝማሚያን ለማስወገድ ሃላፊነት የሚሰማቸው የጦር ኃይል አባላት የሃገሪቱን መፃኤ እድል የመወሰኑን ሃላፊነት ይይዛሉ ።ሃላፊነት የሚሰማቸው የሃገሪቱ ጦር ኃይል አባላት በአሩሻው ስምምነት መሰረት የተደነገገውን ህገ መንግሥት በመጣስ ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ ዘመነ ሥልጣን ለመወደደር መወሰናቸውን ይቃወማሉ ።ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ከስልጣናቸው ተነስተዋል ። መንግሥታቸው ተወግዷል ።»
ባለፈው ዓመት ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞ የብሩንዲ የስለላ መሥሪያ ቤት ሃላፊ ጎደፍሮይድ ኒዮምባሬ ትናንት በአንድ የግል ራድዮ ጣቢያ ፕሬዝዳንት ፕየር ንኩሩንዚዛ ከሥልጣን ተነስተዋል ያሉበት ይህ አዋጅ እንደተሰማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደበባባይ በመውጣት ደስታቸውን በሆታና በጭፈራ ገልፀው ነበር ። ፖሊሶችም ከህዝቡ ጋር የደስታው ተካፋይ ነበሩ ። የመፈንቅለ መንግስቱ ዜና ካስደሰታቸው አንዱ የቀድሞ የብሩንዲ አምባሳደር ፖል ማህዌራ ናቸው ።
«አብዛኛዎቹ ብሩንዲያውያን መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል መባሉን ሲሰሙ በጣም ነበር የተደሰቱት ። በርግጥ በትክክል አስፈላጊ ነበር »
የፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ መንግሥት ትናንትም ሆነ ዛሬ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፈኑን ነው የሚናገረው ። ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ ደግሞ ዛሬ በመንግሥት ራድዮ ጣቢያ የመፈንቅለ መንግሥቱን ሙከራ አውግዘው እጃቸውን ለሚሰጡ ወታደሮች ምህረት እንደሚያደርጉ መናገራቸው ተዘግቧል ።ከፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ የራድዮ ጣቢያው ሥርጭት መቋረጡ ተነግሮ ነበር ።ሆኖም በመንግሥት ሥር ያለው ይኽው ራድዮ ጣቢያ ሥርጭቱንመቀጠሉ ተነግሯል። የብሩንዲ ጦር ኃይል አዣዥ ዛሬ ጠዋት መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉንና የብሩንዲ ስልታዊ ቦታዎችም በንኩሩንዚዛ ታማኝ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን በመንግሥት ራድዮ ጣቢያ ተናግረዋል። ያም ሆኖ በዋና ከተማይቱ በቡጁምቡራ በመንግሥት ሐይላትና በመንፈቅለ መንግሥቱ መሪ ደጋፊዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው ።ሁለቱ ወገኖች ከዛሬ ጠዋት አንስቶ የከባድ መሣሪያዎች እየተታኮሱ ነው ። የጀነራል ንዮምባሬ ደጋፊዎች መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱን ያሳወቁባቸው 4 የግል ራድዮ ጣቢያዎች ለሊቱን መንግሥትን በሚደግፉ ፖሊሶች መቃጠላቸውን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል ።የብሩንዲ ጦር ኃይል አዛዥ መፈንቅለ መንግሥቱ መክሸፉን ዛሬ ጠዋት በመንግሥት ራድዮ ጣቢያ ካሳወቁ በኋላ ደግሞ ራድዮ ጣቢያው የሚገኝበት ህፃ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ተፈፅሞበታል ። የዶቼቬለ የቡጁምቡራ ዘጋቢ እንዳለችው ደግሞ ትናንት ማታ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄደው የኒያምቤራ ቡድንና የብሩንዲ ጦር ኃይል ለድርድር ተቀምጦ ነበር ። ሆኖም የኒያምቤራ ቡድን ጦር ኃይሉ ከጎናቸው እንዲቆም ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱ ነው የተሰማው።በብሩንዲ ጉዳይ ላይ ከምሥራቅ አፍሪቃ መሪዎች ጋር ለመምከር ዳሬሰላም ታንዛንያ ሄደው ወደ ሃገራቸው መመለስ ያልቻሉት ፕሬዝዳንት ንኩሩንዚዛ እዚያው ዳሬሰላም ሆነው በትዊተር ህዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ አስተላልፈው ነበር ። ንኩሩንዚዛ በዳሬሰላሙ ንግግር ላይ አለመካፈላቸው ነው የተነገረው ። ትናንት ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ቢሞክሩም የብሩንዲ አውሮፕላን ማረፊያ የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊ በሆኑ ኃይላት በመያዙ እዚያው ዳሬሰላም ለማደር ተገደዋል ።ለ10 ዓመታት ብሩንዲን የመሩት ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን እወዳደራለሁ ማለታቸው ባስነሳው ተቃውሞ ባለፈው ሰሞን ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ።አሁን በብሩንዲ የተከሰተው አለመረጋጋት በሃገሪቱ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ 1993 እስከ 2005 በሁቱዎችና በቱትሲዎች መካከል የተካሄደውንና 300 ሺህ የተገመተ ህዝብ ያለቀበትን የጎሳ ጦርነት እንዳይቀሰቅስ አስግቷል ። በቅርብ ጊዜው ግጭት ምክንያት ከ50 ሺህ የሚበልጡ የብሩንዲ ዜጎች ወደ ጎረቤት ሃገራት ተሰደዋል ።

Burundi Militärputsch
ምስል Reuters/G. Tomasevic
Burundi Militärputsch
ምስል Reuters/G. Tomasevic

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ