1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቢን ላደን የተገደሉበት አንደኛ ዓመትና የዓለም ሠላም

ሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2004

«የዚያን ቀን ቢን ላደን እዚያ ባይኖርስ?» ጠየቁ ገሚሶቹ፥ «ቦምቡ መጣሉንስ ይጣል፥ ግን ቢን ላደን ሙሉ በሙሉ ቢጨፈለቅ ለመግደላችን ማረጋገጪያችን ምንድ ነዉ?» አሉ የተቀሩት።ሌሎቹ ደግሞ ሌላ-በርግ እንደፃፉት።ልዩ ኮማንዶ ይዝመት የሚለዉ ሐሳብ አሸነፈ

https://p.dw.com/p/14nIo
Der arabische Fernsehsender Al-Dschasira hat am 5.10.2001 ein Video ausgestrahlt, das den mutmaßlichen saudischen Terroristenführer Osama bin Laden (r) zusammen mit dem ägyptischen "Terror-Doktor" Aiman el Zawahiri (l) in einem Lager von bin Ladens Terrororganisation El Kaida zeigt. Nach Angaben des Senders ist das Bildmaterial aus Afghanistan neu. fs12Dfs16er Sender konnte jedoch nicht mit Sicherheit sagen, ob es vor oder nach den Terroranschlägen in den USA am 11. September aufgenommen wurde. Es zeigt die beiden Männer Seite an Seite bei einer Feier für mehrere Mitglieder der Organisation El Kaida, die gerade ihre Ausbildung zum Gotteskrieger beendet haben.
ሟቹና ተተኪዉ የአልቃኢዳ መሪዎችምስል picture-alliance / dpa

ዋሽግተን።ለፕሬዝዳት ባራክ ኦባማና ለትላልቅ ባለሥልጣኖቻቸዉ ያ ዕሁድ የዕረፍት፣ ቀን አይደለም። መሽቷል።ግን ለነሱ የእንቅልፍ ሰዓትም አልነበረም።ከዋይት ሐዉሱ የዘመቻ መከታታያ ክፍል ((Situation Room) ካለዉ ቴሌቬዢን ላይ አፍጥጠዉ ከአቦታባድ-ፓኪስታን በልዩ ካሜራ የሚተላለፈዉን ምስል-ድምፅ ይከታተላሉ።አቦታባድ ሊነጋ ነዉ።«መብራቱን እንዳታጠፊዉ» አሉ ሰዉዬዉ-አራተኛ ሚስቱን።ወዲዉ ጥይት።በቃ። የትልቂቱ ሐገር ትልቅ ጠላት ተገደሉ።ኦሳማ ቢን ላደን።ዛሬ ለነገ-አጥቢያ አመቱ።የዕለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት መሪ ሙት አመት መነሻ፣ አገዳደሉ ማጣቀሻ የድሕረ-ቢን ላደኗ ዓለም ሠላም መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

ቢን ላደን በተገደሉ ሰሞን ጋዜጠኛዉ፥ የቀድሞዉን የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስልድን ጠየቀ።«ቢን ላደን በመገደሉ ተደስተዋል» ብሎ።የአፍቃኒስታኑ ጦርነት፣የዓለም አቀፉ ፀረ-ሽብር ዘመቻ፣ የኢራቅ ወረራ መሪና አቀነባባሪዉ መልስ አልሰጡም።ጠያቂዉ ላይ አፍጥጠዉ- ጠየቁት እንጂ ።«አንተ-አልተደሰትክም» ብለዉ።የሐብታሙ፣ እብሪተኛዉ ጡረተኛ ሚንስትር ግልምጫ ያሸማቀቀዉ ጋዜጠኛ አለመነታም።«በጣም ተደስቻለሁ እንጂ» መለሰ።

ቢን ላደን በተገደሉበት ወቅት ብዙም በማትታወቀዉ የፓኪስታን ከተማ፥ በቅጡ በማይለየዉ ሕንፃ ዉስጥ ተደብቀዉ የስለላ ካሜራ ከመዘወር ሌላ የመሰረቱትን ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን በቀጥታ መምራት አይችሉም ነበር።

ጀርመናዊዉ የአል-ቃኢዳ ጉዳይ አጥኚ ሮልፍ ቶፕሆፈን እንደሚሉት ግን ቢን ላደን ቡድናቸዉን በቀጥታ ከመምራት ርቀዉ የራሳቸዉን ሕይወት ለመጠበቅ በሚባትሉበት በዚያ ወቅት፥ አሁንም እንኳ በተከታዮቻቸዉ ዘንድ እንደ ልዩ መሪ መታየታቸዉ አልቀረም ነበር።

«አቦታባድ ዉስጥ ከዉጪ ዓለም በቴክኖሎጂ ጭምር በታጠረ ቤት ሆኖ ደሕንነቱን ለመጠበቅ ሲባትል ነበር።እዚያ እንደነበር ከፓኪስታን የሥለላ ድርጅት (ISI) ከፍተኛ ባለሥልጣናት በስተቀር የሚያዉቅ አልነበረም።ያኔም የአል-ቃኢዳ ምልክታዊ መሪ ነበር።ዘመቻን በተመለከተ ግን ቢን ላደን ከረጅም በፊት ጀምሮ በታቀዱ ወይም በተፈፀሙ የሽብር ጥቃቶችላይ ተፅዕኖ ማሳደር አይችልም ነበር።»

ሰዉዬዉን እንደ ልዩ መሪ የሚያየዉ የአል-ቃኢዳ አባልና ደጋፊ በቢን ላደንን መገደል ማዘን-መከፋቱ፥ ለብቀላ መዛት-መፎከሩን በተደጋጋሚ ሰምተናል።ከኒዮርክ፥ እስከ ብራስልስ ያሉ ማሕበራት፥ ከካቡል እስከ ሪያድ የሚገኙ የዓለም መንግሥታት ግን ብቸኛይቱን ልዕለ ሐያል ሐገር በማሸበር፥ በሺ የሚቆጠር ሕይወት በማስጠፋት ተጠያቂ የሆኑት ግለሰብ መገደላቸዉን ሲሰሙ ያልተደሰተ ወይም ተደሰትኩ ያላለ የለም።

አፍቃኒስታን የዘመተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በሁለት ሺሕ ሁለት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ቢን ላደንና የቅርብ ተከታዮቻቸዉን ቶራ ቦራ በተሰኘዉ ተራራ ላይ ከቧቸዉ ነበር።የአል-ቃኢዳዉ መሪ ከበባባዉን ሰብረዉ አመለጡ።የቢን ላደን ጉዳይ አጥኚ ፒተር በርግ እንደፃፉት የያኔዉ የአሜሪካ ማዕከላዊ የሥለላ ቢሮ (CIA) ከፍተኛ ባለሥልጣን ማይክል ሞሌር ለፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ቢን ላደን ማምለጣቸዉን ሲነግሯቸዉ ቡሽ ክፉኛ ነበር የተቆጡት።

«ፕሬዝዳንቱ» ይላሉ ደራሲዉ ቢንላደንን ሞሌር እራሳቸዉ ያስመለጧቸዉ ይመስል በሲ አይ ኤዉ ባለሥልጣን ላይ ያንባርቁባቸዉ ያዙ።በዚሕም ሰበብ ቢን የሚያድኗቸዉን ሐይላት ሽሽት ባንድ ቤት ታጥረዉ የተሸሸጉ ቢሆንም መገደላቸዉ ራምስ ፌልድ እንዳሉት ለአሜሪካኖች በጣሙን ለፖለቲከኞቹ እንደ ሌላዉ አስደሳች ዜና ብቻ አይደለም፥ ፌስታ ጭምር እንጂ።


ጀርመናዊዉ የአሸባሪዎች ጉዳይ አጥኚ ሮልፍ ቶፕሆፈን እንዳሉት ድፍን አስር ዓመት ሲታደኑ የነበሩት ኦስማ ቢን ላንደን አቦታባድ-ፓኪስታን ዉስጥ እንደሚኖሩ የፓኪስታን የሥለላ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሳያዉቁ አይቀሩም።የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞም በዚሕ ይስማማሉ።
እንዲያዉም አንዳዶቹ የአሜሪካ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ተንታኞች የፓኪስታን የሥለላ ድርጅት ባለሥልጣናት ባይተባበሯቸዉ ኖሮ ቢን ላደን ያን ያሕል ጊዜ እዚያ ሥፍራ ተሸሽግዉ መኖር አይችሉም ነበር በማለት ይወነጅላሉ።

ፓኪስታኖች ወቀሳ ትችቱን አይቀበሉትም።የፓኪስታን የሥለላ ድርጅት ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባለፈዉ አርብ እንዳስታወቁት ደግሞ አብዛኛዉን ዓለም ላስደሰተዉ፥ ወይም ያስደሰተ ለሚመስለዉ፥ አሜሪካኖችን ላስፈነደቀዉ ግድያ ዋናዋ መሠረት ፓኪስታን በጣሙን የስለላ ድርጅቷ ነዉ።ISI ።ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ሁለቱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ዩናይትድ ስቴትስ ቢን ላደንን ለመግደል የቻለዉ የፓኪስታን የስለላ ባለሙያዎች መስከረም ሁለት ሺሕ አስር ለሲ አይ ኤ ባቀበሉት መረጃ ላይ ተመስርታ ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ቢን ላደንን ይሁን ሌሎች ተጠርጣሪዎቹን በማደኑ ሒደት ከፓኪስታን መንግሥትና የሥለላ ድርጅት «ጠቃሚ» መረጃ ማግኘትዋን ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማና የስለላ ድርጅታቸዉ ባለሥልጣናት አልካዱም።ቢን ላደን አቦታባድ እንደነበሩ የሚጠቁመዉ መረጃ ከፓኪስታን ሥለ መገኘቱን ግን የአሜሪካ ባለሥልጣናት እስካሁን አላረጋገጡም።አላስተባበሉምም።


አጥኚ ፒተር በርግ እንደሚሉት ጥቆማዉ ከየትም ይገኝ ከየት ቢን ላደን አቦታባድ እንደሚኖሩ ፕሬዝዳት ኦባማ ጆሮ የደረሰዉ ፓኪስታኖች ለሲ አይ ኤ ጠቆምን ባለቡት ወቅት ነበር።ጥቅምት ሁለት ሺሕ አስር።


«ዩናይትድ ስቴትስ፥ በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ንፁሐን ወንዶች፥ ሴቶችና ልጆች መገደል ተጠያቂ የሆነዉ አሸባሪዉ የአል-ቃኢዳ መሪ ኦስማ ቢን ላደን የገደለ ዘመቻ ማድረጓን ለአሜሪካ ሕዝብና ለመላዉ ዓለም መዘገብ እችላለሁ።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ግንቦት አንድ ሁለት ሺሕ አስራ-አንድ።

ኦባማና የፀጥታ ሹማምንቶቻቸዉ ከዚሕ ድል ለመድረስ ከመስከረም ጀምሮ እስከ ዚያች ምሽት ድረስ ብዙ ማዉጣት ማዉረድ ብዙ መከራከር መጨቃጨቅ፥ መረጃዎችን መበጠስ-መቀጠል ነበረባቸዉ።ያኔ የሲ አይ ኤ ዳሬክተር የነበሩት ያሁኑ መከላከያ ሚንስትር ሊዮን ፓኔታ ፓኪስታኖች ለሲኤ ኤ አቀበልን ያሉትን መረጃ ለፕሬዝዳንቱ ለማድረስ አልዋሉ፥ አላደሩም።

የመጀመሪያዉ ግርድፍ መረጃ የቢን ላደንን ሾፌር የአቡ አሕመድ አል-ኩዌይቲን ተንቀሳቃሽ ሥልክ ቁጥርን ጠቋሚ ነበረች።ፓኔታ ከኦባማ በተሰጣቸዉ ትዕዛዝ መሠረት ወደ ፓኪስታን ያዘመቷቸዉና ፓኪስታን ላይ እንዲያተኩሩ ያዘዟቸዉ የአሜሪካ ሰላዮች የያዙትን የጥቆማ ገመድ ጫፍ እየጠቀለሉ ሲጓዙ በሰባተኛ ወራቸዉ የገመዱ ሌላ ጫፍ ከተቋጠረበት ግንድ ደረሱ።አቦታባድ።ጭር ካለዉ ሕንፃ።

ያኔ ነዉ-የትልቂቱ ሐገር የፀጥታ ሹማምንት ሙግት ክርክር የተጀመረዉ።ምክትል ፕሬዝዳት ጆ ባይደን፣ መከላከያ ሚንስትር ሮበርት ኤም ጌትስ፣ የጥምር ኤታማዦር ሹሞች ምክትል ሊቀመንበር ጄኔራል ጄምስ ኢ ካርትራይን ቢን ላደን የተሸሸጉበትን ሕንፃ አነስ ባለ ቦምብ ድምጥማጡን እናጥፋዉ ይሉ ገቡ።

«የዚያን ቀን ቢን ላደን እዚያ ባይኖርስ?» ጠየቁ ገሚሶቹ፥ «ቦምቡ መጣሉንስ ይጣል፥ ግን ቢን ላደን ሙሉ በሙሉ ቢጨፈለቅ ለመግደላችን ማረጋገጪያችን ምንድ ነዉ?» አሉ የተቀሩት።ሌሎቹ ደግሞ ሌላ-በርግ እንደፃፉት።ከስድስት ሳምንት ክርክር በሕዋላ ልዩ ኮማንዶ ጦር ይዝመት የሚለዉ ፕሬዝዳንቱ ያሉበት ቡድን ሐሳብ አሸነፈ።እና ፕሬዝዳንቱ ዘመቻዉን አፀደቁ።ሚያዚያ ያሐ-ስምንት።

በትዕዛዙ መሥረት የዘመተዉ ልዩ ኮማንዶ ጦር ግንቦት አንድ-እሁድ ለሰኞ አጥቢያ አቦትአባድ ላይ ትልቁን ጠላት ገደለ ።

«ዛሬ በእኔ መመሪያ፥ ዩናይትድ ስቴትስ አቦታባድ በሚገኘዉ ሕንፃ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ዘመቻ አድርጋለች።ከዉጊያ በሕዋላ (ኮማንዶዎቹ) ኦሳማ ቢን ላደንን ገድለዉ አስከሬኑን ማርከዋል።ፍትሕ ተፈፀመ።»

አቦታባድ የሚሆነዉን ከዋይት ሐዉሱ የዘመቻ መከከታታይ ክፍል (Siruation Room) ሆነዉ ልዩ ካማራ በተገጠመለት ቴሌቪዥን ይከታተሉ ከነበሩት ጥቂት ባለሥልጣናት አንዷ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላፊ ክሊንተን «እንደዚያች ሰላሳ-ስምንት ደቂቃ» አሉ ኋላ «በሕይወቴ ተጨንቄ አላዉቅም።»

ዘመቻዉ የፈጀዉ ጊዜ አጭር ነበር።ላዝማቾቹ ግን አስጨናቂ ።ከ1998 ጀምሮ ሳዑዲ አረቢ፥ ሱዳን፥ ፓኪስታን፥ አፍቃኒስታን ላይ ከተቃጣባቸዉ ያየር የምድር ጥቃት ያመለጡት።የአመታቱን ወጥመድ፥ የቶራ ቦራዉን ከበባ በጥሰዉ የተሰወሩት ኦስማ ቢን ላደን በአርባ ደቂቃ ዉስጥ ተፈጠሙ።


ቢን ላደን አፍቃኒስታን በመሸሸጋቸዉ ሰበብ በዚያች ሐገር ላይ የተለኮሰዉ ጦርነት ግን አልረገበም። እዚያ በሰፈረዉ አሜሪካ መራሽ ጦር ላይ የሚፈፀመዉ ጥቃትም ከቢን ላደን መገደል በሕዋላ ጨመረ እንጂ አልቀነሰም።

ኢራቅን ዕለት በዕለት የሚያሸብር፥ የሚጠፋዉ ሺዎችን የሚያረግፈዉ ጥቃት ቀነሰ እንጂ አልቆመም። ጥቃቱ የቀነሰዉም በቢን ላደን መገደል አይደለም።ከመገደላቸዉ በፊት በተለይ አሜሪካ ጦሯን እንደምታስወጣ ቃል ከገባች በሕዋላ ነበር።ጀርመናዊዉ የሽብር ጉዳይ አጥኚ ጊዶ ሽታይንበርግ እንደሚሉት ወትሮም በተዳከመዉ አል-ቃኢዳ ላይ የታየዉ ለዉጥ ቡድኑ ግርማ ሞገስ የነበረዉን መሪ ማጣቱ ብቻ ነዉ።

«የተለወጠዉ ነገር ቢኖር አንድ በጣም ተቃሚ የአመራር ስብዕና መወገዱ ነበር።አል-ቃኢዳ እስካሁን ድረስ የኦሳማ ቢን ላደንን ግርማ ሞገስ መተካት አልቻለም።»

ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የሐገራቸዉን ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ፥ የአፍቃኒስታንን ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ፥ ኹዋንታናሞን ለመዝጋት፥ ለአል-ቃኢዳ መመስረት እንደ ዋና ምክንያት የሚቆጠረዉን የእስራኤል-ፍልስጤሞችን ዉዝግብ ለማስወገድ የገቡት ቃል-ከቃል አላለፈም።

የሐገራቸዉን ቀንደኛ ጠላት ማስገደላቸዉን ከቃል-ላለፈዉ ድክመት መሸፈኛ፥ በተለይ ለሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን ለመመረጥ እንደ ጥሩ መቀስቀሻ መጠቀማቀዉ አላከራከረም።የመግሪብ አል-ቃኢዳ ከሰሜን አፍሪቃ አልፎ ምዕራብ አፍሪቃ ማሊ ድረስ የተስፋፋዉ ግን ከቢን ላደን መገደል በሕኋላ ነዉ።በተለይ ደግሞ ሊቢያ ስትመሰቀቀል ባገኘዉ ጦር መሳሪያ ነዉ።

«ቦኩ ሐራም» የተሰኘዉ የናይጀሪያዉ ቡድን የተለያዩ ከተሞችን ያሸበረዉ፥ በርካታ ሰዎችን የገደለዉ ቢን ላደን ከተገደሉ በሕዋላ ነዉ።የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ አል-ቃኢዳን መቀላቀሉን ያወጀዉ ከቢን ላደን መገደል በሕዋላ ነዉ።የመን ዉስጥ ተደራጅተዋል የሚባሉት የአል-ቃኢዳ ታጣቂዎች በርካታ ወረዳዎችን የተቆጣጠሩት ከቢን ላደን መገደል በሕዋላ ነዉ።

በየአካባቢዉ የሚገኙት ቡድናት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የአል-ቃኢዳ አካል እንደሆኑ፥ አል-ኢዳን እንደሚደግፉ ወይም የአል ቃኢዳን አላማ እንደሚያራምዱ አልካዱም።ይሁንና የአብዛኞቹ አለማ ብዙዎች እንደሚሉት ብሔራዊ፥ የመመሥረታቸዉ፥ ደጋፊ ተከታይ የማግኘታቸዉ ሰበብ ምክንያትም የየሐገሩ ፖለቲካዊ፥ ምጣኔ ሐብታዊ፥ ማሕበራዊና ሐይማኖታዊ ችግር ነዉ።

ቶፕሆፈን እንደሚሉት አሁን ደግሞ ቡድን፥ አዛዥ-መሪ ሳይኖራቸዉ በፈለጉት ጊዜ ብድግ ብለዉ የሚያሸብሩ ግለሰቦችም ብቅ-ብቅ እያሉ ነዉ።

«ለምሳሌ ቱሉዝ (ፈረንሳይ) በቅርቡ የተፈፀመዉን ጥቃት ብንመለከት በኢንተርኔት ወይም በሌላ መንገድ እራሳቸዉን ብቻ ወደ ፅንፈኝነት የሚለዉጡ የመኖራቸዉን ችግር በትክክል ጠቋሚ ነዉ።ማንም ሳያዛቸዉ፥ ምንም አይነት የሽብር ሕዋስ ሳይኖራቸዉ፣ በማንም በቀጥታ ሳይታዘዙ እርምጃ የሚወስዱ ሰዎች ይኖራሉ።»

እልቂት ግድያ ያልተለዉ የሽብር-ፀረ-ሽብር ዘመቻ ልዩነት ወትሮም እንደካራከረ ነዉ። ዓለም አቀፉ አሸባሪ ድርጅት ከተዳከመ፥ መሪዉ ከተደገደሉም በሕላ ዓለም ከሽብር ሥጋት ካልተላቀቀች ግን ሰዎችን ወደዚያ እርምጃ የሚዶላቸዉ ሰበብ ምክንያት ዳግም ሊጠን፥ የአሸባሪነት ብያኔም በትክክል ለቢየን እንደሚገባዉ ጠቋሚ ነዉ። «ዓለም አቀፍ ፀረ-ሽብር» የተሰኘዉ ዘመቻ ገድል-ድልም አጠያያቂ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ


















Osama bin Laden tot
ኒዮርክ ፌስታምስል AP
epa02714086 Pakistani Army soldiers secure the compound where Al-Qaeda leader Osama Bin Laden was killed by the US military forces in an operation, in Abbotabad, Pakistan on 02 May 2011. Osama bin Laden was killed 01 May in Abottabad, Pakistan in a shootout with US operatives, US President Barack Obama announced. EPA/T. MUGHAL +++(c) dpa - Bildfunk+++
አቦታባድምስል picture-alliance/dpa