1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ባን ኪሙን

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2009

ደቡብ ኮሪያዊው ባን ኪሙን በተችዎቻቸው ዘንድ የሚታወሱት፣ ቁርጠኛ አቋም ባለመያዝ እና የረባ ሥራ ባለማከናወን ነው። ብዙም ግርማ ሞገስ የሌላቸውም ይሏቸዋል።ለአድናቂዎቻቸው ግን የ71 ዓመቱ  ባን ሁሌም ተረጋግተው ኃላፊነታቸውን ሲወጡ የቆዩ መሪ ነበሩ።

https://p.dw.com/p/2UDZj
Schweiz UN-General-Sekretär Ban Ki-moon kommt in Mont Pelerin an
ምስል REUTERS/Pool/F. Coffrini

Bilanz Ban ki-Moon - MP3-Stereo

ባን ኪሙን ለስምንተኛው  የተመድ ዋና ጸሐፊነት ጥቅምት 2006 ዓም ተመርጠው ጥር1 2007 ዓም ነበር በይፋ ሥራቸውን የጀመሩት። በመካከሉ የቀድሞው የኢራቅ አምባገነን መሪ ሳዳም ሁሴን በጎርጎሮሳዊው ታህሳስ 30 ፣ 2006 ዓም በስቅላት ተቀጡ። በዚህ ወቅትም ባን ኪሙን ማንኛውም ሀገር የሞት ቅጣትን የመፈጸም ውሳኔ ላይ ሊደርስ ይችላል በሚል ውሳኔውን ሳይቃወሙ ቀርተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በጎርጎሮሳዊው 2003 ዓም የያዘቻቸውን ሳዳም ሁሴንን ፣ በ2004 ለኢራቅ የፍትህ አካላት ካስረከበቻቸው በኋላ በሰብዓዊነት ላይ ፈጽመዋቸዋል በተባሉ ወንጀሎች ነበር በስቅላት እንዲቀጡ በ2006 ዓም የተፈረደባቸው። ባን ኪሙን በወቅቱ የሰጡት መግለጫ የሚመሩት የተመድ ባወጣው የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር ላይ የሰፈረውን «የእያንዳንዱን ሰው የመኖር መብት»ን የሚቃረን በመሆኑ በዓለም ዙሪያ ቁጣ ቀስቅሶ ነበር። ባን ከፍተኛ ጫና ከተደረገባቸው በኋላም መግለጫቸውን ለማስተካከል ተገደው ነበር።  
ባን በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ያተኮሩት የድርጅቱን የተራራቁ አሠራሮች ማቀራረብ ላይ ነበር። ከርሳቸው በፊት ድርጅቱን የመሩት ጋናዊው ኮፊ አናን በዩናይትድ ስቴትስ ግፊት በ1997 የኃላፊነቱን ቦታ ቢያገኙም ለአሜሪካን ታማኝ ሆነው አልዘለቁም። አናን የተመድን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በማድረግ በአንድ ቃለ ምልልስ ላይ የኢራቁን ወረራ ሕገ ወጥ ሲሉ አውግዘዋል። በዚህ የተነሳም ያኔ ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትን ይሁንታ መጠበቅ ነበረባቸው። በአንጻሩ ባን ኪሙን ግን የዩናይትድ ስቴትስን አስተዋጽኦ ሲያወድሱ ነበር የቆዩት። ከዚያም ባን በገለልተኝነት በ2009 ማህሙድ አህመዲነጃድ የኢራን ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የመልካም ምኞት መግለጫ ልከውላቸዋል። ምርጫው ግን በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ከፍተኛ ማጭበርበር የተካሄደበት ነው በሚል ብዙ አወዛግቧል። የምርጫ ውጤትም በሀገሪቱ ህዝባዊ ተቃውሞ እና አመጽ አስነስቶ ነበር። በወቅቱም 4ሺህ የሚደርሱ የኢራን ዜጎች የታሰሩ ሲሆን 70 ያህል ተገድለዋል። በዚህ ወቅትም አንዳንድ ኢራናውያን ምሁራን ለተመድ አቤት ብለው ነበር። ባን ኪሙን ግን በዝምታ ነው ያለፉት። እነዚህን መሰል አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ጎን የሚገፋው የባን ኪሙን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ግልጽ ወጥቷል። በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው አወዛጋቢ የዓለም የፖለቲካ ጉዳዮችን በመተው በተመ አሠራር ላይ ብቻ ነበር ያተኮሩት። ብዙ ታዛቢዎች እንደሚሉት እንደ ኃላፊ የመተቸት እና የመውቀስ ድርሻቸው ስላልተመቻቸው ሁለተኛውን ዙር ኃላፊነት እስኪረከቡ ድረስ በአወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው ነበር። ይሁንና ባን ትናንት ሲሸኙ ባደረጉት ንግግር በዋና ጸሐፊነታቸው ዘመን ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን  ነው የተናገሩት፤ 
«ለኔ የተመድ የማይጨበጥ ወይም በትምህርት ብቻ የማውቀው አልነበረም። የህይወት ታሪኬ እንጂ ። ለሰዎች ክብር እና መብት ጥበቃ እንዲሁም ለጋራ የሰብዓዊነት ምሶሶዎቻችን ትኩረት ሰጥቻለሁ ። ዛሬ ለችግር ለተጋለጡት እና ለተረሱት ለመቆም ጥረት አድርጌያለሁ ። መጪው ትውልድ በሰላም እንዲኖር የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው። አሁን ለመልቀቅ በተዘጋጀሁበት ወቅት ከልጀነቴ አንስቶ እንደነበረው ልቤ ከተመድ ጋር ነው ።»
 ባን ኪሙን በሥልጣን ዘመናቸው ከልባቸው የገባ ነገር ቢኖር የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ነበር። በአንድ ወቅት ባን ባደረጉት ንግግር  « የአየር ንብረት ለውጥ በሰብዓዊ ፍጡሮች እና በምድራችን ላይ ያሳደረው ስጋት ከኒዩክልየር ጦርነት ስጋት ጋር የማይተናነስ ነው፤» ሲሉ ተናግረው ነበር ። ባን ኪሙን ይህን ያሉት ሥልጣን እንደያዙ በ2007 ቢሆንም መንግሥታት የዓለም ሙቀት መጠን እንዲቀንስ እርምጃዎችን ለመውሰድ የተስማሙት በ2015 ፓሪስ ላይ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ነው። ባን ኪሙን የፓሪሱን  ስምምነት በህይወታቸው እጅግ የተደሰቱበት ጊዜ መሆኑን ተናግረዋል። በቅርቡ ደግሞ «የአየር ንብረት ለውጥ አለ ብዬ አላምንም» የሚሉት ለዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጉዳዩን አሳሳቢነት እና በፍጥነት መፍትሄ የሚያስፈልገው መሆኑን ይረዳሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል ባን ኪሙን  ።

UN-Generalsekretär Ban Ki-moon
ምስል Picture-Alliance/M. Girardin/Keystone
Frankreich Straßburg Europaparlament Ban Ki Moon
ምስል picture-alliance/AP Photo/J.-F. Badias

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ