1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ታሪክ

ባያጅዳ፦ የሐውሳ ማኅበረሰብ መሥራች አባት

ሐሙስ፣ ግንቦት 30 2010

የናይጀሪያ የሐውሳ ማኅበረሰብ መሥራች አባት ተደርገው ይወሰዳሉ፤ ባያጅዳ ይባላሉ። እንደ አካባቢው ስነ-ቃል ከኾነ ባያጂዳ ኑሯቸውን በሰሜናዊ ናይጀሪያ ያደረጉ ዓረብ ናቸው። የእሳቸው ታሪክ ከትውልድ ትውልድ በቃል ሲነገር ቆይቶ ዛሬ ላይ ደርሷል። አንዳንድ ሰዎች ባያጂዳ በእውኑ የነበሩ ሰው ናቸው ሲሉ ሌሎች ይህን አይቀበሉም።  

https://p.dw.com/p/2yEjX
DW African Roots- Bayajida
ምስል Comic Republic

ባያጂዳ «የሐውሳዎች አባት»

የሐውሳ ማኅበረሰብ በቀድሞ ዘመን ወይፈኖችን ይጋልቡ ነበር ተብሎ ይነገራል። እናም ከአንድ ክፍለ ዘመን ቀደም ብሎ ለማኅበረሰቡ ፈረስ መጋለብ ያስተማሩ በሰሜናዊ ናይጀሪያ የሐውሳ ንጉሣዊ ግዛት የመጡት የዐረብ ልዑል ናቸው ይባላል በአፈ-ታሪክ። እኚህ ሰው ባያጂዳ ይባላሉ።  

ስለ ሰሜናዊ ናይጀሪያ የሐውሳ መንግሥት ምስረታ ሲነሳ የታሪኩ አስኳል የባያጂዳ አፈ-ታሪክ ነው። ኾኖም አፈ-ታሪኩ ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ የመጣው በቃል እየተነገረ ነው። በዚህም የተነሳ ባያጂዳ መቼ እንደኖሩ ወይንም ደግሞ በእርግጥም ምድር ላይ ስለመከሰታቸው በውል ለማወቅ ያዳግታል። እንደ አፈ-ታሪኩ ከኾነ ግን ልዑሉ ባያጂዳ ሕይወታቸውን መምራት የጀመሩት ዛሬ ኢራቅ በምትባለው ሀገር በባግዳድ ምድር ነው። ከወላጅ አባታቸው ጋር በመቃቃራቸው ነበር ጠንካራ ፈረሰኞችን አስከትለው ወደ አፍሪቃ ያቀኑት። መዳረሻቸውንም ያደረጉት ሰሜናዊ ናይጀሪያ ዳውራ ላይ ነበር። እዚያ እንደደረሱም ሀገሬውን ከውኃ ጉድጓዱ ውኃ እንዳይቀዳ እንቅፋት የኾነውን እባብ በሠይፍ መትረው ይገድሉታል። ለእዚህ ጀግንነታቸውም በሽልማት የዳውራ ንግሥትን ያገባሉ። ግን ይኽ ታሪክ በእርግጥ የውነት ነው? በናይጀሪያ፤ የታሆዉዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሠር አዶ ማሐማን ይጠራጠራሉ።   

DW African Roots- Bayajida
ምስል Comic Republic

"እንደሚመስለኝ ይኼን ለማረጋገጥ ሳይንቲስቶች እና የቅሪተ-አካል አጥኚዎች የውኃ ጉድጓዱ ድረስ መሄድ ያስፈልጋቸዋል። ጉድጓዱ ይህን ያኽል ጊዜ ነበር የሚለውን እውነታም ለመወሰን በስፍራው ተገኝተው መመርመር ያሻቸዋል። ምክንያቱም የውኃ ጉድጓዱ ባለበት አካባቢ ሁለት ጅረቶች ይፈሳሉ። ያ ደግሞ በአካባቢው የውኃ እጥረት ነበር፤ ውኃውም በፍለጋ የሚገኝ ነበር የሚለውን ነገር ዜሮ ያስገባዋል።   

ታሪኩ እውነትም ኾነ የፈጠራ የሐውሳ ትውፊት ግን ተመስርቶበታል። አፈ-ታሪኩ እንደሚለው መጀመሪያ ላይ ባያጂዳ እና የዳውራ ንግሥት ልጆች ማፍራት አልቻሉም ነበር። እናም ንግሥቲቱ ለባያጅዳ ቅምጥ (ውሽማ) ይሰጣሉ። ሁለቱም ሴቶች ታዲያ ያረግዙና ወንዶች ልጆችን ይወልዳሉ። የንግሥቲቱ ልጅ ስድስት ወንዶች ልጆችን ይወልዳል። ይኽ ልጅ እና የልጅ ልጆቹ በአንድነት ዛሬ ሕጋዊ የሚባሉትን ሰባቱን የሐውሳ ግዛቶች አስተዳድረዋል። የቅምጧ ልጅ በበኩሉ ሰባት ልጆችን ያፈራል። እነሱም አናሳ ወይንም ሕገ-ወጥ የሚባሉትን የሐውሳ ግዛቶች መርተዋል።      

ባያጂዳ የሐውሳ ግዛቶች ታሪክ ማጠንጠኛ እንደመሆናቸው መጠን ምሥጢራዊ በኾነ መልኩ በዓረብ ተጓዦች ዶሴዎች ላይ ግን የተመዘገበ ነገር የለም። ያም በመኾኑ ፕሮፌሰር አዶ ማሃማን ይኽ የሐውሳ ትውፊት የተመሰረተው ፈጠራ ላይ ነው ባይ ናቸው።    

"ከዚህ ታሪክ መዘን የምናወጣው ብቸኛው ነገር ቢኖር የሐውሳ አሚሮች ስለራሳቸው ለየት ያለ መነሻ ለመስጠት የኾነ ያልተለመደ ነገር መፈለጋቸውን ነው። ያን በማድረግም እኔ እኮ የባያጂዳ ዘር ነኝ ማለት ይችላሉ።

DW African Roots- Bayajida
ምስል Comic Republic

አንዳንዶች ይህ አፈ-ታሪክ በ16ኛው እና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መካከል ተፈጠረ ይላሉ። የሐውሳ ባሕል መረጃ ግን እስከ 10ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ብቻ ወደ ኋላ ይጓዛል። የፈለገው ቢባል ግን ባያጂዳ ዛሬ በደብዛዛው ይታወሳሉ፤ በሐውሳ ባሕል ውስጥም የፈረስ ግልቢያ ጨዋታ ስነ-ሥርዓት ዛሬም ድረስ ትልቅ ስፍራ አለው።  

ፒናዶ አብዱ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.