1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብልፅግና ፓርቲ በይፋ መመዝገቡን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 15 2012

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሦስቱ የኢሕአዴግ አባላት እና አምስቱ አጋር የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈርሰው የመሠረቱት ብልፅግና ፓርቲ በይፋ መመዝገቡን አስታወቀ።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩንኬሽን አማሪ ሶሊያና ሽመልስ «ከዛሬ በኋላ ብልፅግና የሚባለው ፓርቲ እውቅና አለው ማለት ነው» ሲሉ በይፋ መመዝገቡን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

https://p.dw.com/p/3VK6W
Äthiopien EPRDF
ምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

ስምንቱ መስራች ፓርቲዎች በይፋ መፍረሳቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አረጋግጧል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሦስቱ የኢሕአዴግ አባላት እና አምስቱ አጋር የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈርሰው የመሠረቱት ብልፅግና ፓርቲ በይፋ መመዝገቡን አስታወቀ።

ቦርዱ ስምንቱ ፓርቲዎች «በተናጠል በጠቅላላ ጉባኤያቸው ውሳኔ መሠረት አድርገው ውህደቱን ለመቀላቀልና ፓርቲያቸውን ለማክሰም የወሰኗቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ውህደቱን ለመመስረት ያደረጉትን ስምምነት በሙሉ ሕጉን ተከትሎ የተፈጸመ በመሆኑ ቦርዱ ፓርቲዎቹ ተሰርዘው ብልጽግና ፓርቲ የእውቅና ሰርተፍኬት እንዲሰጠው» መወሰኑን በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩንኬሽን አማሪ ሶሊያና ሽመልስ «ቦርዱ ዛሬ ወስኗል። ከዛሬ በኋላ ብልፅግና የሚባለው ፓርቲ እውቅና አለው ማለት ነው» ሲሉ በይፋ መመዝገቡን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

በውሳኔው መሠረት ላለፉት ከሁለት አስርት አመታት በላይ ኢትዮጵያን ያስተዳደረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢሕአዴግ በይፋ ፈርሷል።

እሸቴ በቀለ ሸዋዬ ለገሰ