1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሔርተኛ ንቅናቄ ለአማራ

ሐሙስ፣ ሰኔ 7 2010

ከሰሞኑ አንድ ብሔር ተኮር ንቅናቄ መቋቋሙ ይፋ ሆኗል። ባህርዳር ላይ በተካሄደ ሕዝባዊ ስብሰባ መመሥረቱ ይፋ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በምህፃሩ አብን ፤ የአማራን ሕልውና ለመታደግ ያለመ መሆኑን የንቅናቄው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2zaTx
20.06.2013 DW Online Karten Basis Aethiopien spanisch

«የአማራን የህልውና ስጋት ለመከላከል»

መመሪያው «አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ» ነው። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ። ከሰሞኑ ባህርዳር ከተማ በሙሉአለም አዳራሽ በተካሄደ ሕዝባዊ ስብሰባ አንድ ብሔር ተኮር ንቅናቄ መቋቋሙ ይፋ ሆኗል። አቶ ክርስቲያን ታደለ አዲስ የተቋቋመው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። ብሔርን መሠረት ያደረገ ፓርቲ ማቋቋም ለምን አስፈለገ የሚለው ጥያቄ ከተለያዩ ወገኖች እንደሚቀርብላቸው በመጥቀስ ምክንያት ያሉትን እንዲህ ያስረዳሉ።

«ሀገራችን ላለፉት 27 ዓመታት በብሔር ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀት የተዋቀረች ነች። በዚህ ሂደት አሁን የእኛ ፓርቲ እስኪመሠረት ድረስም አማራ በዜግነት የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ራሱን እያደራጀ የኖረ ሕዝብ ነው። ይሁን እና በዜግነት የፖለቲካ መዋቅር እና አደረጃጀት ውስጥ መሳተፉ አማራው የሕልው ጥቅሞችን፤ ዘላቂ ጥቅሞች እና መብቶችን ሊያስከብርለት ስላልቻለ እና እውነተኛ ወካይ ፓርቲ ስላላገኘ ይህንኑ በመረዳት እና አማራው የሚደርስበትን የሕልውና አደጋ ለመቀነስ በማሰብ ነው ይህን ፓርቲ ያደራጀነው።»

በምሕጻሩ አብን የተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲ መሆኑን የገለፁልን የሕዝብ ግንኙነቱ ኃላፊ በዋናነት ንቅናቄው ለአማራ ሕዝብ በየደረጃው የሚወከልበትን፤ ከክልሉ ውጭ ባሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በራሱ ቋንቋ የሚዳኝበትን፤ ቋንቋ እና ባህሉን የሚጠብቅበት ነፃነት የሚያገኝበትን፤ በመረጠው የሥራ መስክም ተሰማርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን የማረጋገጥ ተግባራትን እንደሚያከናውን ዘርዝረዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ተነጣጥሏል ያሉት የአማራ ሕዝብ እና ግዛታዊ አንድነቱ ተበፖለቲካው መሬቶቹ ወደተለያዩ ክልሎች መወሰዳቸው፤ አማራው በሀገር ግንባታ ውስጥ ያበረከተው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ተዘንግቶ አሉታዊ ትርክት በመነዛቱ በየሄደበት መፈናቀሉ እና ይህ የሕልውና አደጋ ሀይ ባይ ማጣቱ በሀቀኝነት የአማራን ሕዝብ ለመወከል በፓርቲነት ተመደራጅተው  ለመሥራት መወሰናቸውንም አስረድተዋል።

Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

ንቅናቄያቸውም ሕጉ በሚጠይቀው መሠረት በምርጫ ቦርድ እውቅና ለማግኘት ሂደት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል። በአባልነትም ነሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ አማሮችን ያቀፈ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ላለፉት 27 ዓመታት ከሀገራዊ አንድነት ይልቅ ብሔር ብሔረሰብ ላይ ያተኮረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነግሶባት በቆየችው ምድር ካለፉት ሁለት ወራት ገደማ ወዲህ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እንደ አዲስ መሰበክ ጀምሯል። ይህም የብዙዎችን የሻከረ መንፈስ እየሞረደ ተነጣጥሎ ከማሰብ ይልቅ ስለጋራ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወደማለም መጋበዙ እየታየ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ከሀገር አንድነት ጋር ተገናኝቶ የሚታየው አማራ በብሔር ለመደራጀት መነሳቱ ትኩረት መሳቡ፤ ግርምት ድንግር መፍጠሩ ይታያል። የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይጣላም ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ ግን  ሌላው ብሔር በተቋቋሙ ፓርቲዎቹ አማካኝነት ጉዳት ችግሩ ይሰተጋባለታል፤ አማራው ይሕን በማጣቱ ተጎድቷል ነው የሚሉት።

«በመሠረታዊነት የአማራ ብሔርተኝነትም ሆነ ይህን ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰው አዲስ የተቋቋመው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከሌሎች የብሔርተኛ እንቅስቃሴዎችም ሆነ ብሔርተኛ ንቅናቄ አራማጆች የሚለይበት አንድ ዐቢይ ነጥብ አለ። ይኸውም ምንድነው በጥላቻ ፖለቲካ አራማጅ አይደለም።»

ለፓርቲው ምሥረታም ደግመው ደጋግመው የሕልዉና አደጋው ዋና መንስኤ መሆኑን ነዉ ያስረዱት።  ብሔር ላይ ያተኮረ የአማራ ድርጅት መቋቋሙ አስፈላጊ ነው የሚለው ሀሳብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅብረተሰቡ መካከል ሲንሸራሸር መቆየቱን ያመለከተዉ የድረገጽ ፀሐፊ በፈቃዱ ኃይሉ ሀሳቡ አሁን ተቀባይነት ያገኘ መምሰሉን አስተውሏል።

Fasil Schloss Gonder Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

«ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አማራ በብሔሩ መደራጀት አለበት የሚለው አስተያየት እያመዘነ እያመዘነ መጥቶ አሁን ከሞላ ጎደል የበለጠ ተቀባይነት ያለው መስሏል። ቢያንስ በእኔ ግምገማ ማለት ነው። በእኔ የግል አተያይ ግን በብሔር መደራጀት በአማራ አልተጀመረም ሁሉም ክልል በብሔር የተደራጁ አሉት። በአሁኑ ሰዓት ጠንካራ የሚባል የብሔር ድርጅት የለም። ከዚህ አንፃር የአማራ ሕዝብን ወይም ክልልን ብል እመርጣለሁ ጥቅም ለማስከበር ሲባል መመስረቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በጠቅላላው በብሔር መደራጀት የግድ አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም አንዱ ብሔር ወይም አንዱ ክልል ውስጥ ያሉት ችግሮች በሙሉ ሌላውም ክልል አሉ። እና እውነተኛው መፍትሄ የሚገኘው በሆነ ርዕዮተዓለም ወይም ደግሞ የሆነ ግብ ይዞ በመነሳት ነው።»

ከፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሞት በኋላ ለአማራ ሕዝብ የሚሟገት እውነተኛ ድርጅት አልነበረም የሚሉት የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ግን ድርጅታቸው የጥላቻ ፖለቲካ እንደማያራምድ እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረውን የአማራ ሕዝብ መብት ለማስከበር እንደሚንቀሳቀስ አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ