ብሩህ ተስፋ ሰጪው የቡና ገበያ

የመንገድ ቡና

በአዲስ አበባ በየቀኑ የሚከወነው የቡና ንግድ ግልጽ የሆነ የራሱ ቅደም ተከተል አለው። ከታች ያለውን ብንወስድ፤ ሴቶች ቴርሙዝ፣ ስኒዎች እና የስኒ ማስቀመጫዎችን ሸክፈው በየጎዳናው ይዘዋወራሉ። አንድ ስኒ ቡና ሦስት ብር ነው፤ ቡና እያፈላች በመሸጥ የምትተዳደረው ሊያ በቀን እስከ 40 ብር እንደምታገኝ ትገልጣለች። በሥራዋ ደስተኛ ናት።

የተሻለ ሕይወት የመምራት ዕቅድ

አስቴር እንዳለ አናት በሚሰረስረው ፀሐይ ቀኑን ሙሉ ስትለበለብ ትውላለች። ወደፊት እንደምንም ብላ ቡና እያፈላች የምትሸጥበት የራሷ ቋሚ ቦታ እንዲኖራት ትሻለች። ምኞቷ ምግብ ቤት ወይም ቡና ቤት ውስጥ የጀበና ቡና መሸጥ ነው።«ማንም ቢሆን የተሻለ ሕይወት ለመምራት ነው የሚያቅደው፤ እኔስ ታድያ የመስራት ትርፌ ምኑ ላይ ነው?» ስትል የ18 ዓመቷ ወጣት ትጠይቃለች።

በፈገግታ ማስተናገድ

«ሁሌም በጥሩ መንፈስ ስለሆነ የማስተናግደው፣ በዚያ ላይ ባሕላዊ የቡና ሥርዓትን በልዩ ሁናቴ ስለሆነ የሚመለከቱት ደንበኞች ይመጣሉ» ትላለች የ19 ዓመቷ ወጣት እየሩሣሌም መሠለ። የጀበና ቡና የምትሸጠው ከአንድ ቡና ቤት አጠገብ ሆና ነው። በወር 700 ብር ታገኛለች። «አንድ ቀን የራሴን ቡና መሸጫ ቤት ለመክፈት ስል ገንዘቤን እያጠራቀምኩ ነው» ትላለች።

የውጭ ሀገር ናፍቆት

ከአንድ ሆቴል አጠገብ በዘረጋችው የጀበና ቡና ንግድ የምትተዳደረው የ21 ዓመቷ ወጣት ሮዛ መለሰ ደግሞ «ኩዌት የምትኖረው ዘመዴ እዚያ የሥራ ፈቃድ እንዳገኝ እየረዳችኝ ነው» ትላለች። ቡና አፍልቶ በመሸጥ በወር እስከ 1000 ብር ታገኛለች። ኩዌት ስትሄድ የበለጠ ገንዘብ እንደምታገን ተስፋ አላት። ከዚያም ኢትዮጵያ ውስጥ የራሷን ንግድ ተቋም መክፈት ነው የምትፈልገው።

ሆቴል የመክፈት ሕልም

ሮዛ መለሰ በባሕላዊ መንገድ ቡና ሲቀዳ እንደሚሆነው ክርኗን በእጇ ደግፋ በተረጋጋ መንፈስ ቡናውን እየቀዳች ነው። የሥራ ፈቃድ ካገኘች በሚቀጥለው ግንቦት ወር ወደ ኩዌት በማቅናት ሰው ቤት ተቀጥራ ለአራት ዓመት ግድም መሥራት ነው ፍላጎቷ። ህልሟ አንድ ቀን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆቴል ቤት መክፈት እና መኪና መግዛት ነው።

ባሕሉን ወደ ውጭ ሀገር ማስፋፋት

በቡና አፍልቶ መሸጥ ከፍተኛ ደረጃው እንደ ቶሞካ ያሉ የቡና መሸጫ ቤቶችን ማቋቋም ነው። እጎአ ከ1953 ዓም አንስቶ ደንበኞች ጥሩ ማዕዛ ካለው ቡና ጋር ተላምደዋል። «አሁን የታሪካችን አንዱን ክፍል የመቀየሪያው ትክክለኛው ጊዜ ነው» ይላሉ የቡና ቤቱ ባለቤት አቶ ወንድወሰን መሸሻ። ምኞታቸው ቡና በሌሎች የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት እንዲሁም በአውሮጳ እና እስያ ውስጥ መሸጥ ነው።

አዲስ የማጣጣም ልማድ

የቡና መቁያዎች እና ቡና ቤቶች የመስፋፋታቸው ነገር አዲስ አይነት የአጠጣጥ ልማድ ብቅ ማለቱን ያሳያል። «እቤት ውስጥ ለአንድ ሠዓት ቁጭ ብለው ቡና ለመቁላት ጊዜ የለህም» ይላሉ ዓለም ቡና በተሰኘው ቡና መሸጫ ድርጅት የገበያ ጉዳዮች የሚመለከታቸው አቶ ጌታቸው ወልደጻዲቅ። እሳቸውም ቢሆኑ ንግዱን በሌሎች የምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት፣ አውሮጳ እና እስያ ማስፋፋት ይፈልጋሉ።

የምዕራብ ሀገራት ተፅዕኖ

«ካልዲስ ቡና» በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ጎዳናዎች አንዱ በሆነው የቦሌ መንገድ ላይ ይገኛል። እዚህ ቡና የሚጠጡት በተለይ የውጭ ሃገራት ሰዎች እና ወጣቶች ናቸው። ባለቤቱ የድርጅቱን አርማ አረንጓዴ እና ነጭ የማድረጉ ሐሳብ የፈለቀላቸው ዩናይትድ ስቴትስ ሄደው ስታር ባክስ የተባለውን የቡና መሸጫ ካዩ በኋላ ነው።

የሚባክን አንዳች ጊዜ የለም

አስቴር እንዳለ ስኒዎቹን ካጣጠበች በኋላ በፍጥነት ወደ ዘንቢሏ በመክተት የሚቀጥሉት ደምበኞቿ ወደሚገኙበት ቦታ ለመሄድ መንገዱን እያቋረጠች ነው። ጊዜ አባከነች ማለት ሸጣ የምታገኘው ገንዘቧም ቀነሰ ማለት ነው። አስቴር ከአንዱ ምግብ ቤት ወይም ቡና ቤት አጠገብ ቦታ ተከራይታ የጀበና ቡና የምትሸጥበት በቂ ገንዘብ ገና አላጠራቀመችም።

በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ በየቀኑ የሚቀዳው እያንዳንዱ ስኒ ቡና፥ በተለይ ሴቶች ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ በማድረጉ ረገድ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ትንሽም ቢሆን የሚፈይደው ነገር አለ።