1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት የመውጣት ይፋ ጥያቄ

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2009

ብሪታንያ ባለፈው ሰኔ ወር ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት ለመውጣት በወሰነችው መሠረት፣ ይህንኑ ኅብረቱን ለቆ የመውጣት ፍላጎትዋን ዛሬ ለኅብረቱ ባቀረበችው ደብዳቤ በይፋ አስታውቃለች። ኅብረቱን ከ40 ዓመት በኋላ ለቃ መውጣት የምትችልበትን ሂደት እንድትጀምር የሚጠይቀውን ደብዳቤ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ተሪዛ ሜይ ትናንት ማታ ፈርመዋል።

https://p.dw.com/p/2aFyo
EU Großbritannien Brexit Brief Botschafter Barrow mit Tusk
ምስል Getty Images/AFP/Y. Herman

M M T/ Ber. London(Britain strikes historic blow to EU) - MP3-Stereo

ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት እንደምትወጣ ያሳወቀችበትን ደብዳቤ ዛሬ ለኅብረቱ አቀረበች። የብሪታኒያ ከፍተኛ ልዑክ ቲም ቦሮው ደብዳቤውን ለአውሮጳ ኅብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ ዛሬ ጠዋት ለአስረክበዋል። ባለስድስት ገጹን ማሳወቂያ የተቀበሉት ቱስክ የብሪታንያ መውጣት ቢያሳዝንም ቀሪዎቹን አባል ሃገራት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድ ማድረጉን ተናግረዋል።
«ብራስልስም ሆነ ለንደን ውስጥ ዛሬ የሚያስደስት ቀን ነው ብሎ ለማስመሰል ምንም ምክንያት የለም። ግማሽ ያህል የሚሆነው የብሪታንያ ድምጽ ሰጭ እና አብዛኛው አውሮጳዊ ከመለያየት ይልቅ አንድ ላይ ሆነን ብንቀጥል ነበር ሞኞታቸው። ስለዚህ እኔ ዛሬ ደስተኛ ነኝ ብዮ አላስመስልም። በተቃራኒው ግን የብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት መውጣት (ብሬግዚት) በጎ ነገርም አምጥቷል። 27ቱን የኅብረቱን አባል ሃገራት ከቀድሞው ይበልጥ ቁርጠኛ አና አንድ አድርጓል። »
የመልቀቂያ ደብዳቤውን ትናንት ፈርመው የላኩት የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ዛሬ ለሀገራቸው ምክር ቤት አባላት ባሰሙት ንግግር መንግሥታቸው በሕዝቡ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎት መሠረት እርምጃውን መውሰዱን አስታውቀዋል። ከአሁን በኋላ ወደ ኋላ መመለስ የለም ያሉት ሜይ፤ ሆኖም ሀገራቸው ከኅብረቱ ጋር በተለያዩ መስኮች በአጋርነት የምትሠራበትን እቅድ ከኅብረቱ ጋር ለሚካሄደው ድርድር እንዳዘጋጁ ተናግረዋል።
«እቅዱ በብሪታንያ እና በአውሮጳ ኅብረት መካከል አዲስ ጥልቅ እና ልዩ አጋርነት የሚጠይቅ ነው። እሴቶችን መሠረት ያደረገ አጋርነት፣ ጥቅሞችን የተመለከተ አጋርነት፤ እንዲሁም ፀጥታ እና የኤኮኖሚ ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ አጋርነት ነው፤ ለብሪታንያ፣ ለአውሮጳ ኅብረት እና ለተቀረው ዓለም የተሻለ ጠቀሜታ ሊሠራ የሚችል አጋርነት። »
የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ ሜይብሪታንያ እና የአውሮጳ ህብረት በአጋርነት የሚቀጥሉበት እቅድ  ከድርድሩ ጎን ለጎን እንደሚነሳ የተናገሩትን ተቃውመዋል ። ሜርክል እንዳሉት የሁለቱ ወገኖች የወደፊት ግንኙነት ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት እንዴት እንደምትነጠል ግልጽ ከተደረገ በኋላ ሊነሳ የሚችል ጉዳይ ነው ብለዋል ። ላለፉት 40 ዓመታት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሆና የዘለቀችው ብሪታንያ ከኅብረቱ የምትወጣበት ድርድር ማብቂያ የ24 ወራት የጊዜ ገደብ ተቀምጦለታል። ቱስክ ረቂቅ የድርድሩን መመሪያዎች  ለ27 ቱ አባል ሃገራት እስከ ዓርብ ያቀርባሉ። የአውሮጳ ኅብረት ዋነኛ ተደራዳሪ ፈረንሳዊው ዲፕሎማት ሚሼል ባርንየ እና የብሪታንያው አቻቸው ዴቪድ ዴቪስ ከመጪው ግንቦት አጋማሽ በኋላ መነጋገር ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

Großbritannien Theresa May Brexit Rede im Parlament
ምስል Reuters

ድልነሳው ጌታነህ

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ