1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብራስልስ፤ ስድስት ተጠርጣሪዎች ተያዙ፤ አሰሳዉ ቀጥሏል

ዓርብ፣ መጋቢት 16 2008

የቤልጅግ ፖሊስ በዋና ከተማዋ ከደረሰዉ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ ስድስት ተጠርጣሪዎችን ያዘ። አሁንም ግን በደህንነት ካሜራዉ የታዩትን ፍለጋዉና አሰሳዉን ቀጥሏል። በብራስልስ ከተማ የሸርቤክ ከንቲባ ዛሬ በቀጠለዉ አሰሳ ከተያዙት አንዱ እግሩን በጥይት መመታቱን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/1IK1e
Brüssel Schaerbeek Polizei bewacht Strassensperre während Razzia
ምስል picture-alliance/AP Photo/A. Grant

ከዚህም ሌላ በፍተሻዉ ወቅት የተዘጋጁ ቦምቦችን ለማክሸፍ በርከት ያሉ አነስተኛ ፍንዳታዎችም እንደነበሩ አመልክተዋል። በአሰሳዉ 15 ኪሎ ከባድ ፈንጂዎች እና ፈንጂ መሥሪያ ንጥረ ነገሮች እንዲሁም እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን መለያ ሰንደንቅ ዓላማም ተገኝቷል። የቤልጅግ ፖሊስ የሚያካሂደዉ ፍተሻና አሰሳም ብራስልስ ብቻ ሳይሆን በተገኘዉ መረጃ መሠረት ፓሪስ ላይ ጥቃት ያደረሰዉን ቡድን ሰንሰለት የተከተለ መሆኑም ተገልጿል። ፖሊስ ከትናንት አንስቶ ፍተሻዉን ሲያካሂድ አካባቢዉ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከአካባቢዉ ኗሪዎች አንዱ ትናንት ማምሻዉን የገጠመዉን እንዲህ ገልጿል።

Belgien Brüssel Bewaffnete Polizisten patrollieren Strassen
ምስል picture-alliance/dpa/O. Hoslet

«ከትምህርት ቤት ስመጣ አካባቢዉ በሙሉ ተዘግቶ ደረስኩ። ስለዚህ ወደ ቤቴ መግባት አልቻልኩም፤ ብጠይቅም ፖሊስ እዚህ የሚሠራዉ ነገር አለ ተባልኩ። በትክክል ግን ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላወቅኩም። እዚህ ቅርብ ፍተሻ ከሚካሄድበት ከ20 ቁጥር ቀጥሎ የሚገኘዉ 14 ቁጥር ዉስጥ ነዉ የምኖረዉ።»

ፖሊስ የጀመረዉ የተጠናከረ አሰሳ እና የዩናይትድ ስቴትስ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የብራስልስ ጉብኝት በወረደባቸዉ ትችት ምክንያት ስልጣን ለመልቀቅ የተዘጋጁት ሁለት የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሃሳባቸዉን እንዲሰርዙ ማድረጉም ተገልጿል። ኬሪ የአሜሪካን ፌደራል የምርመራ ቢሮ FBI የቤልጅግ ፖሊስ በሚያካሂደዉ የወንጀል ምርመራ እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የፈረንሳይ ባለስልጣናትም በዛሬዉ ዕለት የሽብር ጥቃት ማክሸፋቸዉን አመለከቱ። ጥቃቱን ሊያደርስ የነበረዉ ተጠርጣሪዉ ባለፈዉ ኅዳር ፓሪስ ላይ የተፈጸመዉ የሽብር ጥቃት ሠንሰለት ከመራዉ አብደልሃሚድ አቡድ ጋር ቤልጂየም ዉስጥ ክስ ተመስርቶበታል። የ34ዓመቱ የፈረንሳይ ዜጋ ረዳ ክሪክት በፓሪስ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ትናንት ነዉ የተያዘዉ። ፖሊስ ክላሽንኮቭ እና ለጓዳ ሠራሽ ፈንጂ መቀመሚያ የሚሆን ንጥረ ነገር ከበርካታ የጦር መሣሪያዎች ጋርም አግኝቷል። የፈረንሳይ የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር የከሸፈዉ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም የተቃረበ ነበር ብለዋል።

Frankreich Festnahmen Terrorverdächtige in Argenteuil
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Mori

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ