1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብራዚል እና የስደተኛ ልጆች ፖለቲካ

ሰኞ፣ ግንቦት 8 2008

የኬንያዊዉ ልጅ ሥልጣን በያዙ በሰባተኛዉ ዓመት የጀርመኑ ስደተኛ ልጅ ሙስሊም እና ስደተኛ ባይኔ እንዳላይ ይሉ ገቡ።ትራምፕ ስደተኞችን በግንብ፤ ሙስሊሞችን በመግቢያ ፍቃድ ለማገድ ሲዝቱ፤ የፓኪስታኑ ሙስሊም ስደተኛ ልጅ፤ ሳዲቅ ካሕን የለንደን ከንቲባ ሆኑ።የቡልጋሪያ ስደተኛዋ ልጅ ከሥልጣን ሲታገዱ፤ የሊባኖሱ ስደተኛ ልጅ ሥልጣን ያዙ

https://p.dw.com/p/1Ion1
ምስል Getty Images/I. Estrela

[No title]

የብራዚል ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት ያሳለፈዉ ዉሳኔ ብራዚሎችንእሁለት ከፍሎ ገሚሱን ሲያፈነድቅ የተቀረዉን በሐዘን-ቁጭት አኮማትሯል።ለአሜሪካ ፖለቲከኞች በርግጥ አስደሳች ነዉ። ለዶናልድ ትራፕ ግን ዉሳኔዉ በዘር፤ቀለም ሐይማኖት ጥላቻ ከተሞላ መርሐቸዉ ጋር መጣጣሙ አጠራጣሪ ነዉ።ሊባኖሶችተደስተዋል።ቡልጋሪዎች ሳይዝኑ አልቀረም።የመካከለኛዉ ምሥራቅና የምሥራቅ አዉሮጳ ትናንሽ ሐገራት በደቡባዊ አሜሪካዊቱ ትልቅ ሐገር፤ ትልቅ ፖለቲካዊ ቀዉስ ለመደሰት ማዘናቸዉ ፖለቲካዊ ምክንያት የላቸዉም።መደሰት ማዘናቸዉ ግን እርግጥ ነዉ።ለምን?የብራዚል ፖለቲካዊ ቀዉስ መነሻ፤ዉስጣዊና ዉጪያዊ ምክንያቱማጣቀሻ፤ እድምታዉ መድረሻችን ነዉ።

እንደ እግር ኳስ ጥበብ-ምጥቀቷ ሁሉ በአንደንዛዥ ዕፅ መደንዘዢያ-መነገጃነት የገነነችዉ፤ ከሳምባ ዳንስ መፍለቂያነቷ እኩል የወሮበላ-ነብሰ ገዳዮች መናኸሪያነቷ የደመቀዉ፤ ከዉበት-ፍቅር ተምሳሌትነቷ እኩል-የተዉሳክ-ቁሻሻ መከመሪያነቷ የተመሠከረላት ሐገር፤ ሥልጣኔ-ከባርነት፤ ፖለቲካ-ከሙስና፤ ዴሞክራሲ-ከጭቆና፤ፍትሕ-ከአድሎ፤ ልማት-ከጥፋት ሲጋጭባት በርግጥ አዲስ አይደለም።ብራዚል።

ዛሬ ፌደራል ሪፐብሊክ ብራዚል ነዉ-ይፋ ስሟ።በቆዳ-ሥፋትም፤ በሕዝብ ብዛትም ከዓለም አምስተኛ ናት።ከደቡብ አሜሪካ ሐገራት ትልቋም-ሐብታሟም እሷዉ ናት።ከ1990ዎቹ ማብቂያ እስከ 2010 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ድረስ በምጣኔ ሐብት በፍጥነት በማደግ ከዓለም ቻይናን አስቀድማ ትከተል ነበር።የተፈጥሮ ሐብቷን ብዛት፤ አይነት፤ ዉበት-ሥብጥሩን መዘርዘር ሲበዛ አታካች ነዉ።

Brasilien Brasilia Dilma Rousseff
ምስል Reuters/U. Marcelino

ፖርቱጋላዊ ሐገር አሳሽ ፔድሮ አልቫሬስ ካብራል የመራቸዉ የነጭ፤ ካቶሊካዊት ፖርቱጋል ቅኝ ገዢ ወታደሮች እስከተቆጣጠሮት እስከ 1500 ዓመት ድረስ የተለያየ እምነት ተከታዮች፤ የተለያየ ነገድ አባላት፤በየአካባቢያቸዉ የየራሳቸዉን አስተዳደር መስርተዉ ይኖሩባት ነበር።ከሰወስት መቶ ዓመታት በላይ የዘለቀዉ የፖርቱጋል ቅኝ አገዛዝ፤የአዉሮጳ ሐይማኖትን ( ካቶሊክ ክርስትና)፤ የአዉሮጳ ዘርን-ነጭ የአዉሮጳ ፖለቲካዊ-ምጣኔ ሐብታዊ ሥርዓትን እና የአዉሮጳ ሥነ ልቡዊ አስተሳሰብን ተከለ።

የሐገሬዉ አንጡራ ተወላጅ ጉልበት ለአዉሮጳዉያኑ ሠፋሪዎች ባለመብቃቱ፤ ወይም ባለማርካቱ የሠፋሪዎቹን ፍላጎት ለማሟላት ጥቁር አፍሪቃዉያን በባርነት በገፍ-በግፍ የተጋዙትም ያኔ ነበር።ቅኝ ገዢዎች ከሊዝበን ቤተ-መንግሥት በቀጥታ መግዛታቸዉ በ1800ዎቹ መጀመሪያ ቢቋረጥም እንዴ ንጉስ፤ሌላ ጊዜ ጄኔራል፤ ደግሞ ሌላ ጊዜ ሪፐብሊካን እያሉ ያቺን ሰፊ፤ ዉብ፤ሐብታም ሐገር ከመቶ ዓመት በላይ የገዙት አምባ ገነኖቹ የቅኝ ገዢዎቹ ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ነበሩ።

በ1989 የብራዚል ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ በሰጠዉ ድምፅ ፕሬዝደንቱን መምረጡ የዘመነ-ዘመናቱ አምባገነናዊ፤ ወታደራዊ አገዛዝ የማብቃቱ እዉነተኛ ዲሞክራሲ የመፈንጠቁ አብነት ተደርጎ ነበር።ቀኝ ዘመሙ ፖለቲከኛ ፌርናንዶ ኮሎር (የድምፅ አሰጣጡ ሒደት ቢያወዛግብም) ሥልጣን የያዙት እዉቁን የግራ-ፖለቲካ አቀንቃኝ ሉዊስ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫን አሸንፈዉ ነበር።ይሁንና ፌርናንዶ ኮሎር ከሁለት ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ አልቆዩም።በሙስና ተጠርጥረዉ የሐገሪቱ ሕግ-መምሪያ ምክር ቤት (ኮንግረስ) እንዲከሰሱ ወሰነባቸዉ።ዉሳኔዉን ሕግ-መወሰኛዉ ምክር ቤት (ሴኔቱ) እንደሚያጸድቀዉ ሲያዉቁ ሥልጣናቸዉን በፈቃዳቸዉ ለቀቁ።1992።

በ24ኛ ዓመቱ ዘንድሮ ተራዉ በሉላ ደ ሲልቫ ጠንካራ ድጋፍ ሥልጣን የያዙት የግራ-ፖለቲከኛዋ የዲልማ ቫናሮዉሴፍሆነ።ሮብ።«ፕሬዝደንቷ በሕግ-መወሰኛዉ ምክር ቤት ክስ ይመሥረትባቸዉ የሚለዉን ሐሳብ ከምክር ቤቱ አባላት 55ቱ ደግፈዉታል።22ቱ ተቃዉመዉታል።»

ከ81ዱ የሕግ-መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ከሁለት ሰወስተኛ የሚበልጡት ባፀደቁት ዉሳኔ መሠረት ፕሬዝደቷ ለስድስት ወር ከሥልጣን ታግደዉ ምክር ቤቱ የሚወስነዉን መጠበቅ ግድ አለባቸዉ።ሮዉሴፍ የምክር ቤቱን ዉሳኔ «ዘመናይ መፈንቅለ መንግሥት» በማለት አዉግዘዉታል።የተያዘባቸዉን ሥልጣንን አለ አግባብ የመጠቀም ክስ ዉድቅ ለማድረግም እስከ መጨረሻዉ ድረስ እንደሚከራከሩም አስታዉቀዋል።

Brasilien Suspendierung Dilma Rousseff
ምስል Reuters/U. Marcelino

ይሁንና ምክር ቤቱ የወሰነዉን እንዳይወስን የሐገሪቱ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት እንዲያግደዉ የፕሬዝደንቷ ጠበቆች ያቀረቡትን ማመልከቻ ፍርድ ቤቱ ዉድቅ አድርጎታል።ፕሬዝደንቷ ከእንግዲሕ የሚከራከሩትም ከሥልጣን እንዲታገዱ በወሰነባቸዉ ምክር ቤት ላይ ነዉ።በዚሕም ምክንያት እስከ መጨረሻዉ የሚያደርጉት ሙግት ለድል መብቃቱ አጠራጣሪ ነዉ።ዋና ጠበቃቸዉ ሆሴ ኤድዋርዶ ካርዶሶ ሴትዋን ኑፁሕ ይሏቸዋል።የምክር ቤቱን ዉሳኔ ደግሞ ታላቅ ታሪካዊ ስሕተት።

«ከሳቸዉ በፊት ሥልጣን ላይ የነበሩ መሪዎች በሙሉ ያደረጉትን በማድረጋቸዉ፤ ሐቀኛ እና ምንም ጥፋት ያላጠፋች ንፁሕ ሴትን ከወነጀላችሁ፤ፕሬዝደንቷን ጥፋተኛ ለማድረግ በሕግ የተሰጣችሁን ሐላፊነት ከተጠቀማችሁ፤ እኔ ልንገራቸሁ፤ ታሪካዊ የሕግ መፋለስ ትፈፅማላችሁ።የዋሕ ሴትን ወንጅላችኋልና።»

ከፖለቲካዊ መርሕ እኩል የሐይማኖት ሐራጥቃ፤ የዘር፤የፆታ፤ ከሁሉም በላይ የደሐ-ሐብታሞች የጥቅም ልዩነት የሚነዳዉ ቀዉስ፤ ብራዚሎችን ግራ-ቀኝ ከፍሎ ሲያወዛግብ ዊኪሊክስ የተሰኘዉ ሚስጥር አጋላጭ አምደ-መረብ የበተናት ትንሽ መረጃ የብራዚል ቀዉስ ከብራዚል ብቻ የተነሳ-ብራዚል ላይ ብቻ የማይቆም እንደሆነ ጠቁማለች።

የዩንያትድ ስቴትስን ዲፕሎማሲያዊ መልዕክት ዋቢ የጠቀሰዉ መረጃ እንደሚለዉ የሮዉሴፍ ምክትል ያሁኑ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ሚካኤል ቴሜር የብራዚልን የሠራተኞች ፓርቲ ከሥልጣን ለማዉረድ አበክረዉ እንደሚጥሩ ገና በ2006 በብራዚል ለዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ቃል ገብተዉ ነበር።

የያኔዉ የብራዚል ፕሬዝደንት ሉላ ደ ሲልቫ ግን ለአሜሪካኖች ላደሩት ለነ ቴሜር ግፊት፤ሴራና ዘመቻ የሚበገሩ አልሆኑም።የዚያኑ ያክል እነ ቴሜርም ሮዉሴፍን የመሠሉ ደካማ መሪን ሾኬ መትተዉ የሠራተኛዉን ፓርቲ ከሥልጣን እስኪያስወግዱ ድረስ አድበዉ አልተቀመጡም ነበር።ሮብ ተሳካላቸዉ።

ከወግ አጥባቂ፤ ሐብታም ብራዚላዉያን እኩል የዋሽግተን ፖለቲከኞችም ተደሰቱ።ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ለመወዳደር የሪፐብሊካን ፓርቲን ዉክልና ያገኛሉ የሚባሉት ዶናልድ ትራምፕ ግን የቴሜር ትግል ለድል በመብቃቱ የሚደሰቱበት አመክንዮ የለም።ፖለቲካዉን በዶላር ክምር የሚሾሩት ትራምፕ-ስደተኛ ይጠላሉና።«ዩናይትድ ስቴትስ የማንም ችግር ማራገፊያ ሆናለች።እዚሕ ያላችሁት ጥሩዎቹና የፀዳችሁት ናችሁ።ሜክሲኮ ዜጎችዋን ወደኛ ስትልክ ጥሩዎቹን አትልክም።እናንተን አይደለም የሚልኩት።ብዙ ችግር ያለባቸዉን ሰዎች ነዉ የሚልኩት።ያንን ችግራቸዉን ይዘዉ ነዉ ወደኛ የሚመጡት።ደሕናዎቹን ሰዎች እይልኩም።የሚመጡት ከሜክሲኮ ብቻ አይደለም።የሚመጡት ከመላዉ የደቡብ እና የላቲክ አሜሪካ ምናልባትም ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ጭምር ነዉ።»

Brasilien Sao Paulo Gegner von Rousseff feiern die Zustimmung des Senats zur Amtsenthebungsklage
ምስል Imago/A. Mauricio

መካከለኛዉ ምሥራቅ።የብራዚሉ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ስደተኛ ተወላጅ ናቸዉ።ሚካኤል ሚጉል ቴሜር ሉሊያ።ሊባኖሳዊ አረብ።ትራምፕ ራሳቸዉ ጀርመን ስደተኛ ልጅ ናቸዉ።ያባታቸዉ ብጤ ስደተኛ አሜሪካ እንዳይገባ ምናልባት በርሊን ላይ ያዩትን ዓይነት አጥር ለማስገንባት ማቀዳቸዉን በሚደሰኩሩበት መሐል የአረብ ስደተኞቹ ልጅ፤ የብራዚሉ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት የሐገራቸዉ ጥቅም አራማጅ፤ሚስጥራዊ ወዳጅም መሆናቸዉን ዊኪሊክስ ያፈጋዉ።

ሊባኖሶች ግን ተደስተዋል።ወደ ሰሜናዊ ሊባኖሳዊቱ ከተማ ቤታአቦዉራ በሚወስደዉ ጎዳና ላይ የተፃፈዉ የመንግድ ሥም እስካለፈዉ ሐሙስ ድረስ «ምክትል ፕሬዝደንት ቴሜር» የሚል ነበር።«ነገ እንቀይረዋለን» አሉ የከተማይቱ ከንቲባ ባሳም ባርባር።«ነገ የቴሜር አዲስ ሥልጣን ይጨመርበታል፤ፕሬዝደንት የሚለዉ።በመሾማቸዉ በጣም ተደስተናል።ኮርተናልም።» አከሉ ከንቲባዉ።

የደስታ ኩራት ምክንያታቸዉ ፖለቲካዊ፤ ምጣኔ ሐብታዊ፤ ዲፕሎማሲያዊ፤ ሐይማኖታዊም አይደለም።ደም ከዉሐ ይወፍራል አይነት-እንጂ።ቴሜር በ1997 እና በ2011 የወላጆቻቸዉን የትዉልድ መንደር ጎብኝተዉ፤ ዘመዶቻቸዉን አነጋረዉ ነበር።ያኔ ያስተናገዷቸዉ የቅርብ ዘመዳቸዉ ኒዛር ቴሜር «አሁን እደገና ሊባኖስን ቢጎበኝ ማን ያስተናግደዋል» አሉ በቀደም።ምክንያት«እሱ ፕሬዝደንት ነዉ።እኛ ደግሞ ፕሬዝደንት የለንም።ማን ይቀበለዋል።» ጠየቁ ስልሳዎቹን ያጋመሱት ሊባኖሳዊዉ ቴሜር።ሊባኖሶች እንደ ቴሜር ተጠባባቂ፤ እንደ ትራምፕ እጩም እንደ ኦባማ ፕሬዝደንትም የላቸዉም።ሁለት ዓመታቸዉ።

ያም ሆኖ ቴሜር ሥለ ሊባኖስ ለማሰብ አሁን ጊዜ የላቸዉም።የመጀመሪያ ሥራቸዉ ተጠባባቂ የሚለዉን ቅፅል አዉልቀዉ ለመጣል የብራዚል ፖለቲከኞችን በዙሪያቸዉ መኮልኮል ነዉ።እስካሁን ድረስ ከወግ አጥባቂዎቹ በተጨማሪ አቺዮ ኔቬስን የመሳሰሉ የሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮች ቴሜርን ባይደግፉ እንኳን ሮዉሴፍን ስለሚጠሉ ከቴሜር የሚርቁ አይመስሉም።«ሐላፊነትን በመዘንጋት፤ እራስን ከሕግና ሥርዓት በላይ በማድረግ ስሜት በመነሳሳት ይሕ መንግሥት የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብታዊ የሚያናጋ፤ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ የሚያቃዉስ እርምጃ ወስዷል።ሐላፊነታችንን መወጣት አለብን።ነገ የሚጠብቀን ሌላ ቀን ነዉ።»

ሰዉዬዉ በ2014 በተደረገዉ የመለያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በፕሬዝደንት ሮዉሴፍ የተሸነፉ ናቸዉ።ፕሬዝደንቷ ምርጫዉን አጭበርብረዋል ባይም ናቸዉ።ሊባኖሶች ከተደሰቱ ቡልጋሪዎች ያዝኑ ይሆን። እንጃ? ብቻ ዲልማቫና ሮዉሴፍ በቅርቡ በልዩ ክብር ተቀብለዉ ካነጋገሩት መሪ አንዱ የቡልጋሪያዉፕሬዝደንት ሮሰን አሴቭፕሌቭኔሊቭን ናቸዉ። በፍጥነት የምታድገዉ ትልቅ ደቡብ አሜሪካዊት ሐገር መሪ የደሐ፤ትንሺቱን አዉሮጳዊ ሐገር አቻቸዉን በልዩ ክብር የማስተናገዳቸዉ ምክንያት ፖለቲካዊ ፤ምጣኔሐብታዊ፤ ዲፕሎማሲያዊም ነበር ማለት በርግጥ ከባድ ነዉ።ደም ከዉሐ ይወፍራል-እንበል እንጂ-እንደገና።ሮዉሴፍ የቡልጋሪያ ስደኛ ልጅ ናቸዉ።

Brasilien Vize-Präsident Michel Temer
ምስል Pressestelle/Michel Temer

ሮዉሴፍ የስደተኛ ልጅ ናቸዉ።ቴሜርም።ሮዉሴፍ ለደሆችና ለዝቅተኛዉ መደብ የቆመዉን ግራ-ዘመሙን የሠራተኛ ፓርቲ ይመራሉ።ቴሜር ባንፃሩ ወደ መሐል ቀኝ የሚያዳላዉ ፓርቲ መሪ ናቸዉ።ሁለቱ ፖለቲከኞች እንደ ስደተኛ ልጆችም፤ እንደ ብራዚላዊም፤ ፕሬዝደንትና ምክትል ሆነዉ ትልቂቱን ሐገር መምራት አልተሳናቸዉም ነበር።ዳር ግን አልዘለቁም።ሮዉሴፍ ቁልቁ ሲንሸራተቱ ቴሜር ሽቅብ ተንቻረሩ።

በሮዉሴፍ ካቢኔ ዉስጥ አንዲት ጥቁርን ጨምሮ ስድስት ሴቶች ነበሩ።በቴሜር-አንድም ጥቁር፤ አንድም ሴት የካቢኔ አባል የለም።ከሮሴፍ ጋር ብራዚልን ለ13 ዓመት የመራዉ የሠራተኞች ፓርቲ ከሥልጣን ተወግዷል።ወይም ታግዷል።ዮርግ ቪያነን የመሳሰሉ ጠንካራ ሴኔናቶሮች ግን አሁንም ይሟገቱላቸዋል።«እዚሕ እኛ ሐገር የተረጋጉና ጠንካራ ተቋማት አሉ እያሉ የሚናገሩ የሚሉ ሰዎች አሉ።እኔ ለሁሉም የምናገረዉ ግን እዚሕ ሐገር የተቋማት ሥርዓተ-አልበኝነት ነዉ የሰፈነዉ ብዬ ነዉ።»

የጥቁር ኬንያዊዉ ተማሪ ልጅ ሥልጣን በያዙ በሰባተኛዉ ዓመት፤ የጀርመኑ ስደተኛ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ሙስሊም እና ስደተኛ ባይኔ እንዳላይ ይሉ ገቡ።ትራምፕ ስደተኞችን በግንብ፤ ሙስሊሞችን በመግቢያ ፍቃድ ለማገድ ሲዝቱ፤ የፓኪስታኑ ሙስሊም ስደተኛ ልጅ፤ ሳዲቅ ካሕን የለንደን ከንቲባ ሆኑ።የቡልጋሪያ ስደተኛዋ ልጅ ከሥልጣን ሲታገዱ፤ የሊባኖሱ ስደተኛ ልጅ ሥልጣን ያዙ።የስደተኛ ልጆች ፖለቲካ።ግን ስደተኛ ያልሆነዉ ማን ነዉ? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ