1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብከለትን የመቀነስ እቅድ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 9 2007

የበካይ ጋዞችን ቅነሳ መንግሥታት ተስማምተዉ በዓለም አቀፋዊ ሕግ ለማሰር እንዲችሉ ድርድሮች ከተጀመሩ ዓመታት ተቆጥርዋል። ለከባቢ አየር መበከል በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ የሆኑት በኢንዱስትሪ ያደጉትና የበለፀጉት ሃገራት የየበኩላቸዉን የበካይ ጋዞች ቅነሳ እቅድ ለማቅረብ ብዙም አልደፈሩም። ኢትዮጵያ ግን እቅዷን ከሰሞኑ ይፋ አድርጋለች።

https://p.dw.com/p/1Fi9i
USA, klima, kohlekraft, CO2, emissionen
ምስል ap

ብክለትን መቀነስ

እዚህ ቦን ከተማ ባለፉት ለ11ቀናት ተካሂዶ ባለፈዉ ሐሙስ የተጠናቀቀዉ የዓለም የአየር ንብረት ለዉጥ ተመልካች ስብሰባ በመጪዉ ዓመት ፓሪስ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀዉ ዋናዉ ጉባኤ መንደርደሪያ ነጥቦች ያስገኛል ተብሎ የታለመ ነበር። ስብሰባዉ ሲጠናቀቅም በቀጣይ ዓመታት የየሀገራቸዉን የካርቦን የብክለት መጠን የመቀነስ እቅድ እንዳላቸዉ 12 ሃገራት አሳዉቀዋል። ከእነዚህ ዉስጥ ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ነዉ የተሰማዉ። እንዲህ ያለዉን እቅድ በማቅረብም ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ሶስተኛዋ ሀገር ናት። እያደገ የሚገኘዉ ኤኮኖሚዋን በአረንጓዴ የኃይል ምንጮች ላይ ለመገንባት የምታደርገዉ እንቅስቃሴም ከአዉስትራሊያ እስከጃፓን የሚገኙ የበለፀጉ ሃገራት እንደአርአያ ሊወስዱት የሚገባ መሆኑን የኦክስፋም ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉዳይ አማካሪ ቲም ጎሪ ተናግረዋል። ዶክተር ተወልደብርሃን ገብረእግዚአብሔርም ይህንን የሚያጠናክር አስተያየት በጉባኤዉ ማጠቃለያ ላይ መገለፁን ነዉ የነገሩን።

Nil Dammbau in Äthiopien Archiv 28.05.2013
ምስል William Lloyd-George/AFP/Getty Images

ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ የታዳሽ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚ ሀገር ናት። ለረዥም ዓመታት ከዉኃ ማለትም የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆና የቆየችዉ ሀገር በቅርብ ዓመታትም ከንፋስ ኃይል የሚያመነጩ ፕሮጀክቶችን ዘርግታለች። ከመሬት ዉስጥ ሙቀት የኃይል ምንጭም እንዲሁ ተጠቃሚ ናት። እንዲያም ቢሆን ግን ከሀገሪቱ ሕዝብ ሶስት አራተኛ የሚሆነዉ የኤሌክትሪክ ኃይል አልተዳረሰዉም። በዚህ ምክንያትም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ካርቦንን ወደከባቢ አየር የሚለቀዉ የማገዶ እንጨት ለመጠቀም የተገደደ ነዉ። ኢትዮጵያ እስከጎርጎሪዮሳዊዉ 2030ዓ,ም ባሉት ጊዜያት የግብርናዉን ዘርፍ፤ እንዲሁም የግንባታና የመጓጓዣ ስልቶችን የንፁህ የኃይል ምንጭ ተጠቅማ የካርቦን ብክለትን 64 በመቶ የመቀነስ እቅድ ነድፋለች።

Zhara Church Forest, Äthiopien
ምስል Matthew Jellings

በቦኑ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ጉባኤ የተሳተፉ 195 ሃገራት ናቸዉ። ኢትዮጵያ ሆነች ሌሎች ጥቂት ሃገራት የካርቦን ልቀት መጠንን በየግላቸዉ ለመቀነስ ማቀዳቸዉን ቢገልፁም ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ ፓሪስ ላይ ለሚካሄደዉ ቀጣይ ጉባኤ መጠነኛ እጅ መንሻ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ላይኖረዉ ይችል ይሆናል። ትርጉም እንዲኖረዉ ግን ሌሎች ዉይይቶችና ድርድሮች የሚካሄዱባቸዉ መድረኮች እስከዚያዉ ድረስ ይካሄዳሉ። ከሐምሌ መጨረሻ እስከ መስከረም የሚካሄዱት ስብሰባዎች በተለይ ከባቢ አየርን በከፍተኛ ደረጃ እየበከሉ መሆናቸዉ በግልፅ የሚታወቅ እንደቻይና እና ዩናይትድ ስቴትስ የመሳሰሉ ሃገራት ላይ ጫና ለማሳደር ነዉ ተብሏል። እንዲህ ካለዉ ድርድር ጎን ለጎንም የፖለቲካ ዉሳኔ ማሳለፍ እና ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ወገኖችንም ማግባባቱ እንደሚቀጥል የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ መርሃግብር ኃላፊ ክርስቲያና ፊጎርስ ጠቁመዋል። ጀርመን በቫርባሪያ ግዛቷ ያስተናገደችዉ የቡድን ሰባት ሃገራት ጉባኤም ከካርቦን ነፃ የሆነ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴን መጥቀሱ የዚህ ጥረት ዉጤት መሆኑን እሳቸዉ ሲጠቁሙ፤ የቀጣዩ የፓሪስ ጉባኤ አስተናጋጅ የፈረንሳይ ተደራዳሪ በበኩላቸዉ ትዕግስት ይኑረን እንጂ ይደረስበታል ሲሉ ጥያቄ ያቀረቡላቸዉን ጋዜጠኞች አጽናንተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ