1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦን፥ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ተከፈተ

ሰኞ፣ ጥቅምት 27 2010

ከ200 ሃገራት የተውጣጡ 25,000 ታዳሚያን ይገኙበታል የተባለው የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ጀርመን ቦን ከተማ ውስጥ ዛሬ ተከፈተ።   የፊጂው ርእሰ-ብሔር ፍራንክ ባይኒማራማ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጽ/ቤት በሚገኝበት ቦን ከተማ ባሠሙት የመክፈቺያ ንግግር የምድር ግለት መጨመርን ለመታገል ጠንካራ ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2n8am
COP23 UN Klimakonferenz in Bonn
ምስል picture-alliance/Geisler-Fotopress

በእንግሊዝኛ ምህጻሩ COP 23 በመባል የሚጠቀሰዉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ተመካች ጉባኤ የዘንድሮ አዘጋጅ ንዑሷ ደሴት ፊጂ ብትሆንም ከአቅሟ በላይ በመሆኑ ነው ጉባኤው ጀርመን ቦን ከተማ ውስጥ የተከፈተው። የጀርመን የከባቢ አየር ጉዳይ ሚንሥትሯ ባርባራ ሔንድሪክስ የምድር ግለትን ከ2 ዲግሪ በታች ለማድረግ የዛሬ ሁለት ዓመት ፓሪስ ውስጥ የተገባው ቃል ቢያንስ በ1,5 ዲግሪ እንኳ እንዲተገበር ጠይቀዋል።  አያይዘውም ሃገራት የጀመሩትን ጥረት እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። 

«ዓለም አቀፉ የአየርን ንብረት ዲፕሎማሲ በተለየ ሁኔታ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው  የምንገኘው። COP 23 የተሰኘው ጉባኤ ዩናይትድ ስቴትስ ከፓሪሱ ስምምነት መውጣቷን ካስታወቀች በኋላ የተደረገ የመጀመሪያ ጉባኤ ነው። ከጥቂት ወራት በፊት አንዱ አንዱን እየተከተለ በመውጣት ሒደቱ በአጠቃላይ የሚከሽፍ ይመስል ነበር። ይህ እንዳይሆንም የሚቻለንን ሁሉ አድርገናል። እናም እስካሁን ሁሉም በአንድነት እንዳለ ነው። ይህ ባለበት ይቀጥላል ብዬ እገምታለሁ።»

COP23 UN Klimakonferenz in Bonn
ምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com

ጀርመን ለአየር ንብረት ጥበቃ የሚውል 50 ሚሊዮን ዩሮ ለመለገስ ቃል መግባቷን ሚንሥትሯ አስታውቀዋል። የቦኑ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ ዋነኛ ዓላማ የምድር ግለትን ለመቀነስ በፓሪስ የተደረገውን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ነው። በምዕራብ ጀርመኗ ቦን ከተማ እና በተለያዩ የጀርመን ከተሞች ከጉባኤው ቀደም ባሉት ቀናት የጀመረ የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬም ተከናውኗል።  የአየር ንብረት ተቆርቋሪዎች ጀርመን በብዛት የምትጠቀመውን የድንጋይ ከሰል የኃይል ምንች እንድታቋርጥም ጥሪ አስተላልፈዋል። የቦኑ የአየር ንብረት ተመልካች ጉባኤ የሚጠናቀቀው የፊታችን ዐርብ ሣምንት ነው።
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ