1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቦኮ ሃራም ከ400 በላይ ሴቶችና ህጻናት ማገቱ

ረቡዕ፣ መጋቢት 16 2007

በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ የዳማሳክ ከተማ ከአራት መቶ በላይ ሴቶች እና ሕጻናት በቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ሳይታፈኑ እንዳልቀረ ተሰማ። የእገታው ዜና እስካሁን በናይጄሪያ መንግስትም ይሁን በታጣቂ ቡድኑ አልተረጋገጠም።

https://p.dw.com/p/1ExXl
Tschad Fahne Soldaten Kampf gegen Boko Haram Nigeria
ምስል Reuters/Emmanuel Braun

የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ከምትገኘው የዳማሳክ ከተማ ከአራት መቶ በላይ ሴቶች እና ሕጻናትን ማገታቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። የሞባር ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ዳማሳክ በቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ቁጥጥር ውስጥ የነበረች ሲሆን በኒጀር እና ቻድ ወታደሮች ነጻ የወጣችው በያዝንው ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ሱሌይማን አሊ የተባሉ ነጋዴ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች 506 ወጣት ሴቶችንና ሕጻናትና ማገታቸውንና ከመካከላቸውም 50ዎቹን እዚያው መግደላቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ የናይጄሪያ መንግስትም ይሁን ታጣቂ ቡድኑ የሰጡት ይፋዊ መግለጫ የለም። ሬድ 24 ለተባለው ተቋም የአፍሪቃ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ሪያን ካሚንግስ የከተማዋ ነዋሪዎች ቀድሞም መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው በመሰደዳቸው ሁነቱንም ሆነ የታገቱትን ሰዎች ቁጥር ማረጋገጥ አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ።

«በቦኮ ሃራም ታገቱ የተባሉትን ሰዎች ቁጥር የዓይን ምስክሮች ላይ መሠረት ያደረገ በመሆኑ ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም አሁን በከተማዋ የሚገኙ የውጭ ጋዜጠኞች በከተማዋ ከ50 ሰው በላይ አለመኖሩንና ብዙዎቹም በእድሜ የገፉ መሆናቸውን እየዘገቡ ነው። ስለዚህ ወጣቶች በተለይም ሴቶች እና ሕጻናቱ በቦኮ ሃራም ሳይታገቱ አይቀርም የሚል ጠንካራ ግምት አለ።»

Symbolbild Entführungen von Frauen und Mädchen in Nigeria
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

የቻድ እና ኒጀር ወታደሮች ወደ ከተማዋ ሲገቡ የ70 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን ሪያን ካሚንግስ ተናግረዋል። ለስድስት ዓመታት በዘለቀው የቦኮ ሃራም የደፈጣ ጥቃት እና ሽብር 300 ሴት ተማሪዎችን መታገታቸው አይዘነጋም። ናይጄሪያ ለምርጫ ሽር ጉድ በምትልበት እና የቀጣናው ሃገራት በቡድኑ ላይ የጋራ ዘመቻ በከፈቱበት በዚህ ወቅት የተሰማው የእገታ ዜና በአገሪቱ መንግስት ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ሪያን ካሚንግስ ይናገራሉ።

«ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት የተደረገው ይህ እገታ በናይጄሪያ መንግስት በተለይም ደግሞ በገዢው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና እንደሚያሳርፍ ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል።»

ባለፈው ወር የናይጄሪያ ጦር ከቻድ እና ኒጀር ወታደሮች ጋር በመሆን በቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ተይዘው ከነበሩ የሰሜን ምሥራቅ ከተሞችን ማስለቀቅ ችለዋል። የከተሞቹ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ግን እንደቀደመው አይደለም። የመንግስት እና አለም አቀፍ ተቋማት በአካባቢው ሥራቸውን ለመከወን መቸገር አስፈላጊ ግልጋሎቶችን ለማቅረብም ሆነ መረጃ ለማጣራት ፈተና ሆኗል። ሪያን ካሚንግስ የእገታው ዜና ሃሰት ሆኖ ቢገኝ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አላቸው።

«ይህ የእገታ ዜና ሃሰት ሆኖ ቢገኝ ማንም አይጠቀምም። እንዲያውም በአካባቢው ለሚገኙት እና መረጃ በማቅረብ ለተባበሩት የኒጀር እና የቻድ ወታደሮች የከፋ ጉዳት ያደርሳል። በከተማዋ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ተዓማኒነትም ያሳጣል። ዜናው ሃሰት ሊሆን የሚችልበት እድል ትንሽ ነው ብዬ አስባለሁ ይሁንና የታገቱትን ሰዎች ትክክለኛ ማንነት እና ቁጥር ማረጋገጡ ግን ፈታኝ ነው።»

በቀጣናው ሃገሮች የትብብር ዘመቻ የተከፈተበት የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ከያዛቸው አካባቢዎች እንዲለቅ እየተገደደ ነው። ቡድኑ ከናይጄሪያም ይሁን ከጎረቤት ሃገራት ወታደሮች ጋር ፊት ለፊት መዋጋት እንደማይፈልግ ሪያን ካሚንግስ ተናግረዋል። ቦኮ ሃራም አሁን ያገታቸውን ሰዎች ለጥቃት እና ለታጣቂዎቹ መሰረታዊ ግልጋሎት እንዲያቀርቡ ሊያደርጋቸው ይችላል ሲሉም ስጋታቸው ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ