1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቫሌታ፤ የአዉሪሮጳ እና የአፍሪቃ ሃገራት ጉባኤ

ሐሙስ፣ ኅዳር 2 2008

የአዉሮጳ እና የአፍሪቃ መሪዎች በስደተኞች ቀዉስ ላይ ዛሬ በማልታ ዋና ከተማ ቫሌታ የሁለት ቀናት ጉባኤ ጀመሩ።

https://p.dw.com/p/1H4DC
Malta EU-Afrika-Gipfel Angela Merkel in Valletta
ምስል picture alliance/AP Photo/A. Tarantino

ወደ አዉሮጳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መበራከቱን ተከትሎ ከስደተኞች መፍለቂያ ሃገራት ጋር መፍትሄ ለመሻት በተዘጋጀዉ በዚህ ጉባኤ 65 ሃገራት እንደሚሳተፉ የጀርመን የዜና ወኪል ከቫሌታ ዘግቧል። የአዉሮጳ መሪዎች የአፍሪቃ አቻዎቻቸዉ ለኤኮኖሚ ስደተኞች በየሀገራቸዉ መፍትሄ እንዲያበጁ እስከ3,6 ቢሊየን ዩሮ ርዳታ ሊሰጡ ማቀዳቸዉ ተገልጿል። የፖለቲካ ተንታኙ ፎዑም ኪማራ በበኩላቸዉ የአዉሮጳ መሪዎች የስደተኛ መፍለቂያ የሆኑ ሃገራትን ሰላም ማረጋገጡ ላይ ቢያተኩሩ እንደሚበጅ ያመለክታሉ።

Symbolbild Afrika Flüchtlinge
ምስል Getty Images/AFP/P. Huguen

«የአዉሮጳ መሪዎች በመጀመሪያ የችግሩ ምንጭ ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፤ ችግሩ የተፈጠረዉ አንዳንድ የአዉሮጳ መንግሥታት የእነዚያን ሃገራት ሰላም በማናጋታቸዉ ነዉ፤ ይህ ደግሞ አለመረጋጋትን ፈጠረ በዚህም ምክንያትም ሰዎች መጠጊያ ፍለጋ በየአቅጣጫዉ ተሰደዱ። ስለዚህ አሁን በእነዚያ ሃገራት ዉስጥ ሰላማን ማረጋገጥ ላይ ማትኮር ይኖርባቸዋል። ብቸኛዉ መፍትሄ ነዉ የሚመስለኝ።»

Italien Afrikanische Flüchtlinge werden gerettet
የጣልያን የባህር ጠረፍ ጠባቂያዎች ያዳኗቸዉምስል picture alliance/ROPI

በተቃራኒዉ የአፍሪቃ መሪዎች ዜጎቻቸዉ በየሀገሩ ተሰደዉ በየጊዜዉ ወደሀገር ቤት የሚልኩት የዉጭ ምንዛሪ እንዲስተጓጎል እንደማይፈልጉ የፈረንሳይ የዜና ወኪል አመልክቷል። የአዉሮጳ መሪዎች ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር የስደተኞችን ጎርፍ በመከላከል፤ በቂ ምክንያት የሌላቸዉ ስደተኞች ወደየመጡበት በመመለስና የሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም ትብብራቸዉ ለማጠናከር አቅደዋል። የአዉሮጳ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ዶናልድ ቱስክ የሁለት ቀኑ የጋራ ጉባኤ «የተግባር» እንቅስቃሴ የሚጀመርበት ነዉ ብለዋል። ከአፍሪቃ ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ 30 በላይ ሃገራት በዚህ ጉባኤ ላይ ይገኛሉ። በስደት የሚገኙት የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኤልሳቤት ጭሩም ስደተኞችን ለማስቀረት ሲባል ለኤርትራ መንግሥት ገንዘብ እንዳይሰጥ፤ ይልቁንም ኤርትራዉያን በስደት ለሚኖሩባቸዉ ሃገራት ቢዉል እንደሚበጅ መጠየቃቸዉ ተዘግቧል።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ