1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቬስተርቬለና የዉጪ መርሐቸዉ

ሰኞ፣ መስከረም 6 2006

በርግጥም በመሪዎቹ ሽኮቻ፣ በወጥ፣ ራዕይ ጉድለት፣ በመርሕ እጠት ከትንሽነት ወደ ምንምነት ያሽቆለለ ትንሽ ፓርቲያቸዉን ለመንግሥት ሥልጣን ተጋሪነት፤ አብቅተዋል።በዚሕ ይወደሳሉ።የምክትል መራሔ መንግሥትነቱን መንበርም፥ ከትቢያ ያነሱትን ፓርቲያቸዉን የሊቀመንበርነት ሥልጣንም እንዲለቁ ያስገደዷቸዉ ግን የራሳቸዉ ፓርቲ የቅርብ ጓዶቻቸዉ ናቸዉ

https://p.dw.com/p/19iRN
FREI FÜR SOCIAL MEDIA Bundesaußenminister Guido Westerwelle (FDP) spricht am 10.09.2013 in Berlin auf einer Pressekonferenz zu den Medienvertretern. Er hält eine deutsche Beteiligung an der Vernichtung syrischer Chemiewaffen für möglich. Deutschland habe bei der Vernichtung von Chemiewaffen erhebliche Erfahrung und auch entsprechende Programme, sagte Westerwelle. Foto: Kay Nietfeld/dpa
ጀርመን ና የአዉሮጳ ሕብረትምስል picture-alliance/dpa

የሰማንያ ሁለት ሚሊዮኖችን ምድር፣ የዓለም ጠንካራ፣ የአዉሮጳ ልዕለ ቱጃር የአዉሮጳ ሕብረት ዘዋሪ ሐገርን የዉጪ መርሕ መዘወር ከጀመሩ በቅርቡ አራት ዓመት ይደፍናሉ።ከትልቂቱ ሐገር ትልቅ ዲፕሎማትነት ጋር ደርበዉት የነበረዉን የምክትል መራሔ-መንግሥትነት ሥልጣንን ግን በተሾሙ በዓመት ከመንፈቅ ለመልቀቅ ተገደዋል።ጊዶ ቬስተርቬለ።በፀረ-ጦርነት ዲፕሎማሲያቸዉ ይወደሳሉ። ምዕራባዉን ሊቢያን መደብደባቸዉን በመቃወማቸዉ ግን በምዕራብ ወዳጆቻቸዉ ተወግዘዋል።ያንድ ጋዜጠኛ አንድ ጥያቄን በእንግሊዝኛ አልጠየቅም በማለታቸዉ የትችት ዶፍ ወርዶባቸዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትልቅ ጉባኤን በእንግሊዝኛ በመምራት ብቃታቸዉ ግን «ጉድ» አሰኝተዋል። ብዙዎች ባንድ ነገር ይሰማሙላቸዋል።ጎበዝ ዲፕሎማት ናቸዉ።ቬስተርቬለ።ሳምንት ከሚደረገዉ ምርጫ በሕዋላ ግን ከሥልጣን ይሰናበታሉ።የጎላ-ብሒል ምግባራቸዉን ላፍታ ዘክረን እንሰናበታቸዉ።


ሰሞኑን የሐብታም፥ ሐያሉ ዓለም ትኩረት፥ የምዕራብ-ምሥራቁ ልዩነት፥ ሶሪያ እና ጦርነቷ ነዉ።ባለፈወር አጋማሽ የሶሪያ መንግሥት ተኩሶታል ተብሎ በሚጠረጠረዉ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ርዕሠ-ከተማ ደማስቆ አጠገብ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደል፥መጎዳታቸዉን እንደ አብዛኛዉ ዓለም፥ መሪ ዲፕሎማት ሁሉ አስለጋጭ አሉት። አወገዙትም።

«ይሕ በጣም አሳሳቢ ነዉ።ጥርጣሬዉ ከተረጋገጠ የሚደርሰዉን ጥፋት በትክክል መግልፅ ለሚፈልጉ ተገቢ ቃላት ጨርሶ አያገኙም።»

የተወገዘዉ አደገኛ ጥቃት እንዳይደገም መፍትሔዉ፥ በሕዝብ ከተመረጡት የዋሽግተን፥ ለንደን፥ፓሪስ መሪዎች የየሐገራቸዉን ሕዝብ በሐይል ፈጥርቀዉ እስከሚገዙት የሪያድ፥ ዶሐ አምባገነን ነገስታት አንድ የሆኑበት አንድ ነዉ።ሶሪያን በጦር ሐይል መደብደብ።ደብዳቢዉን ጦር የምትመራና የምታስተባብረዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ የድብደባዉን ዓለማ-እና የደብዳቢ ጦሯቸዉን ጥቅል ተልዕኮ አስታወቁ።

«ይሕ ግድያ ሲፈፀም ተመልካች ሆነን የምንቀመጥበት ጊዜ ዓይደለም።አምባገነን በምድር ከሚገኙ የጦር መሳሪያዎች ሁሉ እጅግ አደገኛዉን እንዳሻዉ እንዲጠቀም የሚፈቀድበት ጊዜም አይደለም። ጊዜዉ በሽር አል-አሰድን የመሰሉ አምባገነኖች ላደረሱት ጭፍጨፋ ተጠያቂ መሆናቸዉን ለማሳየት ዉስን ግን ግልፅና ዉጤታማ የአፀፋ (እርምጃ የሚወሰድት) ነዉ።»

የብሪታንያ ምክር ቤት የጦር ሐይል ዘመቻ ዕቅዱን ካገደ በሕዋላ ቀዝ ቀዝ አሉ እንጂ ሶሪን አሜሪካኖች በሚመሩት ጦር ለማስደብደብ ከአሜሪካዉ አቻቸዉም በላይ የዛቱ የፎከሩት የብሪታንያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዊሊያም ሔግ ነበሩ።ሔግ ከምክር ቤታቸዉ ዉሳኔ በሕዋላ ከዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች ሲሠወሩ፥ የፈረንሳዩ አቻቸዉ ሎራ ፋቢዩስ እንደ ደረጃቸዉ ከኬሪ ቀጥሎ ሁለተኛዉን ሥፍራ ያዙ።

«ጥርጣሬዉ ከተረጋገጠ ፈጣን አፀፋ ሊሰጥ ይገባል።አፀፋዉ ከባድ መሆን እንደሚገባዉ ከመጀመሪያዉ ጊዜ ጀምሮ ተናግሬያለሁ።አፀፋዉ እንዴት ገቢር ይሆናል ዛሬማታ ልነግራቸዉ አልችልም።»

እንደ መላዉ ዲሞክራሲያዊ ሐገር ባለሥልጣን የበሽር አል-አሰድን አገዛዝ አምባገነናዊነት በተደጋጋሚ የመሠከሩት ፥እንደ አብዛኛዉ ዓለም ኬሚካዊ ጥፋት-ግድያዉን ያወገዙት ጊዶ ቬስተርቬለ መፍትሔዉ ላይ ከሐገራቸዉ የቅርብ ወዳጆች-ከዋሽግተን ለንደን ፓሪስ አቻዎቻቸዉ ተለዩ።

«ክቡራትና ክቡራን፥ የጀርመን ፌደራላዊ መንግሥት የዉጪ መርሕ የተረጋጋና ፅኑዕ መሆኑን ልነግራችሁ (እወዳለሁ።) መርሑ ከሁሉም በላይ ለፖለቲካዊ መፍትሔ ቅድሚያ ይሰጣል።ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት የሚሰፍነዉ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲገኝ ብቻ ነዉ።በሶሪያም ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት የሚሠፍነዉ በፖለቲካዊ መፍትሔ አማካይነት ነዉ።»

ቬስተርቬለ በዲፕሎማሲዉ አተረጓጎም ወታደራዊ እርምጃን በመቃወማቸዉ ሶሪያን ለመደብደብ ይጣጣሩ ከነበሩት ከምዕራባዉን ፖለቲከኞች፥ ዲፕሎማቶች በጋዜጠኞች ሳይቀር ተተችተዉ ነበር።ዛሬ እዉነቱ ሌላ ነዉ። ሞስኮዎች ባቀረቡት ሐሳብ ሰበብ ወታደራዊዉ አማራጭ ዉቅድ ሲሆን የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርን ከሁለት ሳምንት በፊት ያስተቻቸዉ ፖለቲካዊ መፍትሔ-ያስመሰግናቸዉ ገባ።

በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ (ዘመኑ በመሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ምዕራባዉያን ሐገራት ሊቢያን ለመደብደብ ሲዘጋጁም ቬስተርቬለ ድብደባዉን ተቃዉመዉ ነበር።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት «ከበረራ-እግድ ቀጠና» በሚል ሽፋን ሊቢያ እንድትደበደብ በር የከፈተበትን ዉሳኔ መጋቢት-ሁለት ሺሕ አስራ አንድ ሲያሰፀድቅ የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከምዕራባዉያን አቻዎቻቸዉ ተለይተዉ ድምፃቸዉን አቅበዉ ነበር።

ቬስተርቬለ ድምፃቸዉን ያቀቡት፥ ከሚዋጉት የሊቢያ ተፋላሚዎች አንዱን (የያኔዎቹ አማፂያንን) መደገፍ፥ ሌላኛዉን (የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊን) ሐይል መደብደብ ለሊቢያ ዘላቂ ሠላም አይበጅም፥ ከሁሉም በላይ በአረብ ሐገራት የተቀጣጠለዉን ሕዝባዊ አመፅ ያዳፍነዋል በሚል እምነት ነበር።በዚሕ እምነት አቋማቸዉ ግን ከዉጪም ከሐገራቸዉም «አይንሕ-ላፈር» ያላላችዉ ፖለቲከኛ፥ ዲፕሎማት፥ የፖለቲካ አስተንታኝም ከነበረ ከቁጥር የሚገባ አልነበረም።

ዛሬ-ግን የሊቢያ፥ የግብፅ፥ የሶሪያ፥ የሌሎቹ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ አጎንቁሎባቸዉ የነበሩ የመላዉ አረብ፥ የአፍሪቃም እዉነታ-የቬስተርቬለ ተቺ-አዉጋዦችን ያኔ ሕቅ-ያለዉን ሐቅ-አፍግቶታል።ሊቢያ አምባ ገነን መሪዋ በተገደሉ ባመቱ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ተገድለዉባታል።አምባሳደር።ሐብታም ነች።ግን በጎሳዎች ዉጊያ፥ ፖለቲከኞች ሽኩቻ፥ በሠራተኞች ተቃዉሞ ትጥመለመላለች።በርስ በርሱ ጦርነት፥ በምዕራባዉኑ ጦር ድብደባ የወደመ ሐብት ንብረቷን ለመጠገን እንኳ እስካሁን ፋታ አላገኘችም።

ከሊቢያ የተማሩት የሶሪያ የፖለቲካ ልሒቃን ብቅ ያለዉን ሕዝባዊ አመፅ በቅፅበት ወደ ጠመጃ ዉጊያ ቀይረዉታል።በመላዉ አረብ፥ አፍሪቃም ብቅ ብሎ የነበረዉ አመፅም አልቀጠለም።ግብፅ ላይ ብልጭ ያለዉ ዴሞክራሲም ተዳፍኗል።በሕዝባዊ አብዮት ግብፅን ያስከተለችዉ ቱኒዚያም የዲሞክራሲ ጅምርን በማዳፈን ግብፅን ለመከተል ግራ-ቀኝ ትላጋለች።

የምዕራባዉያኑን የግል ያዉም ያጭር ጊዜ ጥቅምን የማስቀደም ወታደራዊ እብሪት፥ የሕዝብን ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ የማደፈኑ እዉነት የፈጋበት፥ ከሁሉም በላይ ሕይወት፥ ሐብት ንብረትን የማወደሙ ጥፋት የተመሠከረበት የጊዜ ሒደት-ቬስተርቬለን ከትንሽ ፓርቲ ፖለቲከኝነት ወደ ትልቅ ሐገር በሳል ዲፕሎማትነት ለዉጧል።በጀርመን ምክር ቤት የዉጪ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር የክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ሕብረት (CDU)-ፖለቲከኛ ሩፕሬሽት ፖሌንስ እንደሚሉት ቬስተር ቬለ በአካልም በመንፈስም ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሆናቸዉን ማንም ያዉቀዋል።


«እንደሚመሰልኝ በሳል ዲፕሎማትነታቸዉን ማስመስከር ብቻ ሳይሆን በአካልም በመንፈስም የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሆናቸዉን ማንም የሚገነዘበዉ ነዉ።ያከናወኗቸዉ፥ የተሳተፉባቸዉ እና ለማከናወን የጣሩባቸዉ ጉዳዮች የጀርመን ጥቅም ከአዉሮጳ ዕድገትና ጥቅም ጋር አስተሳስረዉ ለማስከበር ነዉ።ለጋራ ጥቅም የቆሙ ናቸዉ።ይሕ ማለት ፍላጎታቸዉ የጀርመንን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ለማስከበር አይደለም።ይሕ ደግሞ ጥሩ ነዉ።ቬስተርቬለ በያዙት ሐላፊነት በግልፅ የበሰሉ ናቸዉ።»

የቬስተርቬለ የዉጪ መርሕ፥ በጥቅሉ የጀመርመን፥ በጣሙን ደግሞ በሥልጣን ላይ ያለዉ ተጣማሪ መንግሥት መርሕ ነዉ።በዚሕም ምክንያት ተጣማሪዉ መንግሥት-ባጠቃላይ-መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተለይ መርሑን በዉጤቱም የቬስተርቬለን ምግባር፥ ሙከራና ጥረት ባንድ ወይም በሌላ በኩል መጫናቸዉ ግልፅ ነዉ።

ከሜርክል ጋር መስራት ደግሞ የፖለቲካ ሳይንቲስት ጉተር ሔልማን እንደሚሉት ከባድ ነዉ።
«ሉዓላዊ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ናቸዉ።ግን ጠንካራ አይደሉም።ባሁኑ ጊዜ ሥልጣናቸዉን ነጥብ ለመሰብሰብ ከሚጠቀሙበት አንጌላ ሜርክልን ከመሰሉ መራሒተ መንግሥት ጋር መሥራት ለአንድ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሲበዛ ከባድ ነዉ።»

ሰዉዬዉ ግን እየሠሩ ነዉ።ከትችትም አምልጠዉ አያዉቁም።የጀርመን መንግሥት ለሳዑዲ አረቢያ ሁለት መቶ ታንኮች ለመሸጥ ማቀዱ በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ይፋ ሲሆን ለሰብአዊመብት ከሚሟገቱ ፖለቲከኞች፥ ባለሙያዎችና ሙሕራን ከፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሞት ነበር።ታንኮቹ እንዲሸጡ የወሰነዉ መንግሥት ነዉ።መንግሥቱን የሚመሩት ሜርክል ናቸዉ።የትችት ወቀሳዉ አርጩሜ የሸነቆጠዉ ግን ቬስተርቬለን ነበር።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ፖለቲከኞችም ቬስተርቬለ የሐገሪቱን የዉጪ መርሕና ዓለማ በግልፅ በሚያስረዳ ሰነድ አላሰፈሩም በማለት ይተቿቸዋል።ሥልጣን በያዙ ማግስት በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኘ አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በእንግሊዘኛ ሊጠይቃቸዉ ጠየቀ፥ በጀርመንኛ ካልሆነ ብለዉ እንቢኝ አሉ። የዶቸ ቬለ ጋዜጠኞች ሳይቀሩ እንግሊዘኛ የማይችለዉ አዲሱ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር እያሉ ተሳለቁባቸዉ።

በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ግን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ፕሬዝዳት ሆነዉ ኒዮርክ ለተሰየመዉ የምክር ቤቱ ጉባኤ በኒዮርኮች ቅላፄ እንግሊዝኛዉን ያንቆረቁሩት ያዙ።

«ይሕ ምክር ቤት በልጆች ላይ አደገኛ ጉዳት ከሚያደርሱ ወገኖች ጥበቃ ሊደረግላቸዉ የሚገቡ ተቋማትን ዝርዝር ለማስፋፋት እንደሚወስን ትልቅ ተስፋ አለኝ።ዝር ዝሩ ከሚያካትታቸዉ ተቋማት መሐል ትምሕርት ቤቶችና ሆስፒታሎች ይገኛሉ።ይሕ ትልቅ እርምጃ ነዉ።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በሚጋጩ ወገኖች መካካል የድርጊት መርሐ-ግብር የመኖሩን አስፈላጊነትም አምነንበታል።»

እኒያ የተቹ፥ የተሳለቁ፥ ያሾፉባቸዉ ምን ብለዉ ይሆን? ብቻ ሰዉዬዉ ለየት ያሉ ናቸዉ።ቦን መዳራሻ ባድ ሆኔፍ ነዉ የተወለዱት።የተማሩት። ቦን።በልጅነታቸዉ ተመዝግበዉበት ለነበረዉ ለሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት የሚያበቃ ዉጤት የለሕም ተብለዉ ትምሕርት ቤት እንዲቀይሩ ተገደዱ።ትምሕርቱን ግን በሕግ፥ ዶከተሩበት።

ለዘንድሮዉ ምርጫ የሚወዳደሩበት ፎቶ እንደብዙ ፖለቲከኞች ቦን ዉስጥ በየአዉራ ጎዳናዉ ሞሰሶ ተገጥግጧል።በየፎቶዉ ላይ ወይም ከግርጌዉ የተፃፈዉ የብዙዎቹ ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ዘመቻ መፈክር «ምጣኔ ሐብት እናሳድጋለን» ፥ «የወር ገቢ እንጨምራለን»፥ ማሕበራዊ ድጎማን እናሻሽላለን»፥ «ተፈጥሮን እናስጠብቃለን»---ወዘተ ይላል።የሳቸዉ ግን «ቦን በመንግሥት ዉስጥ» ይላል።«ይሕ የሚሆነዉ በኛ በነፃ ዴሞክራቱ ፓርቲ (በኤፍ ዴፔ) ብቻ ነዉ»።ጨረሰ።

በእርግጥም ቦንን ፌደራላዊዉ መንግሥት ዉስጥ ከወከሉት ሁሉ በትልቁ የወከሉት እሳቸዉ ናቸዉ።በርግጥም በመሪዎቹ ሽኮቻ፣ በወጥ፣ ራዕይ ጉድለት፣ በመርሕ እጠት ከትንሽነት ወደ ምንምነት ያሽቆለለ ትንሽ ፓርቲያቸዉን (ኤፍ ዴፔን) ለመንግሥት ሥልጣን ተጋሪነት፤ አብቅተዋል።በዚሕ ይወደሳሉ።

በሁለት ሺሕ አስራ-አንድ ግን የምክትል መራሔ መንግሥትነቱን መንበርም፥ ከትቢያ ያነሱትን ፓርቲያቸዉን የሊቀመንበርነት ሥልጣንም እንዲለቁ ያስገደዷቸዉ ግን የራሳቸዉ ፓርቲ የቅርብ ጓዶቻቸዉ ምናልባትም እንደ ፓርቲያቸዉ ከምንምነት ለሚንስትርነት ያበቋቸዉ ፖለቲከኞች ናቸዉ።ላንዳዶች ያሳዝናሉ፤ ለሌሎች ያናድዳሉ፥ ለብዙዎች ያስገርማሉ።ግን እንደገና ለየት ያሉ ናቸዉ።የኤፍ ዴፔን የወጣት ማሕበርን የመሠረቱ፥ ለረጅም ጊዜ የመሩም ናቸዉ።ዘንድሮ ግን ሐምሳ-ሁለት ዓመታቸዉ። በግል ሕይወታቸዉ ግብረ-ሰዶማዊነታቸዉን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ናቸዉ።ጊዶ ቬስተርቬለ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Die FDP Mecklenburg-Vorpommern wählt am 06.04.2013 auf ihrem Parteitag in Teschow (Mecklenburg-Vorpommern) eine neue Parteispitze. Vor der Wahl stellt die Partei ihre Kandidatenliste für die Bundestagswahl im September 2013 auf. Foto: Bernd Wüstneck/dpa pixel
ፓርቲያቸዉ-አነሱት-ጣላቸዉ-ወደቀምስል picture-alliance/ZB
German Foreign Minister Guido Westerwelle attends the vote for non-permanent members for a two-year term on the security council at United Nations headquarters in New York USA, 12 October 2010. Germany, Portugal and Canada are competing for the remaning two seats on the United Nations security council. EPA/PETER FOLEY
ተመድምስል picture alliance/dpa
Außenminister Guido Westerwelle (FDP) sitzt am 08.06.2013 in Afghanistan in der Kanzel einer Transall Maschine. Westerwelle trifft sich am Samstag in Kabul unter anderem mit Präsident Karsai. Foto: Nicolas Armer/dpa
አፍቃኒስታንምስል picture-alliance/dpa
Bundeswirtschaftsminister Philipp Rösler (FDP - l-r), Bundeskanzlerin Angela Merkel (CDU), Bundesverteidigungsminister Thomas de Maiziere (CDU) und Bundesaußenminister Guido Westerwelle (FDP) unterhalten sich am 28.08.2013 vor Beginn der Kabinettssitzung im Bundeskanzleramt in Berlin. Foto: Tim Brakemeier/dpa +++(c) dpa - Bildfunk+++
ከሜርክል ጋርምስል picture-alliance/dpa

ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ



ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ