1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃዉሞ በወልቂጤ

Merga Yonas Bula
ረቡዕ፣ ጥር 16 2010

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ ዞን በወልቂጤ ከተማ ከ800 እስከ 10,000 የሚሆኑ ሰዎች አለ ስለሚባለው የመልካም አስተዳደር መጓደል እና ባጠቃላይ በአገሪቱ ስለሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ቅሬታቸውን እና ስጋታቸውን ለማሰማት ዛሬ ለተቃዉሞ መዉጣታቸዉን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/2rSow
Karte Äthiopien englisch

Proteste in Welkite - MP3-Stereo

በከተማይቱ ሆስፒታል ለመገንባት ካሁን ቀደም የተገባዉ ቃል ለምን ዘገየ በሚል ከንጋቱ 12 ሰዓት እስከ ሶስት ሰዓት ድረስ ሰዎች ለታቃዉሞ መዉጣታቸዉን የዞኑ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች አላፍ አቶ ፋንታሁን ወለደማርያማም ለዶይቼ ቬሌ አረጋግጠዋል።

የዛሬዉን ተቃዉሞ በቅርበት የተከታተሉት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለትካ ሳይንስና የዉጭ ግንኝነት መምህር አቶ ዳንኤል መኮንን ለሀኪም ቤቱ  ግንባታ ከዉጭ ገንዘብ እንደተገኘና መሰረተ ድንጋይ ተቀምጦለት «ህዝቡ ግንባታዉን በጉጉት ሲጠብቅ» እንደነበረ ይናገራሉ። እንደ አቶ ዳንኤል አስተያየት፣ የከተማይቱ አስተዳደር የሆስፒታሉን ግንባታ በፍጹም አለማስጀመሩ ሰለማዊ ሰልፈኞቹን አስቆጥቷል።

ለሆስፒታሉ ግንባታ የተገኘው ገንዘብ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ መጥፋቱ ዋናው የተቃውሞው መነሻ ምክንያት ቢሆንም፣ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ መሰረታዊው ችግር አድርገው ያነሱት ግን አሳሳቢ ያሉትን በዞኑ ደረጃ እና በአገሪቱ አሁን የምታየዉን የፖለትካ አለመረጋጋት መሆኑን መምህር ዳንኤል አስረድተዋል።

የዞኑ ኩሙኒኬሸን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ወለደማርያማም ግን የተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጥያቄ  አሁን በአገሪቱ ካለዉ የፖለቲካ ጥያቄ ጋር በምንም እንደማይገናኝ ጠቅሰዋል።

በማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በተነበቡ መረጃዎች መሰረት፣ በትናንትናውም ዕለት በምስራቁ ክፍል በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን በዱግዳ ቦራ ወረዳ ወይም አሌም ጤና በመባል በሚጠራው አከባብ  ወጣቶች ለተቃዉሞ ወጥተው እንደነበር እና የፀጥታ አካላት ወሰዱት ባሉት ርምጃ የሰዉ ህወት አልፏል። ከትናንት በስቲያ ሰኞ ደግሞ በደቡቡ ክፍል በኦሮሚያ ክልል በቦራና ዞን በሞያሌ ከተማም የፀጥታ አካል እንዲሁ ወሰዱት በተባለ ርምጃ ሰዎች መሞታቸዉን የማህበራዊ የመገናኛ ዘዴዎቹ አክለው ጠቅሰዋል። 

መርጋ ዮናስ 

አርያም ተክሌ