1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተቃውሞ በደቡብ ሱዳን ጋዜጠኛ መገደል

ዓርብ፣ ነሐሴ 15 2007

ደቡብ ሱዳናውያን በርካታ ጋዜጠኞች ሐሙስ ነሐሴ 14 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. ጁባ ውስጥ የተገደለው ባልደረባቸውን በማሰብ ከዓርብ ማለዳ አምስት ሠዓት ጀምሮ ለ24 ሰአታት ብዕራቸውን እንደማያነሱ አስታወቁ። ፔተር ሞይ የተባለው ደቡብ ሱዳናዊ ጋዜጠኛ የተገደለው ሐሙስ እለት ከሥራ ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲያቀና ማንነቱ ባልታወቀ ታጣቂ ነበር።

https://p.dw.com/p/1GJeV
Julius Moi
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Patinkin

[No title]

የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ኅብረት ሊቀመንበር ኦሊቨር ሞዲ፤ ግድያው ኾን ተብሎ የተፈፀመ መሆኑን ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። ለዶይቸቬለ በሰጡት ቃለ-መጠይቅም ይኽንኑ አረጋግጠዋል። ኾኖም ጋዜጠኛው በምን ምክንያት እንደተገደለ ማወቅ እንዳልቻሉ አክለው ገልጠዋል።

«በእርግጥ ለምን እንደተገደለ የምናውቀው ነገር የለም። ምክንያቱም ገዳዩ ግድያውን ለምን እንደፈፀመ ሊገለጥልን አልቻለም፤ ቅጥረኛ ይኹን፣ ከሞይ ጋር የግል ጠብ ይኑረው ምንም አናውቅም።»

ግድያው በተፈፀመበት ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች የጥይት ድምጽ መስማታቸውን ይኹንና ገዳዩ ማን እንደኾነ እንደማያውቁ ተናግረዋል። የጋዜጠኛ ፔተር ሞይ ግድያ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ካለፉት ስምንት ወራት አንስቶ የተገደሉ ጋዜጠኞችን ቁጥር ወደ ሰባት አድርሶታል። ግድያው በመላው ዓለም ቁጣ አስነስቷል። የጋዜጠኞች መብት ተከላካይ በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ(CPJ)የምሥራቅ አፍሪቃ ተወካይ ቶም ሮድስ ግድያውን «ትርጉም አልባ» ብለውታል።

LOGO CPJ

«ይሠራበት የነበረው ጋዜጣ አንዳንድ ባልደረቦቹን አነጋግሬያለሁ። እነሱ እንዳሉኝ ከኾነ ለግድያ ሊያደርሰው የሚችል እጅግ ከረር ያለ ሒስ የታከለበት ዘገባ ሊያገኙበት እንዳልቻሉ ነው። የሚያሳዝነው ነገር አኹን ብዙ ለመናገር ጊዜው ገና መኾኑ ነው። ግን አንድ በእርግጠኛነት መናገር የምችለው፤ ይኽ ግድያ በእርግጥም ደቡብ ሱዳናውያን ጋዜጠኞች አንደበታቸውን እንዲለጉሙ አለያም ከዚያም በላይ እንዲፈፅሙ ማሸበሩን ነው።»

ቶም ሮድስ «ደቡብ ሱዳን በታሪኳ አኹን ባለችበት አስቸጋሪ ወቅት ገለልተኛ ድምጾች ከእለት እለት እየታፈኑባት ነው» ሲሉም አክለዋል። ጋዜጠኛ ፔተር ሞይ ከመገደሉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር ባሳለፍነው እሁድ «በሀገሪቱ አፍራሽ» ያሉትን ዘገባ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞችን ሊገድሉ እንደሚችሉ ዝተው ነበር። የደቡብ ሱዳን የጸጥታ ኃይላት ግድያውን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ አለመስጠታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ቶም ሮድስ ግድያው ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው ይላሉ።

«ያነጋገርኩት ባልደረባው እንደገለጠልኝ ከኾነ ኹለቱም እጆቹ ላይ ያሉት ጠቃሚ ንብረቶቹ አልተነኩም። የእጅ ስልኩም ኾነ የገንዘብ ቦርሳው አልተወሰደም። ይኽ የሚያመለክተው ግድያው ኾን ተብሎ ለመፈጸሙ እንጂ የዝርፊያ ድርጊት አለመኾኑን ነው።»

የደቡብ ሱዳን የቀድሞው ጋዜጠኛ ፔተር ጁሊየስ ሞይ አስክሬን
የደቡብ ሱዳን የቀድሞው ጋዜጠኛ ፔተር ጁሊየስ ሞይ አስክሬንምስል AFP/Getty Images/Stringer

የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎች ሰላም እንደተጠሙ፤ የደቡብ ሱዳን መንግሥትም ሰላም እንዲያመጣላቸው አጥብቀው እንደሚሹ የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኞች ኅብረት ሊቀመንበር ኦሊቨር ሞዲ አስታውቀዋል።

«ዜጎች፣ ጋዜጠኞች፣ አለያም ማንኛውም ሰው የሚሻው በሀገሪቱ ሰላም እንዲወርድ ነው። ኹለቱ ወገኖች ወይንም ማንም ይኹን ማን ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ አካላት ስምምነት ላይ ካልደረሱ ይኽ ሰላም ሊመጣ አይችልም።»

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት አዲስ አበባ ውስጥ በተደጋጋሚ የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ደቡብ ሱዳንን በዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ከ180 ሃገራት 125ኛ ላይ አስፍሯታል።

የጋዜጠኛ ፔተር ሞዲ አስክሬን በሚገኝበት መኖሪያ ቤቱ ጁባ ውስጥ ጋዜጠኞች ዛሬ ንግግር ካደረጉ በኋላ አስክሬኑ ለቀብር ካጆኬጂ ወደተባለው የጋዜጠኛው የትውልድ ስፍራ ተወስዷል። በስፍራው የጀርመን ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን በቦታው የነበረ ጋዜጠኛ ተናግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ