1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተከታታይነት የሚጠይቀው ጣናን የመታደጉ ጥረት

ማክሰኞ፣ ጥር 15 2010

እምቦጭ የሚል ስያሜ የተሰጠውን የዉኃ ላይ አረም ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የዘመቻ የመሰሉ እንቅስቃሴዎች በክረምቱ እና ክረምቱ ከወጣ በኋላም ታይተዋል። ይህ የዉኃ ቀበኛ ተክል ግን እንደውም ከዚህ ቀደም ወዳልታየባቸው አካባቢዎች ሁሉ እየተዛመተ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። አረሙን የማጥፋት የሚደረጉ ጥረቶች እንዴት ይቀጥሉ?

https://p.dw.com/p/2rNaL
Wasserhyazinthen  Lake Tana Äthiopien
ምስል Adugnaw Admas

ከሰው ኃይል ጋር በርከት ያሉ ማሽኖች ለማጥፋቱ ቢሰማሩ ይመከራል

 

አገሬው እምቦጭ እያለ የሚጠራው የዉኃ ላይ አረም የጣና ሐይቅ ከወረረ ከስድስት ዓመታት በላይ እንደተቆጠረ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ የአካባቢው ምሁራን ይናገራሉ። ቀደም ሲል በሐይቅ አቅራቢያ የሚኖሩ አርሶ አደሮች እየቆረጡም ሆነ እየነቀሉ ሊያጠፉት የሞከሩ ቢሆንም እያደር መስፋፋቱ የቀጠለው አግባብ ያለው አረሙን የማጥፋት ርምጃ ባለመወሰዱ እንደሆነ ነው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዉኃ ስነምህዳር ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር አያሌው ወንዴ የገለፁልን። የሐይቁን ዉኃ በክረምት እና በጋ የሚኖር የመቀነስ እና መጨመር ሁኔታ ተከትሎ መሬቱን ለእርሻም ሆነ ለግጦሽ በዘፈቀደ መጠቀሙም ሌላው አረሙን የልብ ልብ ሰጥቶ ለመስፋፋቱ መንስኤ መሆኑንም ይናገራሉ።

አረሙን ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት የተፈለገውን ያህል ውጤት ማምጣት ያልቻለው ተከታታይ ሥራ ባለመሠራቱ እንደሆነ ነው ዶክተር አያሌው ወንዴ ያስገነዘቡት። እምቦጭ በሚወገድበት ጊዜ የሚወድቁ ፍሬዎቹም ሆኑ ቅንጣቢዎቹ የመብቀል እና የመራባት ዕድላቸው ሰፊ መሆኑም ልብ እንዲባልም አሳስበዋል። ጣና ላይ ቀደም ሲል አረሙን ያስተዋለው የአካባቢው አርሶ አደር የክረምቱን ወራት እየጠበቀ በራሱ ዘዴ ሲያጠራው መሰንበቱን በማስታወስም፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ በስፋት በመነገሩ ሌላው ወገን ማሽን ይዞ መጥቶ ይረዳኛል በሚል መዘናጋት እንደታየበትም ሳይጠቅሱ አላለፉም። የማሽን ጉዳይ ከተነሳ በውጭ ሃገራት ያሉ ለዚህ ተግባር የሚውሉ ማሽኖችን ተመልክቶ የራሱን ዲዛይን ቀርጾ ማሽኑን በመሥራት ሙከራ ያደረገ ወጣት የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ አራጋው ደስታ ስለጥረቱ እንዲህ ይላል።

Äthiopien - Tana See - Kleine Maschine
አራጋው የሠራት ትንሿ የእምቦጭ መንቀያ ማሽንምስል Aragaw Desta

ይህ ማሽን እምቦጩን ነቅሎ ያዘለውን ውኃም ጨምቆ የሚያወጣ ነው። አራጋው እንደታዘበው የአረሙ 95 በመቶ ውኃ ነው። በጣና ሐይቅ ላይ እንደልቡ የተንሰራፋው እምቦጭ አረም ታዲያ በዚህች ትንሽ ማሽን ተነቅሎ እንደማያልቅ የገለፀው አራጋው ሌሎች ተጨማሪ ማሽኖች ስለሚያስፈልጉ ያንን እውን ለማድረግ ድጋፍ እያፈላለገ መሆኑንም ተናግሯል። የግሉ አቅም እጅግም ስለማያወላዳም ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተለቅ ያለ እና እሱ ከሰራት ከመጀመሪዋና ማሽን አምስት እጥፍ መያዝ የምትችል በመሥራት ሂደት ላይ መሆኑንም ያብራራል። 50 በመቶ ሥራው መከናወኑን የገለፀልንን የማሽን ግንባታ ሥራ ለማጠናቀቅም ለሥራው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ግዢ ፈጣን ባለመሆኑ እንጂ በአንድ ወር ውስጥ ሊያልቅ ይችል እንደነበረም ሳይገልጽ አላለፈም። በዚህ ሥራው የማማከሩን ድርሻ የያዙት መምህሩ አቶ ብሩክ ግርማም ትልቅ ሚና እንዳላቸው ነው ከአራጋው የተረዳነው።

Äthiopien - Tana See - Kleine Maschine
ትንሿ እምቦጭ መንቀያ ማሽን በሙከራ ሥራ ላይምስል Aragaw Desta

የጣና ሐይቅ መጎዳት የብዙዎችን ስሜት የነካ መሆኑን አፅንኦት የሰጡት አቶ ብሩክ ለማሽኑ የሚሆኑ የተወሰኑ ዕቃዎችን ማምረት ገሚሱን ደግሞ በፍጥነት መግዛት ቢቻል አንድ ብቻ ሳይሆን በርከት ያሉ ማሽኖችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መሥራት ይቻል እንደነበርም አመልክተዋል።

ከጣና ሐይልቅ ላይ እምቦጭን ለማጥፋት ማሽን በመገንባት ሥራ የተጠመደው አራጋው ደስታ በየጊዜው የአረሙን ይዞታ እየተመላለሰ እንደሚመለከት ነው የነገረን። እሱም ሆነ ሌሎቹ ወገኖች ያስተዋሉት እምቦጭን በሰው ኃይል ብቻ ማጥፋት ከማድከም የዘለለ ውጤት እንደማይኖረው ነው።

እምቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ ይሰማል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች የሚሰጧቸዉን ምክሮች ከግምት በማስገባት ጥረቶቹ ለውጤት እንዲበቁ ማድረጉ አማራጭ የሚኖረው አይመስልም። እናም ዛሬም ጣና ድረሱልኝ ማለቱን እንደቀጠለ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ